ዛሬ ከዋና አሰልጣኙ ገብረክርስቶስ ቢራራ እና ከክለቡ አመራሮች ጋር የተለያየው ወላይታ ድቻ ደለለኝ ደቻሳን ጊዜያዊ አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙን በተለይ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ደለለኝ ደቻሳ ክለቡን በቀጣዮቹ ጨዋታዎች እየመራ ይዘልቃል፡፡ በወላይታ ውስጥ በሚገኙ የታዳጊ ፕሮጀክቶችን በማሰልጠን የአሰልጣኝነት ህይወቱን የጀመረው ይህ ወጣት አሰልጣኝ ዐምና የአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ወደ ዋናው ቡድን ከመጣ በኋላ የአሰልጣኝ ዘነበን ስንብት ተከትሎ ክለቡን በሁለት ጨዋታ ላይ መርቶ ማሸነፍ ችሎ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። በሁለተኛው ዙርም የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ረዳት በመሆን የዘለቀ ሲሆን ዘንድሮ በገብረክርስቶስ ቢራራ የአሰልጣኝነት ዘመን ግን ግዛቸው ጌታቸው በረዳትነት በመሾሙ በቡድን መሪነት እየሰራ ከቆየ በኃላ ነው የዋና አሰልጣኙን ስንብት ተከትሎ በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ክለቡን እንዲመራ የተመረጠው፡፡
በተያያዘ ዜና ክለቡ ሌሎች ጊዜያዊ ሹመት አከናውኗል፡፡ አቶ ምትኩ ኃይሌ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ፣ የክለቡ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ የነበረው ዘላለም ማቲዮስ የቡድን መሪ እና ቴክኒክ አማካሪ በመሆን የተሾመ ሲሆን አቶ ሚካኤል ዋዳን ደግሞ የደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ሆነዋል፡፡
ወላይታ ድቻ ከሁለተኛው ዙር ጀምሮ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር እቅድ እንዳለው ሲጠቆም ከቡድን መሪነቱ ተነስቶ የነበረው አብዲ ራዋም ዳግም ወደ ቦታው ክለቡ ይመልሰዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
©ሶከር ኢትዮጵያ