“በእግር ኳስ ውስጥ ሁሌም ማድረግ ያለብህ ትልቁ ነገር ስህተትን ማፈንፈን ነው” አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል

በፓናማ እና ኮስታሪካ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ጨዋታቸውን ቅዳሜ እለት አድርገው በሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ ትላንት ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ የ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ከሶከር ኢትዮጽያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

ስለ ውጤቱ

ውጤቱ ይገባናል። ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ከመጣው ሰዓት ጀምሮ የማስበው ውጤታማ ቡድን መስራት ነው። ለዚህ ይረዳን ዘንድ ብዙ የክለቦችን ጨዋታ እየተዟዟርን ተመልክተን ነው ምርጫ ያከናወንነው። የቅድመ ማጣሪያው ተጋጣሚያችን ቡሩንዲ ከመሆኗ አንፃር አጫዋወታቸውን ለማጥናት ተሞክሯል። ከልጆቻንን ጋር ስነ-ልቦናዊ ቅድመ ዝግጅት እና ታክቲክ ላይ አትኩረን ነበር የሰራነው። ቡድኔ በዝግጅቱ ወቅት በመፈራራት ሳይሆን በመከባበር ነበር ሲሰራ የቆየው። በዚህም ልጆቻችን እንዲይዙት የፈለግነውን ነገር ሜዳ ላይ ተግብረውታል።

ስለተጋጣሚ እና ስለጨዋታው

ተጋጣሚያችንን ቡሩንዲን ቀደም ብለን ለማውቅ ጥረናል። ቡድኑ ውስጥ በውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ጭምር ያካተቱ ሲሆን በጨዋታው በመጀመሪያ ያደረግነው ስህተቶችን እንዲፈጥሩ ነበር የጣርነው። በእግር ኳስ ውስጥ ሁሌም ማድረግ ያለብህ ትልቁ ነገር ስህተትን ማፈንፈን ነው። በዛ አጋጣሚ የምታገኘውን ወደ ውጤት መለወጥ ነው። ተጫዋቾቼ ይህን በሚገባ ተረድተውን ተግብረውታል፤ በዚህም ውጤታማ ሆነናል። በቀጣይም ይህ ቡድን በዚሁ ጥንካሬ የሚቀጥል ከሆነ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን በርካታ ተጫዋቾችን ማግኘት ይቻላል።

ስለቀጣዩ ጨዋታ

እግር ኳስ ላይ ከምንም በላይ የሚወስንህ በእለቱ ያለህ አቋም ነው። ተጋጣሚያችን ወደዚህ ሲመጡ ምን ይዘው እንደሚመጡ አናውቅም። እግር ኳስ እገሌ ስለተጠራ እሱ ወይም እሱ ሁሌም ይጫወታል ማለት አይደለም። በቀጣዩም ጨዋታ አቅም ያለው ይሰለፋል።

በስተመጨረሻ

ገና ጀምርነው እንጂ አልጨርስንም። አቅማችን የፈቀደውን ሁላ ለማድረግ እኔም ልጆቹም እንዲሁም የሙያ አጋሮቼ በሙሉ ዝግጁ ነን። በቀጣይ ፌዴሬሽኑ ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ለቡድነለ ቅርብ ሆነው እንዲረዱ በትህትና እጠይቃለው። ስለተገኘው ውጤት የኢትዮጵያን ህዝብ እንኳን ደስ ያላችሁ እላለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ