የፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከአስራ አምስት ቀናት እረፍት በኋላ በዚህኛው ሳምንት ሲመለስ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያልተጠበቀ ሽንፈት በማስተናገድ ደረጃውን አዳማን ለረታው ፋሲል ለማስረከብ ተገዷል። መቐለ ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ድል ሲያስመዘግብ ሲዳማም ተከታታይ አራተኛ ድሉን አሳክቷል። ኢትዮጵያ ቡና በሳምንቱ ከፍተኛ ግብ በማስቆጠረ ያሸነፈ ቡድን ሲሆን ድሬዳዋ ከተማም ከወራጅ ቀጠናው ማምለጡን ቀጥሎበታል። እኛም እንደተለመደው በዚህኛው ሳምንት ትኩረት ሳቢ የነበሩ ክለብ ነክ ጉዳዮችን በተከታዩ ፅሁፋችን ዳሰናቸዋል።

👉የኢትዮጵያ ቡና አስደናቂ ድል እና የተተረማመሰው ስሑል ሽረ

በ16ኛ ሳምንት የመጀመሪያ የጨዋታ ቀን ኢትዮጵያ ቡናዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም ስሑል ሽረን አስተናግደው ከሙሉ የጨዋታ የበላይነት ጋር 6-1 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች በሁለቱም አጋማሾች ሦስት ሦስት ግቦችን አስቆጥረው ወጥ የሆነ ዕለት ማሳለፋቸውን ባስመሰከሩበት ጨዋታ አቡበከር ናስር ሐት-ትሪክ ሲሰራ የመስመር አጥቂው ሀብታሙ ታደሰ ሁለት እንዲሁም ሚኪያስ መኮንን ቀሪዋን አንድ ግብ አስቆጥረዋል። ለሽረ ደግሞ ሀብታሙ ሸዋለምም የዓመቱ አምስተኛ ፍፁም ቅጣትምቱን እንደተለመደው ማስቆጠር ችሏል።

በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ላይ ወላይታ ድቻን በመርታት ከውጤት ማጣት ጋር በተያያዘ ገብተውበት ከነበረው የስነ ልቦና ጫና በመላቀቅ የመጀመሪያው ዙሩን በድል ያጠናቀቁት ቡናማዎቹ ከ15 ቀናት እረፍት መልስ በጀመረው የሊጉ ሁለተኛ ዙር ደግሞ በዚህ አስደናቂ ድል መጀመር ችለዋል።

ወጣቱ አጥቂ አቡበከር ናስር በደመቀበት ጨዋታ ስሑል ሽረዎች መከላከል ሽግግር ወቅት የነበራቸው እጅግ የተተረማመሰ ቦታ አያያዝ እንዲሁም አንድ ኳስ የያዘን የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች ለማስጣል በቁጥር በርከት ብለው ይሄዱበት የነበረው መንገድ አንድ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ እርከን ከሚጫወት ቡድን እጅግ የማይጠበቅና በርካቶች ቡድኑ በመጀመሪያው ዙር የነበረውን መልካም ጉዞ ጥያቄ ውስጥ የከተተ እጅግ የወረደ የጨዋታ ቀን አሳልፈዋል።

ከቀናት በፊት የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥር የፈፀሙት ሽረዎች በሁለቱ ምክትል አሰልጣኞች እየተመሩ ባደረጉት በዚሁ ጨዋታ በዚህን ያህል የግብ ልዮነት መሸነፋቸው ለአዲሱ አሰልጣኝ ከፊቱ የተደቀነውን የቤት ስራ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ጨዋታ ነበር። በቀጣይም ከግማሽ የውድድር ዘመን በኋላ ወደ ሜዳቸው በሚመለሱበት መርሐ ግብር ከጠንካራው ሲዳማ ቡና ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ አንዳች አውንታዊ ውጤት ይዘው በመውጣት ከዚህ አስደንጋጭ ውጤት ለመንቃት ይጠባበቃሉ።

👉 የፋሲል ከነማ ድል እና የተሻሻለው አዳማ ከተማ

ሜዳቸው በመቀጣቱ ሳቢያ ወደ ባህር ዳር አቅንተው አዳማ ከተማን ያስተናግዱት ፋሲል ከነማዎች በ14ኛው ደቂቃ በዛብህ መለዮ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ የተሻሻለው አዳማ ከተማን በማሸነፍ ወደ ሊጉ አናት ዳግም የተመለሱበትን ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል።

ለወትሮው በቋሚነት ከሚጠቀሙባቸው ተጫዋቾች ውስጥ በአስገዳጅ ምክንያት የአራት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ የገቡት ፋሲል ከነማዎች በአመዛኙ የጨዋታ ክፍለጊዜ በተጋጣሚያቸው አዳማ ከተማ የበላይነነት ቢወሰድባቸውም ወሳኟን ሦስት ነጥብ ይዘው ከመውጣት ያገዳቸው የለም።

በጨዋታው በርከት ያሉ የግብ እድሎችን ያገኙት አዳማ ከተማዎች እድሎችን ወደ ግብነት መቀየር ባለመቻላቸው ብቻ ከባህርዳር ስታዲየም ተሸንፈው ሊወጡ ችለዋል። በአንፃሩ ለዋንጫ እየተፎካከሩ የሚገኙት ፋሲሎዎች በመሰል በተጋጣሚ ብልጫ በተወሰደባቸው ጨዋታዎች ላይ እንኳን ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው መውጣታቸው በበጎነት የሚጠቀስ ነው።

👉ወልቂጤ ከተማ አሁንም ፈታኝ ቡድን መሆኑን አስመስክሯል

ዘንድሮ ሊጉን የተቀላቀሉት ወልቂጤዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ጠንካራውን ቅዱስ ጊዮርጊስ በጫላ ተሺታ ብቸኛ ግብ በመርታት አስደናቂ ውጤትን አስመዝግበዋል።

አዲስ አዳጊዎቹ ወልቂጤ ከተማዎች በርከት ያሉ በከፍተኛ ደረጃ የመጫወት ልምድ የሌላቸውን ተጫዋቾች ከተወሰኑ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ጋር በመቀላቀል ጥሩ የውድድር ዘመን እያሳለፉ ይገኛል። በውድድሩ የመጀመሪያ ሳምንታት ግብ ለማስቆጠር አይናፍር የነበረው የቡድኑ የአጥቂ መስመር አሁን ላይ ቅርፅ እየያዘ የመጣ ይመስላል። በተለይ በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ወደ ዓዲግራት አምርተው ከወልዋሎ ጋር ያደረጉት ጨዋታ የዚህን መሻሻል ሁነኛ ማሳያ ነው። በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታም ከተጋጣሚያቸው በተሻለ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን በመልሶ ማጥቃት መፍጠር ቢችሉም ከአንድ አጋጣሚ ውጭ ሌሎቹን መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።

በእሁዱ ጨዋታ ላይ በመጀመሪያ ዙር የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ ከነበረው የመከላከል አወቃቀር ውስጥ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ሁለቱ የመሀል ተከላካዮች ቶማስ ስምረቱ እና ዐወል መሐመድ በተለያዩ ምክንያቶች ባይኖሩም ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ የነበረውን ጥንካሬን ማስቀጥል ችለዋል።

ለግምት አስቸጋሪ የሆነውና ተለዋዋጭ መልክ ያለው ቡድኑ በተለይ ከሜዳቸው ውጭ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ጠቅጠቅ ብለው ለመከላከል የሚሞክሩበት እንዲሁም ሲያስፈልግ የጨዋታውን ሒደት ለማቀዝቀዝ የሚያደርጉት ጥረት የሚደነቅ ነው። በተጨማሪም ኳስ በእግራቸው ሲገባ በረጃጅም ኳሶች የፈጣኖቹን አጥቂዎች ፍጥነት ለመጠቀም የሚያደርጉት ጥረት ቡድኑ ለተጋጣሚዎች እጅግ ፈታኝ ሲሆን እየተስተዋለ ይገኛል።

👉ወሳኝ የሜዳ ውጭ ድል ያስመዘገበው መቐለ 70 እንደርታ

ወጣ ገባ የሆነ የመጀመሪያ ዙር ያሳለፉት መቐለ 70 እንደርታዎች ሁለተኛውን ዙር በወሳኝ የሜዳ ውጭ ድል መጀመር ችለዋል። ወደ ሆሳዕና አምርተው በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘውን ሀዲያ ሆሳዕናን የገጠሙት መቐለ 70 እንደርታዎች ኦኪኪ አፎላቢ በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው ተመልሰዋል።

በፕሪምየር ሊጉ አብዛኛዎቹ ክለቦች በሜዳቸው በሚያደርጉት ጨዋታ ላይ ማሸነፍ የተለመደ ከመሆኑ አንፃር በሰንጠረዡ አናት የሚገኙ ክለቦች ልዩነት ለመፍጠር ከሌሎቹ በተሻለ መሰል የሜዳ ውጭ ድል ቁልፍ ሚናን ይጫወታሉ።

ነጥባቸውን ወደ 28 በማሳደግ በጎል ልዩነት ተበልጠው በ3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት መቐለዎች መሐል ሜዳ ላይ በመጀመርያው ዙር የነበረባቸውን ክፍተት ለመድፈን የተሻሉ ዝውሮሮችን ፈፅመዋል። በዚህም በሁለተኛው ዙር ከመጀመሪያው የተሻለ የውድድር አጋማሽ ለማሳለፍ የተዘጋጁ ይመስላል።

👉 ወልዋሎ አሁንም መሪነቱን ማስጠበቅ እንደተሳነው ቀጥሏል

ከአስደናቂ ጅማሯቸው ማግስት የድል መላው የጠፋቸው ወልዋሎዎች አሁንም ሁለተኛውን ዙር በተንገራገጨ መልኩ ጀምረዋል። በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ ከመምራት ተነስተው አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ሰበታ ከተማን እስከ 63ኛው ደቂቃ በፈጣኖቹ አጥቂዎቻቸው ጁንያስ ናንጂቡና ኤታሙና ኬይሙኒ ሁለት ግቦች ሲመሩ ቢቆዩም በዳዊት እስጢፋኖስ ሁለት የቅጣት ምት ግቦች የኋላ ኋላ አቻ ለመውጣት ተገደዋል።

በአዲሱ አሰልጣኛቸው ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ እየተመሩ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉ ሲሆን አሰልጣኙን ይህን የመከላከል ሚዛን ለማሻሻልና የተከላካይ መስመሩን ተጋላጭነት ለመቀነስ በማሰብ ለወትሮው ቡድኑ ከሚከተለው አጨዋወት በተለየ በቅርቡ ከአዳማ ከተማ ቡድኑን የተቀላቀሉት ዐመለ ሚልኪያስ እና ዮናስ በርታን ከተከላካዮቻቸው ፊት በመጠቀም ከክፍት ጨዋታ የሚመጡ ጥቃቶችን በመከላከል ረገድ የመከላከል ፍንጭ ቢያሳዩም ከቆሙ ኳሶች በተቆጠሩ ሁለት ግቦች አሁንም አቻ ለመለያየት ተገደው በታደሰው ስታዲየማቸው የመጀመሪያውን ሙሉ ሦስት ፍለጋቸው አሁንም ቀጥሏል።

ለተከታታይ ሁለተኛ ተከታታይ ሳምንት በእጁ የገባውን ሶስት ነጥብ አሳልፎ የሰጠው ቡድኑ ከፍ ባለ ደረጃ እየተፎካከረ ለመቀጠል በቀላሉ ግብ የሚያስተናግዱበትን ችግር በአፋጣኝ መፈተሽ ይኖርበታል።

👉ድሬዳዋ ከተማ እያንሰራራ ይገኛል

በ16ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ድሬዳዋ ላይ ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው ድሬዳዋ ከተማ 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ካንዣበበበት የወራጅነት ስጋት ለመላቀቅ እያደረገ የሚገኘውን ግስጋሴ አሳምሯል። ሪችሞንድ አዶንጎ አንድ እንዲሁም አማካዩ ቢንያም ጾመልሳን ሁለት ግቦችን ባስቆጠሩበት በዚህ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ በጊዜያዊ አሰልጣኝ ፍሰሃ ጥዑመልሳን እየተመሩ ሁለተኛ ተከታታይ ጨዋታቸውን በሜዳቸው ማሸነፍ ችሏል።

በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በአጋማሹ የዝውውር መስኮት እያስፈረሙ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች ከአዳዲስ ፈራሚዎቻቸው መካከል የመስመር ተጫዋቹ ሄኖክ ኢሳይያስን ብቻ በእሁዱ ጨዋታ ተጥቀመዋል።

ቀስ በቀስ ከወራጅ ቀጠና እያመለጡ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች በተከታታይ ሁለት የጨዋታ ሳምንት ባስመዘገቧቸው ድሎች ነጥባቸው 20 በማድረስ ወደ 11ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችለዋል። በቀጣይ ደግሞ ፋሲል ከነማን በተመሳሳይ በሜዳቸው የሚያስተናግዱ በመሆኑ ከዚህ ጨዋታ ድል ማግኘት ይበልጥ ከወራጅ ቀጠናው ሊያርቃቸው ይችላል።

👉 ባህር ዳር ከተማ በሜዳው አሁንም የሚቀመስ አልሆነም

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው ባህርዳር ከተማ አሁንም በሜዳው የሚቀመስ አልሆነም። በዚህኛው ሳምንት ደግሞ በቀድሞ አሰልጣኛቸው ጳውሎስ ጌታቸው የሚመራው ጅማ አባ ጅፋርን 1-0 ማሸነፍ ችሏል።

እንደ ወትሮው በርከት ያለ ግብ ማስቆጠር ባይችሉም በ40ኛው ደቂቃ ፍፁም ዓለሙ ያስቆጠራት ብቸኛ ግብን አስጠብቀው መውጣት ችለዋል። ሌላኛው የዚህ ጨዋታ ትሩፋት ቡድኑ ለተከታታይ ጨዋታ ምንም ግብ ሳያስተናግድ መውጣቱ ነው። በሁለተኛው አጋማሽ ጥንቃቄን መርጠው የተጫወቱት ባህር ዳር ከተማዎች ጥረታቸው ሰሞሮ ግብ ሳያስተናግዱ መውጣት መቻላቸው ለአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ስብስብ ከነጥቡ እኩል የሚታይ ስኬት ነው።

የነጥብ መጠጋጋቶች በስፋት በሚስተዋሉበት የሊጉ ሰንጠረዥ ባህርዳር ከተማ ነጥቡን ወደ 26 ያሳደገው ቡድኑ ከመሪው ፋሲል ከነማ በሦስት ነጥቦች ብቻ አንሶ ወደ አምስተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል።

👉 8 ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታ ሲዳማ አሸንፏል

በሳምንቱ እጅግ ተጠባቂ ጨዋታ ሀዋሳ ስታዲየም ላይ ወላይታ ድቻን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና 5-3 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ጣፋጭ ድል ማስመዝገብ ችሏል።

ጠንካራ ፉክክርን ባስተናገደውና ከጨዋታው ጅማሮ አስከ ፍፃሜው ድረስ በጎሎችና በተለያዩ ሁነቶች የተጀበው ጨዋታ ስታዲየም የተገኙ ደጋፊዎችን እጅግ ዘና ያሰኘ ጨዋታ ነበር። የሲዳማ ቡና የአጥቂ መስመር አሁንም ምን ያህል አስፈሪ እንደሆነ የታየ ሲሆን በተመሳሳይ የመከላከል ሒደታቸውም አሁንም ስራዎች እንደሚያስፈልጉት ያስመለከተ ጨዋታ ነበር።

ሀብታሙ ገዛኸኝ ሐት-ትሪክ በሰራበት ጨዋታ ዳዊት ተፈራ እና አዲስ ግደይ ቀሪዎቹን ግቦች ለሲዳማ አስቆጥሯል። በአንፃሩ የሲዳማ ቡናዎችን ፈጣን አጥቂዎች ለመቆጣጠር ተቸግረው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች በቀላሉ ግቦችን ቢያስተናግዱም ብርቱ ፉክክር ማድረግ ችለዋል። እድሪስ ሰዒድ ሁለት እንዲሁም ባዬ ገዛኸኝ የወላይታ ድቻን ግብ ማስቆጠር ችለዋል።

ሲዳማ ቡና በተከታታይአራተኛ ጨዋታውን በማሸነፍ ወደ ዋንጫ ተፎካካሪነት መመለሱን ሲያሳይ ጎሎችን ለማስቆጠር የማይቸገር ቡድን መሆኑን በድጋሚ አሳይቷል። በዚህም 33 ጎሎች በማስቆጠር ከየትኛውም ቡድን ቀዳሚው ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ