አዲሱ የወልዋሎ አሰልጣኝ ስለ ቀጣይ አቀራረባቸው ተናግረዋል

“በሁለት ቀን መጥቼ ሌላ አዲስ አጨዋወት ፈጥሬ ቡድኑን ውዥንብር ውስጥ መክተት አልፈልግኩም” ዘማርያም ወልደ ጊዮርጊስ

በመጀመርያው ዙር ሳቢ ያልሆነ አቀራረብ ከነበረባቸው ቡድኖች ውስጥ ወልዋሎዎች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። በዚህም መነሻነት ከሳምንት በፊት አዲስ አሰልጣኝ ሆነው የተሾሙት ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ በሁለተኛው ዙር የአጨዋወት ለውጦ እንደሚኖር አስረግጠው ተናግረዋል።

በትናንትናው ዕለት ሁለት ልምምዶች ብቻ አሰርተው ቡድናቸውን ይዘው የገቡት አሰልጣኝ ዘማርያም በጨዋታው ስለተከተሉት አጨዋወት እና ስለቀጣይ የቡድኑ አጨዋወት ከጨዋታው በኃላ ሀሳባቸው ሲሰጡ በሁለት ቀን ልምምድ ቡድኑን ውዥንብር ውስጥ ለመክተት እንዳልፈለጉ እና የቡድኑ አጨዋወት ለመቀየር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

“በሁለት ቀን መጥቼ ሌላ አዲስ አጨዋወት ፈጥሬ ቡድኑን ውዥንብር ውስጥ መክተት አልፈልግኩም። ነገር ግን የተወሰነ ጥገና ለማድረግ ሞክሬያለው። እኔ ይሄ መጫወት የምፈልገው አጨዋወት አይደለም። ቡድኑ ከዚህ ቀደም በረጃጅም ኳሶች ነበር ሲጫወት የነበረው። በአንድ ጊዜ ከዚ አጨዋወት ማውጣት ደግሞ ከባድ ነው። በሒደት ከጨዋታዎች በኋላ ግን ማሻሻያዎች አድርገን አቀራረቡን እንለውጠዋለን። ” ብለዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ