ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

ድሬ ላይ የሚደረገውን የ17ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

ሁለተኛ ዙሩን በፌሽታ የጀመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ያገኙትን ሁለት ተከታታይ ድል ለማስቀጠል እና ካለባቸው የወራጅነት ስጋት ለመላቀቅ ፋሲልን ይገጥማሉ።

የድሬዳዋ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አቻ ተሸነፈ

በጊዜያዊው አሰልጣኝ ፍሰሃ ጥዑመልሳን እየተመራ ወደ ጥሩ ጎዳና እየተንደረደረ ያለ የሚመስለው ድሬዳዋ በርከት ያሉ ተጨዋቾችን ወደ ቡድኑ በመቀላቀል ቡድኑን እያዋቀረ ይገኛል። በተለይ ቡድኑ ከፍተኛ የወራጅነት ስጋት ስላለበት ጨዋታዎችን በጥንቃቄ መከወን ጀምሯል። ባሳለፍነው ሳምንት ጨዋታም ሀዋሳን በሜዳው በመጋበዝ 3-1 አሸንፏል።

ቀጥተኝነትን አዘውትሮ የሚጠቀመው ቡድኑ ዘለግ ያለ ቁመት ላላቸው አጥቂዎቹ ኳሶችን በማሻገር ግቦችን ይፈልጋል። በተለይ በመስመር በኩል የሚጣሉ ኳሶችን እንደ ዋነኛ የግብ ማስቆጠሪያ ምንጭነት በመጠቀም የግብ እድሎችን ለመፍጠር ይታትራል። ነገም በተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ ወደ ሜዳ በመግባት ጨዋታውን እንደሚከውን ይጠበቃል።

ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ በርከት ያሉ አማካዮችን በነገው ጨዋታ ሊጠቀም ይችላል። ምክንያቱም ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ ከኳስ ጋር ያለው ግንኙነት በአንፃራዊነት ሻል ያለ ስለሆነ ቡድኑ የኃይል ሚዛኑን ለማመጣጠን ይረዳው ዘንድ አማራጩን ሳያቅማማ ሊጠቀም ይችላል።

ድሬዳዋ ከተማ ባለፈው ያልተጠቀመባቸውን አዲስ ፈራሚዎች በነገው ጨዋታ የሚጠቀም ይሆናል። በዚህም ይስሀቅ መኩሪያ፣ ምንያምር ጴጥሮስ፣ አንዶህ ኩዌኪ እና እንዳለ ከበደ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ የሚጠበቅ ሲሆን ፉይሴኒ ኑሁን ግን ከቡድኑ ጋር እንደማይገኝ ተሰምቷል። በጉዳት ምክንያት ደግሞ ጣቱ ላይ ውልቃት ያጋጠመው ሳምሶን አሰፋን ጨምሮ በረከት ሳሙኤል፣ ያሬድ ታደሰ፣ ረመዳን ናስር፣ ፈርሀን ሰዒድ እና ቢኒያም ጥዑመልሳንን በነገው ጨዋታ አያሰልፍም፡፡ በተጨማሪም በአምስት ቢጫ ካርድ ምክንያት ፍሬድ ሙሸንዲም ወደ ሜዳ እንደማይገባ ተጠቁሟል። በአንፃራዊነት ደግሞ የሙህዲን ሙሳም መሰለፍም አጠራጣሪ ነው ተብሏል።

የፋሲል ከነማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ ተሸነፈ አቻ አሸነፈ አሸነፈ

ወደ ባህር ዳር በመምጣት አዳማን ያሸነፉት እና የሁለተኛ ዙሩን ውድድር በድል የጀመሩት ዐፄዎቹ ጥር 30 የተቀዳጁትን ብቸኛ የዓመቱ የሜዳ ውጪ (መቐለ 70 እንደርታ) ድል ለመድገም እና ሊጉን በአስተማማኝ ደረጃ ለመምራት ድሬ ገብተዋል።

እንደ ሌሎቹ የሊጉ ክለቦች ከሜዳው ውጪ ለማሸነፍ የሚቸገረው ፋሲል በዚህኛው ዙር ይህንን ችግሩን መቅረፍ ይጠበቅበታል። በተለይ ቡድኑ እውነተኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ መዝለቅ የሚሻ ከሆነ ነጥቦችን በሜዳው እና ከሜዳው ውጪ መሰብሰብ ግድ ይለዋል።

ጨዋታዎችን በማፍጠን እና በማቀዝቀዝ የጨዋታውን ሚዛን እንደፈለጉ ሲቆጣጠሩ የሚታዩት ፋሲሎች ነገም ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ የኳስ ቁጥጥር ሂደትም ቡድኑ ኳስን በትዕግስት በማንሸራሸር ግቦችን ያነፈንፋል። በተለይ በሱራፌል ዳኛቸው ቅልጥፍና እና ብቃት ታግዞ የተጋጣሚን የግብ ክልል በተደጋጋሚ ይጎበኛል። በተጨማሪም በመስመር ላይ በሚጫወቱት የቡድኑ የወገብ በላይ ተጨዋቾች ታግዞ የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር ለመዘርዘር እና ክፍተቶችን ለመፍጠር ይታትራል። ከዚህ መነሻነት ቡድኑ የነገውን ጨዋታ በተመሳሳይ አቀራረብ ሊከውን እንደሚችል ይታሰባል።

በተጨማሪም የቡድኑን ብሎም የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሙጂብ ቃሲምን ያነጣጠሩ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን በነገው ጨዋታ ሊያዘወትር ይችላል። በተቃራኒው ግን ቡድኑ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ተጋላጭ ሲሆን ይስተዋላል። በተለይ በተጨዋቾች የተናጥል የመዘናጋት ስህተት ቡድኑ ኪሶችን ለተጋጣሚ ተጨዋቾች ሲለግስ ይስተዋላል። ከዚህ መነሻነት ቡድኑ ነገ ችግሮች ውስጥ እንዳይገባ ያሰጋል።

በፋሲል ከነማ በኩል ምንም የጉዳት ዜና አለመኖሩ ሲረጋገጥ ሽመክት ጉግሳ ግን ቅጣት ላይ በመገኘቱ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆኗል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– በሊጉ እስካሁን ሰባት ጊዜ ተገናኝተዋል። ፋሲል ከነማ ሦስት ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይ ሲሆን አንድ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ አሸንፏል። በቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

– በግንኙነታቸው ፋሲል ከነማ ዘጠኝ፤ ድሬዳዋ ከተማ ሁለት ጎሎች አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)

ፍሬው ጌታሁን

ያሲን ጀማል – ፍሬዘር ካሳ – ያሬድ ዘውድነህ – አማረ በቀለ

እንዳለ ከበደ – ኤልያስ ማሞ – ይስሀቅ መኩርያ – ሄኖክ ኢሳይያስ

ሙህዲን ሙሳ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ

ፋሲል ከነማ (4-2-3-1)

ቴዎድሮስ ጌትነት

እንየው ካሳሁን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባዬ – አምሳሉ ጥላሁን

ጅብሪል አህመድ – ሀብታሙ ተከስተ

ዓ/ብርሀን ይግዛው – በዛብህ መለዮ – ሱራፌል ዳኛቸው

ሙጂብ ቃሲም

©ሶከር ኢትዮጵያ