የዘጠናዎቹ ኮከቦች | ከቺቾሮ… ባሎኒ… እስከ አዲስ አበባ ስታዲየም የዘለቀ የእግር ኳስ ጉዞ (ክፍል ሁለት)

ከቀናት በፊት ከኤፍሬም ዘርዑ ጋር ያደረግነው የመጀመርያ ክፍል ማቅረባችን ይታወሳል አሁን ደግሞ ሁለተኛው እና የመጨረሻው ክፍል ይዘንላችሁ ቀርበናል።

ተጫዋቹ በሜዳ ውስጥ መቶ ብር ስለተሸለመት አጋጣሚ ፣ ከኤርትራ ስለቀረበለት ጥያቄ ፣ ስለ ብሄራዊ ቡድን ቆይታው እና ሌሎች ጉዳዮች ቆይታ አድርጓል።

ስለ ደደቢት ቆይታው እና ውጤታማው ስብስብ

ወደ ደደቢት በ2002 ነው ያመራሁት። በመጀመርያው ዓመት የጥሎ ማለፍ አነሳን፤ በሁለተኛው ዓመትም የአፍሪካ ውድድሮች ላይ ተሳትፈናል። በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ጥሩ ተፎካካሪ ቡድን ነበረን። በ2005 ሊጉን ከማንሳታችን በፊት ዋንጫውን ለማንሳት የተቃረብንባቸው ግዜያት ነበሩ። በተለይም 2003 ብዙ ትግል አድርገን ነው ሁለተኛ ደረጃ ይዘን ያጠናቀቅነው። 2005 ዋንጫው ባነሳንበት ጊዜም በጣም አሪፍ ቡድን ነበረን። ዋንጫው ለማንሳትም ብዙ ፈተና አልገጠመንም። በስብስብ ደረጃ በጣም ውጤታማ ስብስብ ነበረን፤ ሁለት ምርጥ ቡድን የሚወጣው ነበር። ብሔራዊ ቡድኑ ራሱ ከደደቢት እስከ 13 ተጫዋቾች የሚመርጥበት ጊዜ ነበር። በደደቢት የነበረኝ ቆይታ በአጠቃላይ ጥሩ ነበር ፤ አሰልጣኞች ቢቀያየሩም በቡድኑ የነበረው ፍቅር ለቡድኑ ውጤታማነት ትልቅ ድርሻ ነበረው። በክለቡ የነበረው ፍቅር እና መከባበር በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም። በደደቢት የነበረኝ ግዜ በጥቅሉ አሪፍ ነበር።

እግርኳስ መጫወት ለማቆም የወሰነበት ምክንያት

ከዛ ዓመት (2005) በኋላ ወደ አሜሪካ እንደምሄድ ወስኜ ጨርሼ ነበር። ወደ መብራት ኃይል እና ኢትዮጵያ ቡና ሄዶ የመወጫት አጋጣሚዎች ቢኖሩም አልፈለግኩም። ጫማዬን ለመስቀል የወሰንኩበት ዋነኛው ውሳኔ ግን እኔ በእግር ኳስ ውስጥ ከቆየው የሚያድጉ ተጫዋቾች አይኖሩም፤ ቢያንስ በኔ ቦታ አንድ ታዳጊ ቢያድግ ትልቅ ነገር ነው ብዬ በማሰብ ነው። ከዛ በኃላ መጫወት እችል ነበር። ነገር ግን ቅድም እንዳልኩህ እግርኳሱ ወጣቶች ያስፈልጉታል።

ቡድኑ በጣም አሪፍ የወጣቶች ቡድን ስለነበረው ዕድል እንዲሰጣቸው የምንጠይቅባቸው ጊዜያቶችም ነበሩ። ቡድኖችም በተተኪዎች ማመን አለባቸው መሆን የሚገባውም እሱ ነው። ራሴን እየጠበቅኩ እስከ አራት አምስት ዓመት መጫወት እችል። ነበር ግን ትርጉም የለውም ፤ ከኔ መቆየት ይልቅ አንድ ታዳጊ ከታች ቢያድግ ይሻላል። በዛን ወቅትም እንደ ሀይደር ሸረፋ ፣ ምኞት ደበበ፣ ተካልኝ ደጀኔ፣ ሶፎንያስ ሰይፈ፣ ሄኖክ ኢሳይያስ እና ኃይልአብ ኃይለሥላሴ በታዳጊ ቡድኑ ውስጥ ነበሩ። በዛን ወቅት በቡድኑ የነበሩ ታዳጊዎች አሁን ጥሩ ደረጃ ላይ ነው የሚገኙት።

በአጠቃላይ በእግር ኳስ ስለነበረው ቆይታ

በምፈልገው ደረጃ ደርሻለው ብዬ ለመናገር አልደፍርም። ነገር ግን በዛን ሰዓት የስኬት መጨረሻ ብሄራዊ ቡድን መጫወት ነበር። ውጭ ወጥቶ መጫወት በጣም ከባድ ነበር ፤ መንገዶች አልነበሩም። ደስ እያለኝ ነው የተጫወትኩት በርግጥ ማቆም ባለብኝ ሰዓት አይደለም ያቆምኩት። ግን ኳስ ቆይታዬ በጣም ደስተኛ ነበርኩ።

በእግር ኳስ ሕይወቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ክለብ

በሀገሪቱ ትላልቅ ለሚባሉ ክለቦች ነው የተጫወትኩት፤ ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ በእግር ኳስ ሕይወቴ የተጫወትኩበት ትልቁ ክለብ ነው።

ትልቅ ቦታ የሚሰጠው አሰልጣኝ

ያሰለጠኑኝ ትልላቅ አሰልጣኞች ብዙ ናቸው። ሁሉም የየራሳቸው ጥሩ ነገር አላቸው። በብሄራዊ ቡድን ደረጃ እና በክለብ ደረጃ የማውቃቸው አሰልጣኞች ብዙ ናቸው። ከብዙዎቹ ብዙ ነገር ተምሬያለው። እንደ ትላልቅ ወንድሞቼ የማያቸው ገብረመድኅን ኃይሌ እና ፀጋዬ ኪዳነማርያም አሉ። የየራሳቸው ጥሩ አካሄድ አላቸው። ሌላ ደግሞ ሁሌም ለለውጥ የሚተጋ ብዙ ጥሩ ነገር ያየሁበት ውበቱ አባተ አለ። በደምብ የማላቃቸው እና ተማሪ እያለው አስመራ መጥተው ለታዳጊ ብሄራው ምርጫ ለጥቂት ግዜ የማውቃቸው ጋሽ ሐጎስ ደስታ አሉ። በዛን ወቅት በአስራ ስድስት ዓመቴ ያሰሩን ስራ መቼም አልረሳውም። በሳቸው ስር አለመሰልጠኔም ይቆጨኛል።

በኤርትራ ስለቀረበለት ጥያቄ እና ስለ ኢትዮጵያ ታዳጊ ብሄራዊ ቡድን ቆይታው

ጊዜው 1990 ነበር፤ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ። ሙሽር የሚባል ግብፃዊ አሰልጣኝ በዛን ወቅት ለኤርትራ ወጣት ብሄራዊ ቡድን እንድጫወት ጥያቄ አቅርቦልኝ ነበር። አንተ ህፃን ነህ ኤርትራ ኢትዮጵያ አትበል የተሰጠህን ዕድል ተጠቀምበት ይለኝ ነበር። እንደውም ከዛ ግዜ በኃላ ነው ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት እና የብሄራዊ ቡድን ማልያ የመልበስ ፍላጎቱ ያደረብኝ። እና ከኤርትራ ብሄራዊ ቡድን ጥሪ ደርሶኝ ነበር። ከዓመት በኃላም ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ትንሽ ከቆየው በኃላ ጋርዝያቶ ለብሄራዊ ቡድን ጠራኝ። መጀመርያ ላይ ስልሳ ተጫዋቾች ሲመርጥ አልተመረጥኩም ነበር። ከዛ በኃላ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ከመብራት ኃይል እና ባንኮች ስጫወት አይቶኝ በሁለት ጨዋታ ነው የመረጠኝ። ከብሄራዊ ቡድን ጋር ለስድስት ወራት በወጣ ገባ እየተጫወትን ለጨዋታ ወደ ኬንያ ከመሄዳችን በፊት ተጎዳው እና ቀረው። ጉዳቱ ለሦስት እና አራት ዓመታት ከኔ ጋር ቆይቷል። መርፌ እየተወጋው ነበር የተጫወኩት።

ስለ ዋናው ብሄራዊ ቡድን ቆይታው

በዋናው ብሄራዊ ቡድን ብዙ ቆይታ አልነበረኝም። ከዛ ይልቅ ወደ ግሪክ ኦሎምፒክ ለማለፍ ተቃርቦ የነበረው ውጤታማው የኦሎምፒክ ቡድን አባል ነበርኩ። ግሪክ ኤሎምፒክ ለመሄድ ከጫፍ ደርሰን በመጨረሻው ጨዋታ በዩጋንዳ ተሸነፍን። ከዛ ሽንፈት በኃላ መራራ ሀዘን ውስጥ ገብተን ነበር። አሸናፊ ግርማ ፣ ጌቱ ተሾመ ፣ አንዷለም ንጉሴ ፣ ታፈሰ ተስፋዬ ፣ ዳዊት መብራቱ ፣ ሳዳት ጀማል ፣ ዘውዱ በቀለ ፣ ዮናስ ገብረሚካኤል እና ሌሎች በጣም በጣም ብዙ ኮከቦች የነበሩበት ቡድን ነበር።

ሜዳ ውስጥ መቶ ብር ስለተሸለመበት አጋጣሚ እና ሌሎች የማይረሳቸው አጋጣሚዎች

አንድ ቀን ከሐረር ጋር ሐረር ላይ እየተጫወትን መሐል ሜዳ አከባቢ ተከላካዮች ሲቀባቡሉ ነጥቄ ከርቀት ጎል አገባሁ፤ ከዛ የኛ ተቀያሪ ቡድን ቅርብ ርቀት ላይ ነበር። ከነሱ ጋር ደስታዬ እየገለፅኩ ኮለኔል ዐወል አብዱራሂም ከትሪቡን ወርዶ እዛው ሜዳ ውስጥ መቶ ብር ሸለመኝ። ከዛ በኃላ ብሩ እዛው ለአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ሰጠሁት ውበቱም መቶ ብር ጨመሮ መለሰልኝ ። ከነ ህመሜ ገብቼ ግሩም ግብ ያስቆጠርኩበት አጋጣሚ መቼም አልረሳውም።

ከዛ ውጭ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ እያለሁም በጥሎ ማለፍ ከሀዋሳ ጋር ስንጫወት ግሩም ግብ አስቆጥርያለው። በዛን ሰዓት የነበሩ ተጫዋቾች እስካሁን ድረስ ያስታውሷታል፤ የዛኔም በተመሳሳይ አቶ አብነት ገብረመስቀል ልዩ ሽልማት ሸልመውኝ ነበር። በእግር ኳስ ውስጥ የምወደው አጋጣሚም ልክ እንደዚህ ዓይነት ደስ የሚሉ አጋጣሚዎች ናቸው።

ስለ ቀጣይ እቅዱ

የእግር ኳስ ስልጠናዎች እየወሰድኩ ነው ፤ ቀደም ብዬ ጀምሬዋለው። በእቅዴ መሰረት ትምህርቱን እጨርሰዋለው። በኳሱ በቆየሁባቸው ግዜያት ብዙ ትምህርት ወስጃለው አሰልጣኝ መሆን ለኔ ቀላል ነው፤ ተሰጥኦ አለኝ። እሱም ብቻ ሳይሆን በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ዙርያም መስራት እፈልጋለው።

አሁን ስለሚገኝበት ሁኔታ

በአሁኑ ሰዓት በአሜሪካ ነው ያለሁት። ወደ ሀገሬ ተመልሼ መምጣቴ አይቀርም። የጀመርኳቸው ስልጣናዎችም ሌሎች የግል ጉዳዮችም ሲያልቁ ወደ ሀገሬ እመለሳለው። በቅርቡ በሀገር ውስጥም ክለቦች የመያዝ ዕድል አጋጥሞኝ ነበር። ግን ገና ነኝ፤ አንዳንዴ ካለ በቂ ዝግጅት ደፍረህ መግባትም ዋጋ ያስከፍላል። በዛ ምክንያት አልተቀበልኩትም። በአሁኑ ሰዓት በግል ስራ እና ቅድም ያልኩህ ነገሮች እየሰራሁ እገኛለው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ