የመሐል ሜዳ ታጋዩ ገብረኪሮስ አማረ

በዘጠናዎቹ መጀመርያ ከታዩ ኮከቦች አንዱ ነው። በእግር ኳስ ህይወቱ ለወጣት ብሄራዊ ቡድን ፣ መብራት ኃይል ፣ ጉና ንግድ ፣ ድሬዳዋ ባቡር ፣ ወንጂ ስኳር እና በርካታ ዓመታት በአምበልነት ላገለገለው ትራንስ ኢትዮጵያ ተጫውቶ አሳልፏል። በባህሪው ፊትለፊት ተናጋሪ ፣ ቁጡ እና ከረጅም ርቀት አክርሮ በሚያስቆጥራቸው ግሩም ግቦች የሚታወቀው ይህ የቀድሞ ተጫዋች ስለ እግር ኳስ ህይወቱ ፣ ስላጋጠሙት ፈተናዎች እና በድንገት አዳራሽ ውስጥ ጫማውን ለመስቀል ስለወሰነበት አጋጣሚ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

የእግር ኳስ ህይወትህ አጀማመር ምን ይመስል ነበር ?

” እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ኳስን በሰፈር ከጀመርኩ በኃላ ሆስቴል የተባለ የታዳጊ ቡድን ነው የገባሁት። በደንብ በመጫወት በቀጣይነት እግር ኳስ ተጫዋች መሆን አለብኝ ብዬ ማሰብ የጀመርኩት ልክ ሆስቴል ስገባ ነው። በትምህርት ቤት ደረጃም ለተማርኩበት አፄ ዮሐንስ ትምህርት ቤት ብዙ ጨዋታዎች አደርግ ነበር። በዛ ሰዓት በመቐለ ትልቅ ክለብ ለነበረው ዱቄት ለተባለ ቡድን ነው የፈረምኩት ፤ ክለቡን ስቀላቀል ገና ልጅ ነበርኩ። በ1986 የመንግስት ለውጥ ከተደረገ በኃላ ደግሞ ክለቦች በግዚያዊነት ተበትነው ስለነበር ለጥቂት ጊዜ በወረዳዎች ውድድሮች እናደርግ ነበር። ከዛ ሁኔታዎች ሲመቻቹ በአስመላሽ ዓለማየሁ ይመራ ለነበረው ለትግራይ መብራት ኃይል ለአንድ ዓመት ተጫወትኩ። ከአንድ ዓመት ቆይታ በኃላ ደግሞ ለመቐለ 70 እንደርታ (በወቅቱ መቐለ ከነማ ይባል ነበር) ለሦስት ዓመታት ከተጫወትኩ በኃላ ለወጣት ብሄራዊ ቡድን በርካታ ጨዋታዎች አድርጌያለው።”

ለወጣት ብሔራዊ ቡድን እንዴት ተመረጥክ ?

” ጋሽ ሠውነት ቢሻው በሥራ ምክንያት ወደ መቐለ መጥቶ ስጫወት አየኝ፤ በእሱ አማካኝነትም ለወጣት ብሔራዊ ቡድን ተመረጥኩ። ወቅቱ ክረምት ስለነበር ውድድር አልነበረም። ጋሽ ሰውነት እንዲያዩን ጨዋታ ተዘጋጀ ከዛ በኃላ ተመረጥኩ። ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በጣም ስኬታማ ጊዜ ነበረኝ፤ በመጀመርያ ሁለት ጨዋታዎቼ ቡድኑ በኔ ብቸኛ ግቦች ነበር ያሸነፈው። በዚያን ሰዓት አሁን የባህርዳር ከተማ አሰልጣኝ ያሆነው ፋሲል ተካልኝ ፣ አንዋር ትንሹ እና መስፍን ፒስን የመሳሰሉ አቅም ያላቸው ጎበዝ ተጫዋቾች ነበሩ።”

በውጤታማው እና የፕሪምየር ሊጉ አሸናፊ በነበረው መብራት ኃይል ያሳለፍከውን ጊዜስ እንዴት ትገልፀዋለህ ?

” ከመብራት ኃይል ጋር በቃላት መግለፅ የማልችለው ጥሩ ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት። ከተጫዋቾቹ ጋር ለመዋሀድ ጊዜ አልወሰደብኝም። እንደ አንዋር ፣ ኤልያስ ጁሀር እና አፈወርቅ ኪሮስ የመሳሰሉ የወቅቱ ኮከቦችን የያዘ ምርጥ ቡድን ነበር። አሰልጣኛችን ማስተር ሐጎስ ደስታ ለኔ የነበራቸው ስሜት ደግሞ በጣም ደስ የሚል ነበር ፤ ሁሌም ያበረታቱኝ ነበር። ነብሱን ይማረው እና አሰግድ ተስፋዬም የወጣት ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ከነበርኩበት ሰዓት ጀምሮ ሁሌም ይመክረኝ ያበረታታኝ ነበር። በአጠቃላይ በመብራት ኃይል ደስ የሚል ብዙ ትምህርት የወሰድኩበት ቆይታ ነበረኝ። በዚያን ዓመት የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ አንስተናል።”

ታድያ እንዴት ከዚህ ውጤታማ በድን በድንገት ለቀህ ወደ ትራንስ አመራህ ?

“በህይወቴ ከሚፀፅቱኝ ውሳኔዎች አንዱ መብራት ኃይልን ለመልቀቅ መወሰኔ ነው። የዛኔ ገና ወጣት ነበርኩ ፤ ብዙም ነገር አላውቅም። አሳዳጊ ክለቤን ወደ ዋናው ሊግ ማሳደግ አለብኝ ብዬ ነው የህይወቴን ወርቃማ ዕድል ትቼ ወደ ትራንስ የሄድኩት። ሌላው ደግሞ የመብራት ኃይል ደመወዜ ሰባት መቶ ነበር፤ ትራንስ ሀምሳ ብር እንጨምርልሀለን ሲሉኝ ከነበረኝ ስሜት ጋር ተደማምሮ ፈረምኩ። የመብራት ኃይል የክለብ ጓደኞቼን እንኳን በቅጡ ሳልሰናበት ነው ክለቡን የለቀቅኩት። ይህ ውሳኔ በጣም ነው የሚፀፅተኝ ፤ እዛ ብቆይ ኖሮ የእግር ኳስ ህይወቴ ሌላ መልክ ይኖረው ነበር።”

በትራንስም ብዙ አልቆየህም። ከክለቡ ጋር ያሳለፍከው ዓመት እና የመልቀቅህ ምክንያት ምን ነበር ?

” ከውጤታማው የመብራት ኃይል የአንድ ዓመት ቆይታ በኃላ ወደ ትራንስ ኢትዮጵያ ነው የተመለስኩት። ክለቡ ቀድሞ ስጫወትበት የነበረው መቐለ ከነማ ሆኖ ስሙ እና ባለቤትነቱን ወደ ትራንስ ኢትዮጵያ ቀይሮ መወዳደር የጀመረመት ዓመት ነበር። በ1991 በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ አማካኝነት ወደ ትራንስ ከተመለስኩ በኃላ አምበል ሆኜ በግሌ በጣም ጥሩ ዓመት አሳለፍኩ፤ ቡድኑንም ወደ ፕሪምየር ሊግ አሳለፍነው። አዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ ባንኮችን ተከትለን ሦስተኛ ደረጃ ይዘን ነበር ያጠናቀቅነው፤ በግሌም እንደ ቡድንም እጅግ በጣም ጥሩ ውድድር ነበር። ከዚያ ግን በ1992 ሁሉም የቡድኑ አባላት የደመወዝ ዕድገት ሲያገኙ እኔ ስንት ነገር ትቼ ቡድኑን ለማሳደግ የመጣሁት እና በወቅቱ አምበል የነበርኩ ሰው በማላውቀው ምክንያት ተዘለልኩ። ይህን ነገር ተቋቁሜ ዓመቱ ተጀመረ ከትንሽ ወራት በኃላ ግን ከቡድኑ እንድለቅ ተደረገ።”

በቀጣይ የትራንስ የቅርብ ተቃናቃኝ ወደ ሆነው ጉና ያመራበት ሁኔታስ እንዴት ነበር ?

” በዛን ወቅት ሁለቱም ክለቦች እና አሰልጣኞች መካከል ከፍተኛ ውጥረት ነበር። ከትራንስ ጋር የዝውውር መስኮቱ ከተዘጋ በኃላ ነው የተለያየሁት። ሂደቱን ቶሎ ጨርሰውልኝ ወደ ሌላ ክለብ ሄጄ እንዳልጫወት ነገሩን አጓተቱት። ከዛ መስኮቱ ተዘጋና ደመወዝ ብቻ እየተቀበልኩ እስከ ውድድር ዓመቱ አጋማሽ ቆየሁ። በግልፅ እኔን ለመጉዳት የተደረገ ነበር ፤ በዛን ሰዓት ደሞ ብዙ ነገሬን አጥቻለው። በመሆኑም በዓመቱ አጋማሽም ነበር ለጉና ለመጫወት የፈረምኩት። እኔ ትራንስን መልቀቄ ሲሰማ ጉና አናገሩኝ። ለወራት ከቡድኑ ጋር ልምምድ እየሰራው እና ምግብ ከቡድኑ ጋር እየበላው እንድቆይ ተደረገ ፤ ጊዜው ሲደርስም ለጉና መጫወት ጀመርኩ። ከጊዜ በኃላ ግን በጉና ነገሮች ሊመቹኝ አልቻሉም ፤ አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት በቂ የመጫወት ዕድል አይሰጠኝም። ቀድሞው ከትራንስ ለቅቄ ጉና እንድመጣ የተደረገበት ምክንያትም በሁለቱ አሰልጣኞች መካከል ለነበረው ውጥረት ጉናዎች መጠቀምያ ሊያደርጉኝ አስበው መሆኑ ገባኝ። ምክንያቱም በእውነት ፈልገውኝ ቢያስፈርሙኝ ከነብቃቴ አያስቀምጡኝም ነበር። በከተማው ጥሩ ተወዳኝነት ስለነበረኝ በዛ ለመጠቀም እና ለተራ ብሽሽቅ ነበር የፈለጉኝ። ”

ከጉና ከተለያየህ በኃላ ለአንድ ክለብ ለመፈረም ተቃርበህ ሳይሳካ ቀረ፤ ምን ነበር የተፈጠረው ?

” ልክ ጉናን ከለቀቅኩ በኃላ ወደ አየር መንገድ ለመዘዋወር ጨርሼ ገና ከመፈረሜ በፊት ከቡድኑ ጋር ልምምድ ጀመርኩ። ከቀናት በኃላ ግን ሳልጠብቀው ‘አትፈለግም’ ተብዬ ዝውውሩ ከሸፈ። በዚያን ሰዓት ለዝውውሩ ሲረዳኝ የነበረው ነብሱን ይማረው ፀጋይ ኃይሉ በወቅቱ አሰልጣኝ ለነበረው በምን ምክንያት ዝውውሩ እንደከሸፈ ሲጠይቀው ‘ገብረኪሮስ ጠጪ ነው ሰካራም ነው’ አለው። እሱም ‘ ገብረኪሮስ እንኳን ቢራ ኮካ-ኮላ ራሱ አይጠጣም’ አለው። ብዙ ብዙ ነገሮች ነበሩ በዛን ሰዓት ግን የአየር መንገዱ ዝውውር አልተሳካም። ከዛ በኃላ ወደ ወንጂ ስኳር እና ድሬዳዋ ባቡር ነበር ያቀናሁት፤ ሁለቱም ክለቦች ውስጥ በጣም አሪፍ ቆይታ ነበረኝ። ብዙ ጨዋታዎች ተሰልፌ ተጫውቻለው በቆይታዬም ደስተኛ ነበርኩ። በተለይ በባቡር ከነጋምብሬ እና አሻጋሬ ጋር አሪፍ ቆይታ ነበረን። ከዚያ ግን ወባ ይዞኝ በጣም ታመምኩ እና ሳልፈልግ ባቡርን ለቅቄ ወደ ትራንስ ተመለስኩ።”

ስለመጨረሻው የትራንስ ቆይታህ እና ጫማ ስለሰቀልክበት አጋጣሚ አጫውተን…

” የትራንስ የመጨረሻ ዓመታት ቆይታዬ በጣም የበሰልኩበት እና ቡድን የመምራት አቅሜን ያዳበርኩበት ጊዜ ነበር። ግን በመጨረሻ ሰዓት በነበረው የክለቡ ሁኔታ ደስተኛ አልነበርኩም። በዛ ምክንያትም ከዋና አሰልጣኙ ጋር መስማማት አልቻልኩም። መጥፎ ነገር ካየው ዝም ብዬ ማለፍ አልችልም። ‘ቡድኑ አቅም ያለው ሁለተኛ ቡድን እያለው ለምን ወደ ግዢ ይገባል?’ ስል ውግዘት ይደርስብኝ ነበር። ከዛም ‘ገብረኪሮስ ሊያሰራኝ አልቻለም’ የሚል ክስ ቀረበብኝ እና የክለቡ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ር ገብረመስቀል በክለቡ ዙርያ አጠቃላይ ስብሰባ አደረጉልን። በዶክተር አግባቢነትም በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በድንገት ከክለቡ ተጫዋችነት ወደ ሁለተኛው ቡድን መሪነት ተሸጋገርኩ። ዶክተርን ጨምሮ ሙሉ የክለቡ አባል ከጎኔ ነበር ፤ ቡድኑ የራሴ እንደሆነ እና ለጊዜው ወደ ሁለተኛ ቡድን ወርጄ እንድሰራ እና ቀጣይ ዓመት የዋናው ቡድን ምክትል አሰልጣኝ እንደምሆን በበላይ አካሎች ተነግሮኝ በድንገት ከተጫዋችነት ወደ ቡድን መሪነት ወረድኩ ፤ ደሞወዜ ሳይቀነስ። ይህ ሁሉ የሆነው ችግሮችን ፊት ለፊት ስለምጋፈጥ እና መብቴን ለማስከበር ወደ ኃላ ስለማልል ነው። በዚህ መልኩ በድንገት ከእግር ኳስ ጫማዬን ሰቀልኩ። በቀጣይ ዓመት ክለቡ አሰልጣኝ ቀየረ ፤ ቃል በተገባልኝ መሰረት ምክትልም አልሆንኩም። ይባስ ብሎ ከደመወዜ ከግማሽ በላይ ቀንሼ እንድሰራ ተጠየቅኩ። መጫወት እየቻልኩ ጫማዬን መስቀሌ አሁንም ድረስ ይቆጨኛል ፤ አቅሙ ነበረኝ። ከኔ ጋር በወጣት ብሄራዊ ቡድን እና መብራት ኃይል የተጫወቱ እስከ ቅርብ ዓመት ተጫውተዋል። የእግር ኳስ ህይወቴን ‘ያድማል’ እየተባልኩ ነው ያሳለፍኩት። ይሄ ነገር እስካሁን ድረስ መኖሩ ደግሞ በጣም ያናድደኛል። ብቃቱ እያላቸው የባከኑ በጣም ብዙ ወጣቶች አሉ። አብዛኛው የእግር ኳስ ህይወቴን አምበል ነበርኩ። ስለዚህ ስለተጫዋቾች እና ስለ ክለቡ ነገሮች በቅርበት ማወቅ አለብኝ። ትክክል ያልሆነ ነገር አይቼ ዝም አልልም ፤ ከብዙዎቹ የሚያጣላኝም ይሄ ነበር።”

የአሰልጣኝነት ህይወትህ እንዴት ነበር ?

” ማሰልጠን የጀመርኩት በ1999 መጨረሻ የትራንስን ሦስተኛ ቡድን በመያዝ ነበር። በመቀጠል በ2000 በእነጋዜጠኛ ዳንኤል አስመላሽ ጥረት ድጋሜ በተመሰረተው መቐለ ከነማ በምክትልነት ለብዙ ዓመታት ሰራው። ከዚያም በኃላ በራያ አዘቦ በዋና አሰልጣኝነት ሰርቻለው። በሁለቱም ቡድኖች በጣም ብዙ ስራዎች ሰርቻለው። በመቀጠል ወደ ስሑል ሽረ አምርቼ ወደ ከፍተኛ ሊጉ አሳድጌዋለው ፤ በጣም በትንሽ በጀት ነው ቡድኑን ያሳደግነው። በትግራይ ውሀ ስራዎች ሰርቻለው ቀጥዬም በድጋሜ ወደ ሽረ ተመልሼ በቴክኒካል ዳይሬክተርነት አገልግያለው። ከዚያም የሳምሶን አየለ ምክትል ሆኜ ሰርቻለው። በሁለተኛው ዙርም ከአንገቱ በታች ሰምጦ የነበረውን ቡድን እንደ አዲስ ገንብተን ጥሩ ተፎካካሪ አድርገን ከመላው ቡድን ጋር ተባብረን አትርፈነዋል። በህይወቴ ከምያስደስቱኝ ነገሮች አንዱ በዛን ወቅት በጋራ የሰራነው ሥራ ነው።”

አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለህ ?

“በዚህ ሰዓት በመቐለ 70 እንደርታ እየሰራው እገኛለው። የቴክኒክ ዳይሬክተር ቦታ ላይ ከሌሎች ባልደረቦቼ ጋር በመሆን በታዳጊዎች ላይ እየሰራን ነው። በቀጣይም ከእግዚአብሔር ጋር ክለቡን አንድ ደረጃ ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ነገሮችን ለመስራት ዕቅድ አለን።”

በእግር ኳስ ህይወትህ የማልዘነጋቸው የምትላቸው አጋጣሚዎች ?

” በጣም ብዙ አይረሴ አጋጣሚዎችን አሳልፍያለው። ከነዚህ ውስጥ በመከላከያ ላይ ያስቆጠርኳት የመጀመርያ ግቤ ፣ በወጣት ቡድን ያሳለፍኩት ጊዜ እና ከመብራት ኃይል ጋር ያነሳሁት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ በህይወቴ የማይረሱ አጋጣሚዎች ናቸው። በአሰልጣኝነት ህይወቴ ደግሞ በስሑል ሽረ በሁለት አጋጣሚዎች የነበረኝን ቆይታ አልረሳውም። ”

ከተጨዋቾች እና አሰልጣኞች የነማን አድናቂ ነህ ?

” በዘጠናዎቹ ከነበሩት አሰግድ ተስፋዬ ፣ አንዋር ትልቁ ፣ ኤልያስ ጁዋር ፣ አሸናፊ ግርማ እና አፈወርቅ ኪሮስን አደንቅ ነበር። በወቅቱ የሊጉ ክስተት ነበሩ ፤ በግሌም በጣም አደንቃቸው ነበር። ከአሁኑ ትውልድ ደግሞ አስቻለው ታመነ ፣ ያሬድ ከበደ ፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ኃይልአብ ኃይለስላሴን አደንቃለው። አስቻለው ፣ አማኑኤል እና ያሬድ በየክለቦቻቸው ወሳኝ ተጫዋቾች ናቸው ፤ ኃይልአብ ደግሞ በሀገሪቱ በግል ብቃት ደረጃ እምቅ ብቃት ያለው ግን ያልተጠቀምንበት ተጫዋች ነው። ከአሰልጣኞች ደግሞ ማስተር ሐጎስ ደስታ እና ጋሽ ሰውነት ቢሻውን አደንቃለው በእግር ኳስ ህይወቴ ትልቅ ቦታ አላቸው። ማስተር ሐጎስ ደስታ በመብራት ኃይል ቆይታዬ ብዙ ነገር አስተምሮኛል። ጋሽ ሰውነት ደግሞ ለወጣት ብሄራዊ ቡድን ያስመረጠኝ እሱ ነው። ከዛ ውጪ ደግሞ አብርሀም መብራቱን በጣም አደንቀዋለው።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ