የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የተጫዋቾች የደመወዝ ክፍያን በተመለከተ ለክለቦች መመሪያ ሰጠ

(መረጃው የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ነው)

ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኮሮና ቫይረስ በዓለም ብሎም በሀገራችን ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ውድድሮች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጡ እንዲሁም ሀገራችን ላይ እየደረሰ ያለው የወረርሽኝ መጠን እየጨመረ መምጣቱ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ በመሆናችን በቀጣይ የሚደረጉ ውድድሮች መሰረዛችን ይታወቃል፡፡

ፊፋ ሚያዚያ 07/2020 በሰርኩላር ቁጥር 1714 ኮቪድ 19 ባቀረበው ምከረ ሀሳብ  ክለቦች እና ተጨዋቾች የኮቪድ 19 አለም አቀፍ ወረርሽኝ ለሁሉም የሰው ዘሮች የመጣ በመሆኑ ከኮንትራት ማስጠበቅ እና ኮንትራትን በስምምነት ከመቀነስ ጋር በተገናኘ ክለቦች እና ተጫዋቾች እግር ኳስ ሰብዓዊነትን የሚያበረታታ በመሆኑ ባጋራ በመመካከር ይህንን ክፉ ጊዜ እንዲወጡት ምክረ ሀሳብ አቅቧል፡፡ በሀገራችን የሚገኙ ጥቂት ክለቦችም ይህንን የፊፋ ምክረ ሀሳብ በመቀበል ተግባራዊ በማድረጋቸው የመጣውን ችግር በጋራ በመፍታት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ ክለቦች የኮቪድ 19 ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ደመወዝ አለመክፈል እንዲሁም  በዲሲፒሊን እና ይግባኝ ሰሚ የተወሰነባቸውን ወሳኔ ተግባራዊ እያደረጉ አለመሆኑን ከሚመጡልን አቤቱታዎች ተረድተናል፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፒሊን መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 80/1/ መሰረት ክለቦች የተጫዋቾችን፤ የአሰልጣኞች እና የህክምና ባለሙያዎችን መብት በውላቸው መሰረት እንዲያሟሉ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክለቦች ያልከፈሉትን ደመወዝ ኮንትራታቸውን በማክበር ወይም ከተጫዋቾች ጋር በመወያየት የደመወዝ እና በዲሲፒሊን የተወሰነላቸውን ክፍያ እሰከ ሐምሌ 5/2012ዓ.ም በመክፈል ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሪፖርት እንዲያደርጉ እያሳሰብን፤ ይህ ተግባራዊ ሳይሆን ቢቀር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቀጣይ እርምጃ ክለቡ ላይ እንደሚወስድ ያሳውቃል ፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ