ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቢጂአይ ኢትዮጵያ ጋር የአጋነርት ስምምነትን ፈፀመ

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር በዛሬው ዕለት ከቢጂአይ ኢትዮጵያ ጋር የአጋርነት ስምምነትን በሸራተን አዲስ ሆቴል ተፈራርሟል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ አንጋፋ ከሚባሉ ክለቦች መካከል ቀዳማዊውን ቦታ የሚይዘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ በተለያዩ ጊዜያት ከድርጅቶች እና ተቋማት ጋር ራሱን በገቢ ደረጃ ለማጠናከር የአጋርነት ስምምነቶች በተለያዩ ወቅቶች ሲፈፀም የተስተዋለ ሲሆን በዛሬው ዕለት ግን የፈፀመው እስከዛሬ ካደረጋቸው ትልቁ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በዚህም ዛሬ በሸራተን አዲስ ሆቴል የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከቢጂአይ ኢትዮጵያ ጋር ለአምስት ዓመታትን የሚቆይ የስፖንሰርሺፕ ስምምነትን ፈፅሟል፡፡ በፊርማ ስነ-ሥርዓቱ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር የቦርድ ሊቀ-መንበር አቶ አብነት ገብረመስቀል ክለቡን በመወከል እንዲሁም ደግሞ የቢጂአይ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ኃላፊ ሚስተር ሎውረንስ ሎኩዬ ድርጅቱን በመወከል ሁነቱን ፈፅመዋል፡፡

የፈረሰኞቹ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና የክለቡ አመራሮች በተገኙበት ሥነ-ስርዓት ጋዜጠኞች ጥያቄ በመሰንዘር ምላሽ የተሰጠ ሲሆን ስምምነቱ የቅዱስ ጊዮርጊስን የመለማመጃ ሜዳ ግንባታ ማፋጠን፣ የክለቡን የፋይናንስ አቅም ማጠናከር፣ ክለቡ በደንብ በአክሲዮን እንዲደረጅ ማድረግ ላይ ትኩረት የሚያደርግ መሆኑም በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡ ቢጂአይ ኢትዮጵያ በቀጣይም የመለያ ስፖንሰር ለመሆን ማቀዱም ተነግሯል፡፡

ቢጂአይ ኢትዮጵያ በተለይም በቅዱስ ጊዮርጊስ ምርቱ ለረጅም ዓመታት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ጋር በአጋርነት ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል።

ከክለቡ ጋር በተያያዘ በዘንድሮው ዓመት ውላቸውን ያጠናቀቁ ተጫዋቾችን ውል ለማራዘም ከተጫዋቾቹ ጋር ንግግር መጀመሩን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ