የዳኞች ገፅ | በኢትዮጵያ ዳኝነትን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሻገረው ኃይለመልዓክ ተሰማ

በኢትዮጵያ የዳኞች ታሪክ ውስጥ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር መልካም ሥም ካተረፉ ምስጉን ዳኞች መካከልና በዓለም አቀፍ መድረክ የሀገሩን ስም ከፍ ማድረግ የቻለው የቀድሞ ኢንተርናሽናል ዳኛ የወቅቱ የጨዋታ ታዛቢ ኃይለመልዓክ የዛሬው የዳኞች ገፅ እንግዳችን ነው።

በዳኝነቱ ዘመን ብዙ ትልልቅ ጨዋታዎችን በብቃት ዳኝቷል። ከመምሪያ ሁለት የጀመረው የዳኝነት ጉዞው እስከ ኢንተርናሽናል ዳኝነት አድርሶት ለሃያ ሰባት ዓመት አገልጓሏል። በርከት ያሉ የምስጉድ ዳኝነት ሽልማት በሀገር ውስጥ ያገኘው ኃይለመልዓክ በሦስት ተከታታይ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ በመሳተፍ የኢትዮጵያ ዳኝነትን ወደ አዲስ ምዕራፍ አሻግሯል። የካፍ ኮፌዴሬሽን ዋንጫ ሁለት የፍፃሜ ጨዋታዎች አጫውቷል። ለቁጥር የበዙ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎችን በለተያዩ ሀገራት በመዞር ሰርቷል። የሴካፋ ዋንጫ፣ የአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ፣ የኦሊምፒክ ማጣርያ ጨዋታዎችን ከዳኛባቸው ውድድሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። የፊፋ የዓለም ወጣቶች ዋንጫን (አርጀንቲና ላይ) እና የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ውድድሮችን በብቃት ዳኝቶ ተመልሷል። በአሁኑ ወቅት የጨዋታ ኮሚሽነር እና የኢትዮጵያ ዳኞች ኮሚቴ አባል በመሆን ለአስራ ሁለት ዓመታት እየሰራ ይገኛል። የመልካም ስብዕና ባለቤት የሆነው የኃይለመልዓክ በዳኝነት ሃያ ሰባት ዓመት በጨዋታ ታዛቢነት አስራ ሁለት ዓመት በድምሩ ለሠላሳ ስምንት ዓመት ሀገሩን አገልግሏል፣ እያገለገለም ይገኛል። የዚህ ሁሉ ዓመት የዳኝነት ጉዞውን አስመልክቶ በዛሬው የዳኞች ገፃችን እንግዳ አድርገነዋል። መልካም ቆይታ!

ትውልድ እና እድገትህ እንዴት ነው? ከእርሱ ልጀምር

አዲስ አበባ ቦሌ ቡልቡላ ተወልጄ የአስር ቀን ልጅ ስሆን ወደ ለገሀር አካባቢ በመምጣት ነው ያደግኩት። እንደሚታወቀው ለገሀር በርካታ ምርጥ ተጫዋቾችን እና ዳኞችን ያፈራ ሰፈር ነው።

መቼም ለገሀር ምርጥ ዳኞችን እንዳፈራ እየነገርከኝ ነው። ስለዚህ ዳኛ እንድትሆን ለገሀር አስተዋፅኦ አድርጓል ማለት ይቻላል ?

በትክክል! ብዙ በጣም ስመጥር የነበሩ ዳኞች ነበሩ። ለምሳሌ አባ ኃይለማርያም፣ ለገሠ ብዙ ዳኞችን አሁን በስም ያልጠቀስኳቸው ጭምር የወጡበት ሠፈር በመሆኑ እነርሱን እያየው ነው ወደ ዳኝነቱ የገባሁት።

የመጀመርያውን የዳኝነት ኮርስ መቼ ወሰድክ ?

ያኔ በቀድሞ አጠራር ሸዋ ስፖርት ፅህፈት ቤት የአሁኑ የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን በቀጥታ እዛ ሄጄ ተመዘገብኩኝየ። ስልጠናውን በሚገባ ተከታትዬ ጠዋት ጃልሜዳ የ ሲ ” ቡድን ጨዋታን አጫውቼ ከሰዓት ደግሞ ቀበሌ 10 ላይ በማጫወት በ1972 የመጀመርያውን የመዳኘት ስራዬን ጀመርኩ። እንዲህ እንዲህ እያለ ፍቅሩ እየጨመረ መጣ። ያው በፎቶ ላይ እንዳየኸው ድሮ የምናጫውተው ከላይ ጥቁር መለያ አድርገን ከስር ቱታ ለብሰን ነበር።

አንድ ብለህ በሲ ቡድን ጨዋታ በመምራት የጀመረው የዳኝነት ህይወትህ ቀጣይ ጉዞህ ምን ይመስላል።

እንግዲህ ቅድም እንዳልኩሁ በ1972 የጀመርኩት ዳኝነት የ “ሲ” ቡድን የቀበሌ ጨዋታዎችን ለብዙ ዓመት እየሰራው እንዲሁም የኢሴማ ውድድሮችን እያጫወትኩ ልምዶችን ካገኘው በኃላ በ1980 ላይ ከስምንት ዓመት በኃላ ማለት ነው። ፌደራል ዳኝነትን አግኝቼ በዲቪዚዮን ደረጃ በኢትዮጵያ ሻምፒዮን ጨዋታዎችን መምራት ጀምርያለው። የሚገርምህ በዳኝነት ዘመኔ የመጀመርያውን ትልቅ ጨዋታ ያጫወትኩት በጣም አስታውሰዋለው በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ቃጫ ከሚባል የሠራተኛ ቡድን ጋር ያደረገውን ጨዋታ ነበር። በወቅቱም ጨዋታው አንድ ለአንድ በማለቁ በሀገሪቱ የሬዲዮ ሚዲያዎች አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጨምሮ በትልቁ ቮልድ ተደርጎ ቃጫ ነጥብ አስጣለ ተብሎ ሲዘገብ አስታውሳለው። ጊዮርጊስ ትልቅ ቡድን ነው ቃጫ ደግሞ አነስተኛ ግምት የተሰጠው የሠራተኛ ቡድን ስለሆነ ጊዮርጊስን ነጥብ ማስጣሉ በጣም አስገራሚ በመሆኑ ነው። ይህን ጨዋታ ነው መጀመርያ በትልቅ ጨዋታ የተመደብኩት።

በፌደራል ዳኝነቱ ብዙም ሳትቆይ ኢንተርናሽናል ዳኛ የሆንከው?

አዎ በፌደራል ዳኝነት ለሦስት ዓመት ከቆየው በኋላ በ1984 ከመንግስት ለውጥ በኃላ በረዳት ዳኝነት ኢንተርናሽናል ሆኛለው። በቀደመው ዘመን አንዴ መሐል አንዴ ረዳት እየሆንን ነበር የምናጫውተው። በአዲስ አበባ ስታዲየም ከሀምሳዎቹ ክለቦች እስከ 1980 ድረስ ረዳት ዳኛ ሆኜ ነበር የምሰራው። በ1984 ሚናችሁን ለዩ ሲባል ለሁለት ዓመት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሆኜ አገልግያለው። ከዛ በመቀጠል ነው ወደ መሐል ዳኝነቱ ልገባ የቻልኩት

ታዲያ እንዴት ወደ መሐል ዳኝነቱ ልትገባ ቻልክ?

በጊዜው ከፊት ያሉ (እኔን የሚቀድሙ ዳኞች ማለቴ ነው) በእድሜ እየገፋ ዳኝነቱን ለማቆም እያሰቡ ሲመጡ፣ እንዲሁም ፊፋ የዳኛ እድሜ ከአርባ አምስት እንዳይበልጥ ወስኖ ስለነበር የአብዛኛዎቹም እድሜ ወደ እዛ እየቀረበ ሲመጣ ሳየው ተተኪ እንደሌላቸው ሳውቅ ፍላጎቴ ወደ መሐል ዳኝነት ተሳበ። በወቅቱ ደግሞ ወደ መሐል ዳኝነት ለመግባት አንድ ዓመት በሀገርህ ውስጥ በመስራት አለብህ ስለተባለ ለአንድ ዓመት በመሐል ዳኝነት ካጫወትኩ በኃላ የተሰጠውን ፈተና ወስጄ ኢንተርናሽናል የመሐል ዳኛ ሆንኩኝ።

በወቅቱ በኢትዮጵያ በዳኞች መካከል የተለያዩ ውዝግቦች ተፈጥረው እስከመታገድ የደረስንበት ምክንያት ምንድነው?

የተወሰኑ ዳኞች ወደ ፊፋ የተላካው የኢንተርናሽናል ዳኞች ስም ዝርዝር ትክክል አይደለም። ኢንተርናሽናል ዳኝነት ያሟሉ እና ያላሟሉ አሉ በሚል ፌዴሬሽኑ ክስ ከሰሱ። ዓለሙ አበበ፣ ዓለም ነፃብህ እና ሌሎች አሁን ልብ ያላልኳቸው ፌዴሬሽን በመሄድ ከሰሱ፤ በዚህ ጊዜ ጉዳዩ ፊፋ ጋር ደርሶ አስተካክሉ አለ፣ ፌዴሬሽኑ ደግሞ ትክክል ነው የላኩት ስም ዝርዝር አላስተካክልም የሚል አቋሙን አሳወቀ። በዚህ ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት ፊፋ ኢትዮጵያን ዳኞችን ለአንድ ዓመት ከማንኛውም ከኢንተርናሽናል ዳኝነት ሰርዟል። ከአንድ ዓመት በኋላ ፊፋ በድጋሚ የሰረዘውን አንስቷል።

በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገር ብዙ ጨዋታዎችን አጫውተሀል። በተወሰነ መልኩ መነሳት ያለባቸውን አንሳልኝ

ኡ! ብዘረዝረው ሁለት ቀን ይፈጃል፤ በጣም በርካታ ከመሆኑ አንፃር። ነገር ግን በዋናነት እኔ በጣም ደስ የሚለኝ ሦስት የካፍ ኮፌዴሬሽን የፍፃሜ ጨዋታን አይቮሪኮስት፣ ቱኒዚያ እና ናይጄሪያ ላይ አጫውቻለው። እንዲሁም ጋና ላይ በተካሄደው የወጣቶች የአፍሪካ ዋንጫ ሄጄ ጨዋታዎችን እንዲሁም ያልጠበኩትን የደረጃ ጨዋታን በማጫወቴ በጣም የተደሰትኩበት ነው። ኢትዮጵያ ላይ የተዘጋጀውን የአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫን በመቀጠል ወደ አርጀንቲና በመሄድ የዓለም ወጣቶች ዋንጫን አጫውቻለው። በአፍሪካ ዋንጫ በተከታታይ ለሦስት ጊዜ በአውሮፕያውያን አቆጣጠር ከ2000–04 ድረስ ጋና እና ካሜሮን በጥምረት ያዘጋጁትን፣ ማሊ እንዲሁም ቱኒዚያ የተካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫን ሀገሬን በመወከል ሠርቻለው። ሌላው የዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች፣ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያዎች ከብዙ በጥቂቱ ሠርቻለው። በዚህ ሁሉ ዳኝነት ዘመኔ ያልተንኳኳ በር የለም። በተለይ የሰሜን እና የደቡብ አፍሪካ ሀገሮች ማጫወት አይቻልም። ምክንያቱም በገንዘብ ሊገዙህ ይፈልጋሉ። ይህንን አሳፋሪ ነገር በመቃወም በንፁሁ ህሊና ባስቸጋሪ ነገሮች አልፌ በጥሩ ስም እና ምስጋና ተመልሻለው።

የነገርከኝ ስኬቶች ቀላል አይደሉም፤ የተለያዩ ውድድሮችን በብቃት አጫውተሀል። ሆኖም የዓለም ዋንጨ አለመመረጥህ የሚፈጥርብህ ነገር አለ?

ምንም የሚሰማኝ የለም። ምክንያቱም ፊፋ ያወጣው የዕድሜ ጣርያ በማለፉ እንጂ በ2006 ጀርመን ላይ እሄድ ነበር። ይህም በመሆኑ ብዙም የሚፈጥርብኝ ነገር የለም። ከእኔ በፊት የነበሩትም ይሄን አላሳኩም። ተስፋዬ ነበር እርሱም ኤርትራዊ ሆነ። የአቴንስ ኦሊምፒክም የመሔድ ዕድሌ ሠፊ ነበር። በተመሳሳይ ፊፋ ያስቀመጠው የዕድሜ ጣርያ እንዳልሔድ አድርጎኛል። ከኔ በኃላ ነው አሁን በዓምላክ ያሳካው።

ዳኝነትን መቼ አቆምክ? የመጨረሻ ጨዋታህ ማንን ከማን አጫወትክ ነው?

በበ1998 ዳኝነትን አቁሜለው የመጨረሻ ያጫወትኩትን ጨዋታ በሀገር ውስጥ አላስታውሰውም። ግን ከሀገር ውጭ ሱዳን ላይ በኢንተርናሽናል መድረክ የመጨረሻዬን ጨዋታ ማጫወቴን አስታውሳለው። ከዳኝነቱ በኃላ በአንድ ምክንያት ለሁለት ዓመት ያህል ካልሆነ በቀር ለአስር ዓመት እስካሁን ድረስ በኮሚሽነርነት እያገለገልኩኝ እገኛለው። በዳኞች ኮሚቴ እየሰራው እገኛለው።

ቅድም በተወሰነ መልኩ ነካክተህ አልፈህዋል። በሰሜን አፍሪካ ለመዳኘት በሚኬድበት ወቅት የተለያዩ ማማለያዎች ይቀርባሉ ይባላል። አንተ በዚህ መልኩ ያጋጠሙህ ችግሮች ነበሩ ?

በጣም እንጂ! እንኳን በትልልቅ ውድድሮች አይደለም እዚህ ግባ በማይባለው የሴካፋ ዋንጫ ሁሉ ሳይቀር ይህ ዳኞችን በገንዘብ ለመግዛት የሚደረገው ሩጫ የተለመደ ነው። በዚህ መልኩ እኛ ኢትዮጵያውያን ከዚህ በፊትም አሁንም የሀገራችንን መልካም ስም ጠብቀን ለመመለስ ችለናል። ሆኖም በእኔ ዘመን አፍሪካ ውስጥ አንዳንድ የሚልከሰከሱ ዳኞችም ነበሩ፤ በዚህም ሁለት ዓመት የተቀጡ አሉ። በኛ ጊዜ ሆቴል ክፍላችን ድረስ በመምጣት የማይንኳኳ በር የለም። በተለይ የሰሜን እና ደቡብ አፍሪካ ቡድኖች (ሀገሮች) በዚህ ይታወቃሉ። ካፍ እና ሴካፋ ያሉ ሰዎች በሚገባ ያውቁኛል። አልቀበልም፤ አላውቅም እያልኩ መመለሴን። በዚህ በጎ ስራዬ በተለያየ ካፍ፣ ሴካፋ ውስጥ ካሉ ሰዎች የምስጋና ደብዳቤ ተልኮልኛል። በዚህ በኩል በዓምላክ በደንብ ነው ምክሬን የሰማው፤ በደንብ መክሬዋለው፤ ለዚህም ነው ትልቅ ስኬት ላይ የደረሰው ።

በዳኝነት ዘመንህ ለስኬቴ የምትለው ምንድነው ?

ለኔ ስኬት ከጓደኞቼ ጋር በህብረት ያለ ልዩነት አብሬ በሰራኋቸው ውድድሮች በብቃት መዳኘት፣ አስፈላጊውን ልምምድ ሳላቋርጥ መስራቴ ለኔ ትልቅ ስኬት ነው። እንዳውም በተለያዩ የስብሰባ መድረኮች ምሳሌ የሚያደርጉት እኔን ነው። በሄድኩባቸው ውድድሮች ሁሉ በተፈተንኳቸው ፈተናዎች ሁሉ አንደኝነትን አግኝቼ ነው የምመለሰው። ምሳሌ ሲሉ ከኢትዮጵያ እኔን በተደጋጋሚ መጥራታቸው ለኔ ስኬት ነው። በአጠቃላይ ለረዥም ለዓመታት እራሴን ጠብቄ በብቃት መስራቴ ትልቁ ስኬት ነው።

ካጫወትካቸው ጨዋታዎች ሁሉ የተደሰትክበት ጨዋታ የቱ ነው ?

በጣም በህይወቴ ሁሌም የማረሳው ጨዋታ የ1987 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ንግድ ባንክ ጋር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሻምፒዮን የፍፃሜ ጨዋታ ነው። እጅግ የምደሰትበት አስገራሚ ፉክክርር የተደረገበት ለእኔ ምርጡ ጨዋታ ነው።

በዳኝነት ዘመንህ ያገኛሀቸው የኮከብነት ክብሮች?

ብዙ ክብርን አግኝቻለው። በአዲስ አበባ ደረጃ ሁለቴ በኢትዮጵያ ደግሞ ሦስቴ አግኝቻለው። በጣም የማረሳው በአንድ ወቅት ነፍሱን ይማረው ዳኛ ተድላ ተሰማ (በህይወት የለም) በታሪክ ይሄ የለም፤ አልሰማውም። በነበረን የችሎታ መቀራረብ ተነሳ ሁለታችን እኩል ኮከብ ዳኛ ብለው ሸለሙን። ይሄን ጊዜ አምባሳደር ቶፊቅ ላጥ አድርገው በግላቸው በኔ ተደስተው የሸለሙኝ እንዱሁም አቶ ፀሀዬ ገ/እግዚአብሔር (የቀድሞ የዳኞች ከሚቴ ሰብሳቢ የነበሩ) እንዲሁም ኢንጅነር ግዛውን በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እፈልጋለው።

አዝናኝ ፈገግ የሚያሰኙ ገጠመኞች አሉህ ?

በጣም ብዙ ነው። አንድ ወቅት የመኢሰማ ጨዋታ እያጫወትኩ ወደ መጨረሻው ደቂቃ ምን ሁኔታ እንደተፈጠረ አላውቅም። ረዳት ዳኛውም አይቶታል፤ እኔም አይቼው በጠፋው ጥፋት ቅጣት ምት ሰጠሁ። ያን ኳስ ተቀባበለውት ጎል ያስቆጥራሉ። ጨዋታውን ላስጀምር ስል ከየት መጣ ሳንል ብቻ ከኋላዬ ድው የሚል ድምፅ ሰማሁ፤ አዙሮኝ ብዥ ብሎብኝ ወደቅኹ። በምን እንደመታኝ አላውቅም፤ ደምም የለውም። ብድግ ብዬ ዞር ስል ተጫዋቾች ልጁን ያዙት እኔ ደግሞ ጉርምስና አለ፣ ህልህ ያዘኝ ፣ ካልደበደብኩ፣ ካልገደልኩ ብዬ ተለምኜ ለማስታረቅ ሞከሩ እንቢ አልኩ ጨዋታውን አላጫውትም ብዬ ጥዬ ወጣሁ። በወቅቱ በጣም ነው የተናደድኩት። ዳኝነትን የምተው ቢሆን ኖሮ የዛን ጊዜ ነበር የማቆመው። ያን ልጅ ፍለጋ ቤቱ አማኑኤል አካባቢ ነው ተብዬ ሰፈሩ ሄድኩኝ። እስቲ ይታይህ የአማኑኤል ወጣት ሄጄ ልደበድብ። ይሄን አጋጣሚ መቼም አልረሳውም።

ሌላው ውጭ ሀገር ደግሞ ስም መጠቀስ ባልፈልግም አንዳንድ ዳኞች አንዱ በህይወት የለም፤ አንዱ አለ የውሃ ዋና ሳይችሉ እንችላለን ብለው ዘለው ገብተው እዛው ሞተው ሊቀሩ ሲሉ ልዑልሰገድ በጋሻው ዘሎ ገብቶ አዳናቸው እንጂ ልንዳኝ ሄደን ሬሳ ይዘን ልንመጣ ነበር። ሌላው ለዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ እኔ ፍሬሽ ነበርኩ ማዳጋስካር ሄደን መኮንን አስረስ ፓስታ ነው ብሎ ብላ ይለኛል። እኔም ምንደሆነ አላቅም ፓስታ መስሎኝ አንዴ ጎርሼ የማይሆን ስሜት ሲሰማኝ የምበላበትን ሳህን ገሸሽ ሳደርገው አይተው የሳቁብኝ አጋጣሚ አረሳውም። ብቻ በዛን ዘመን ብዙ የስልጣኔ መገለጫ ቴክሎኖጂዎች የመጡበት ወቅት በመሆኑ ከሀገር ስንወጥ ብዙ ገጠመኞች አሉ። አንዲሁ ለዓለም ዋንጫ ሄደን አንዱን ዳኛ ከሞት ያተረፍንበት አጋጣሚ አለ ስሙን ልደብቅ ነበር። አልደብቅም ብዙዎች ቦቸራ በሚለው ሰሙ ነው የሚያቁት ሞሮኮ ራባት ለትራንዚት ቆመናል ወደ ሌላ ሀገር ለመሄድ ዝም ብሎ እያነሳ ያገኘውን ያጋብሳል (ይበላል) “ይሄ ምድነው ይበላል?” ሲለኝ እኔም ብላ እለዋለው እርሱም ይሄንንም ያንንም ይበላል። ትንሽ ቆይቶ ያ ጥቁር መልኩ ምን ልበልህ ተለብልቦ ቢጫ ሆኖ መልኩ ተለወጠ እኔ እስቃለው እድሜ ለሻለቃ በልሁ እርሱ ነው አንከብክቦት ሆስፒታል ወስዶት የዳነው። በዚህ ምክንያት አውሮፕላኑ መብረር ከሚገባው 35 ደቂቃ ለመዘግየት ተገዶ ነው የተነሳው።

በዳኝነት ዘመንህ ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛውን ውድድሮችን በዳኝነት መርተሀል። በዚህ አጋጣሚ ያዘንክበት ጨዋታ አለ?

ብዙውን ጊዜ የፍፃሜ ጨዋታዎችን መርቻለው፣ ብዙ የኮከብነት ክብር አግኝቻለው። በዚህ ሁሉ ጥንካሬ ውስጥ መቼም ሰው ፍፁም አይደለም፤ ልሳሳትም እችላለው። በ1996 ወይም 97 መሰለኝ ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሲጫወቱ ቡናዎች ፍፁም ቅጣት ምት ከለከልከን፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ከግብጠባቂው እጅ የተነጠቀ ኳስ ነው የገባብን በማለት ይናገራሉ። አካክሶም ነው ይላሉ አሉ። ለኔ ግን በቅርበት እስከታየኝ ድረስ በራሴን ንፁህ ህሊና የሰራሁት ነው። ጨዋታው አልቆ ስወጣ ግን ያሁሉ ውርጅብኝ የወረደብኝን በዳኝነት ዘመኔ ካሳዘነኝ አጋጣሚዎች አንዱ ነው። ዳኝነት ለፍተህ፣ ደክመህ ሰርተህ የምትሰደብበት ሙያ ነው። ይህ ሁኔታን በህይወቴ ከማረሳው ነው። በተረፈ ግን አብዛኛውን በሙገሳ በጭብጨባ በምስጋና ነው የጨረስኩት።

አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ዳኝነትን እንዴት ታየዋለህ ?

አሁን ያለውን ዳኝነት የማየው በጣም እድለኞች መሆናቸውን ነው። ቴክሎኖጂው በጣም በሰፋበት፣ ዳኛውን የሚረዱ ብዙ ነገሮች በተፈጠሩበት ዘመን ላይ የተገኙ በመሆናቸው ዕድለኛ ናቸው። ከእኔ ማቆም በኋላ በጣም ክፍተት ተፈጥሮ ነበር። ጠንካራ ወጥ አቋም ለተከታታይ ዓመት የሚያሳዩ ዳኞችን ለማየት ተቸግረን ነበር። ሆኖም ሁሌም የማይደክመው፣ ጠንካራው ሠራተኛ የኔ ወንድም እስኪመስል ድረስ በዓምላክ ተሰማ ብቅ ብሏል። ከሴቶችም አሉ ምሳሌ የሚሆኑ። ግን ይህንን እያዩ መነሳሳት ነበረባቸው። ሌላው የሚያሳዝነኝ ምድነው። እዚህ ሀገር ዕድሎች አግኝተዋል ኤሊት ውስጥ ገብተው ከአንድ ሁለት ሦስት ሰዎች ውጭ ወጥተው ጥሩ ደረጃ መድረስ የሚቻለውን አጋጣሚ ባልታወቀ ምክንያት ተቀንሰዋል። አንዴ ሪትም ውስጥ ከገባህ መውጣት የለብህም። የዚህ ዘመን ዳኞች ጥሩ ናቸው። ግን መስራት ይጠብቅባቸዋል። በዓምላክን እያየ የሚተኛ ዳኛ ያለ አይመስለኝም። ጥሩ ጥሩ ወጣት ዳኞች አሉ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ከትናንት ዛሬ እንዴት ታየዋለህ ?

በሌላ ሙያ ገብቼ ብዙም እንዳልዘላብድ አደራ ። ቀድሞ የነበሩ ጨዋታዎች ማንም የሚመሰክረው ነው። እናንተ ወጣቶች የድሮውን ኳስ በታሪክ ነው የምታቁት። ድሮ ገንዘብ የለም ነበር። ለዚህም ነበር አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ከሀገራቸው ውጭ ለጨዋታ ሲሄዱ የሚጠፉበት ምክንያት፤ ሀገራቸውን እግርኳስን ጠልተው አይደለም። ኑሯቸውን ለማሻሻል ብለው ነው። ድሮ ኳስ ነበር። ተወው ይሄንን አንድ ግብጠባቂ ለብሔራዊ ቡድን ለመምረጥ አሰልጣኞች ማንና እንምረጥ ብለው የሚጨነቁበት፣ የሚቸገሩበት ፣ ስድስት ሰባት ክለቦች ምርጥ ግብጠባቂዎች የሚያፈሩበት ጊዜ ነበር። የአጥቂዎች ጠንካራ ምት፣ ወኔ አልሸነፍ ባይነት፣ ሲሸነፉ እንባቸውን ጠርገው የሚወጡበት ጊዜ ነበር። በዛን ጊዜ በዳኛ ምክንያት ማድረግ የለም። አብረኸው ከነስህተቱ አሸንፈህው ውጣ ነው የሚባለው። የድሮውን እና የአሁኑን ማነፃፀር ከባድ ነው። ከፍተኛ ልዩነት አለ። የአሁኑ ቴክኒካሊ ጠቅጠቅ ነች እንጂ ብዙም ነገር የለውም። እውነት ለመናገር የአሁኑ ለገንዘብ ነው። የአሁኑ ብልጥ ነው ጎበዝ ነው። አብዛኛው ላለመጎዳት ራሱን እግሩን ነው የሚጠብቀው። ወደ ፊት ብዙ ስልጠናዎች ያስፈልጋሉ፤ የድሮውን ለመመለስ። በተለይ ግብጠባቂ ላይ በጣም ነው የማዝነው ከአስራ አንድ በላይ የሊጉ ክለቦች የውጭ ማድረጋቸው በጣም ያሳፍራል። እንግዲህ ባለሙያ ባልሆንም ስለጠየከኝ ትንሽ ይሄን ልናገር ብዬ ነው።

የቤተሰብ ህይወት?

ትዳር ይዣለሁ፤ የአንድ ቀውላላ የባስኬት-ቦል ቁመና ያለው ወንድ ልጅም አባት ነኝ። ቅዱስ ኃይለመላዐክ ይባላል። ቁመቱ ከእናትዬው ከእኔም በልጧል። ሁለታችንም ረዥም በመሆናችን በእኛ የወጣ ይመስለኛል። ባለቤቴ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል “ኒኩለር” ሜዲሲን የህክምና ባለሙያ ነች። እኔ ደግሞ በፊት ኦዲት ቢሮ ነበር የምሰራው አሁን በግል ድርጅት የጠቅላላ አገልግሎት ቢሮ ኃላፊ ሆኜ ነው የምሰራው። በዚህ ሁሉ የዳኝነት ዘመኔ ምርጡ የሠላሳ ዓመት በላይ ጓደኛዬ አብሮኝ አሁንም ያለው ዶ/ር አያሌው ጥላሁን ማመስገን እፈልጋለው። በመጨረሻም እግርኳስን በጣም አመሰግናለው። በእግርኳስ ብር የራሴን ቤት ገንብቻለው፣ መኪና ገዝቻለው። ዘጠና ዘጠኝ ፐርሰት በእግርኳስ ነው የተጠቀምኩት። ስለዚህ ሁሉም ዳኞች እዛ ቦታ ላይ ለመድረስ ተግቶ መስራት ይጠይቃል እላለሁ።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ