ኢትዮጵያ ቡና የተጫዋቾቹን ውል አድሷል

ኢትዮጵያ ቡና የውል ዘመናቸው የተጠናቀቁ ሦስት ተጫዋቾችን ውል ለማደስ ከስምምነት ላይ መድረሱ ታውቋል። አማኑኤል ዮሐንስ፣ አሕመድ ረሺድ እና ተመስገን ካስትሮ ያራዘሙ ተጫዋቾች ሆነዋል።

ከወጣት ቡድኑ አድጎ ያለፉትን አምስት ዓመታት ያገለገለው አማኑኤል ዮሐንስ ካለፈው የውድድር ዓመት ጀምሮ የቡድኑ አምበል የሆነ ሲሆን በተሰረዘው የዘንድሮው የውድድር ዓመትም በተለያዩ ሚናዎች የካሳዬ አራጌን ቡድን ሲያገለግል መቆየቱ ይታወቃል።

ሌላው ለማራዘም የተስማማው ተጫዋች ሁለተኛ አምበል የሆነው አሕመድ ረሺድ ነው። የመስመር ተከላካዩ ቡናን በመህቀቅ በ2010 ለድሬዳዋ ከተጫወተ በኋላ በ2011 ተመልሶ ኢትዮጵያ ቡናን ሲያገለግል ቆይቷል።

ተመስገን ካስትሮ ሦስተኛው የቡና ቆይታውን ያራዘመ ተጫዋች ሆኗል። ሁለገቡ ተጫዋች በ2011 ቡናማዎቹን ተቀላቅሎ መልካም አጀማመር ቢያደርግም በከባድ ጉዳት ለረጅም ጊዜያት ከሜዳ ለመራቅ ተገዶ በተሰረዘው የዘንድሮው የውድድር ዓመት ወደ ሜዳ መመለስ ችሎ ነበር።

ከክለቡ ጋር በተያያዘ ስማቸው ያልተጠቀሱና በቆይታቸው አሳማኝ እንቅስቃሴ ያላሳዩ ተጫዋቾች እንደሚቀነሱ የታወቀ ሲሆን በቅርቡ ስማቸው ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በተመሳሳይ ሦስት ተጫዛቾችን ወደ ቡድኑ ለመቀላቀል መቃረቡ ተነግሯል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ