“ከልጅነቴ ጀምሮ ስፈልገው ወደነበረበት ቦታ በመምጣቴ በጣም ደስ ብሎኛል” አዲሱ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

👉“ምንም እንኳ ባልጠበኩት ጊዜ ቢሆንም ለዚህ ታላቅ ሃላፊነት በመታጨቴ እና ከልጅነቴ ጀምሮ ስፈልገው ወደነበረው ቦታ በመምጣቴ ታላቅ ደስታ ተሰምቶኛል”

👉”ከኢንስትራክተር አብርሃም ጋር ትላንት ተደዋውለን ነበር…”

👉”ከዚህ በፊት የነበረውን ብሔራዊ ቡድን 100% አስቀጥላለሁ ብዬ ቃል አልገባም”

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ ረፋድ ወሎ ሠፈር በሚገኘው ጽሕፈት ቤቱ አሠልጣኝ ውበቱ አባተን የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ አድርጎ መሾሙን በጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። በመግለጫውም አሠልጣኙ ብሔራዊ ቡድኑን ለሁለት ዓመታት ለማሰልጠን ፊርማቸውን መስከረም 15 ማሳረፋቸው ተገልጿል። አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በቆይታቸው ብሔራዊ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ የማሳለፍ እና ለዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ዙር (ፕሌይኦፍ) ማድረስ እንደ ግዴታ ተጥሎባቸው ሃላፊነት እንደተሰጣቸውም ተብራርቷል። የነዳጅ እና የስልክ እንዲሁም ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ሳይጨምር በወር ያልተጣራ 212 ሺ ብር (የተጣራ 125 ሺ) እንደሚያገኙ የተገለፀው አሠልጣኝ ውበቱ አባተ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ መሆናቸው ይፋ ከሆነ በኋላ ሃሳባቸውን በስፍራው ለተገኙ ብዙሃን መገናኛዎች አካፍለዋል።

“ምንም እንኳን ባልጠበኩት ጊዜ ቢሆንም ለዚህ ታላቅ ሃላፊነት በመታጨቴ እና ከልጅነቴ ጀምሮ ስፈልገው ወደነበረበት ቦታ በመምጣቴ በጣም ደስ ብሎኛል። በተቻለኝ አቅም ጥሩ ስራዎችን በመስራት በውሌ ላይ የተቀመጠውን ግዴታ ለማሳካት እጥራለሁ። እንዳልኩት ባላሰብኩት እና ባልጠበኩት ጊዜ ቢሆንም እድሉን ያገኘሁት ሁል ጊዜ እንደ አሠልጣኝ ዝግጁ ነበርኩ። እኔ ከዚህም በላይ ከባባድ ፈተናዎች በእግርኳስ የአሠልጣኝነት ህይወቴ አሳልፌያለሁ። ይህ ፈተና ለእኔ አዲስ ቢሆንም ራሴን በሚገባ አዘጋጅቼ ፈተናውን እጋፈጣለሁ።

“በአጭር ጊዜ ተጫዋቾችን ሰብስቦ ወደ ጨዋታ መግባት እጅግ ከባድ ነው። ለዛውም ለ7 ወራት ከእንቅስቃሴ የራቁ ተጫዋቾችን ሰብስቦ። ይህ ግን በዓለም የመጣን ችግር ተከትሎ ስለሆነ የሆነው ምንም ማድረግ አንችልም። ከዚሁ ጋር አያይዤ መግለፅ የምፈልገው ከዚህ በፊት የነበረውን ብሔራዊ ቡድን 100% አስቀጥላለሁ ብዬ ቃል አልገባም። ምክንያቱም ተጫዋቾቹ ምን ላይ እንዳሉ ስለማላቅ። አሁን ላይ ግን ሰፋ ያለ ስብስብ ጠርተን በቶሎ የሚደርሱልንን ተጫዋቾች መርጠን ዝግጅታችንን እንቀጥላለን።

“ከዚህ በፊት በክለብ ደረጃ ያሳየሁትን የጨዋታ አስተሳሰብ በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ለማስቀጠል እሞክራለሁ። ብሔራዊ ቡድን ላይ እንደውም ከክለብ የተሻለ ነገር ይገኛል። ምክንያቱም የተጫዋቾች ውል እና ደሞዝ ሳያሳስበን በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን የትኛውንም ጎበዝ ተጫዋች መርጠን ስለምንይዝ። ስለዚህ በዚህ ጥቅም የተሻለ ነገር ለመገንባት እንሞክራለን።

“እርግጥ ነው ከሰበታ ከተማ ጋር የአንድ ዓመት ውል ነበረኝ። ግን ይህ ሃገራዊ ጥሪ ነው። እነሱም ሃገሬን እንዳገለግል ፍቃድ ሰጥተውኛል። ፌዴሬሽኑም የሚቀሩ የወረቀት ስራዎችን ለማጠናቀቅ እየሰራ ነው።

“በግሌ አብርሃም ይቀጥላል የሚል እምነት ነበረኝ። ምክንያቱም የእርሱ ቡድን በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ነገርን እያሳየ ስለመጣ። እኔም ከክለቤ ጋር ውል ስለነበረኝ ወደዚህ ቦታ እመጣለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። ግን ነገሮች በዚህ መልኩ ተጓዙ።

“አሁህም ድረስ ግን ከአብርሃም ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ። በፊትም እርሱ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ተደርጎ ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ የአቅሜን ሙያዊ ድጋፍ ሳደርግለት ነበር። አሁንም ጥሩ ጓደኛዬ ነው። እንደውም ትላንት ማታ ተደዋውለን ነበር። ‘መልካም የስራ ዘመን’ ብሎ ጥሩ ምኞቱን ተመኝቶልኛል።

“የአሠልጣኝ ቡድን አባላትን በተመለከተ ከፌዴሬሽኑ ጋር ተነጋግረናል። አንድ የግብ ጠባቂ አሠልጣኝ እና ሁለት ረዳት አሠልጣኞችን በራሴ እንድመርጥ መብት ተሰጥቶኛል። ከዚህ ውጪ ሌሎች እኔን የሚረዱ የአሠልጠኝ ቡድን አባላትን ወደ ስብስቡ ለማካተት ከፌዴሬሽኑ ጋር እየተነጋገርን ነው።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!