በአሠልጣኝ ቅጥር ዙሪያ የተፈጠረው አለመግባባትን አስመልክቶ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ማብራርያ ሰጡ

በአሠልጣኝ ቅጥር ዙሪያ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ እና የቴክኒክ ኮሚቴ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ግልፅ አደረጉ።

ረፋድ 4:30 በተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አዲሱ አሠልጣኝ ማን እንደሆኑ ተገልጿል። በዚህም የቀድሞ የአዳማ ከተማ፣ የደደቢት፣ የኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የሀዋሳ ከተማ፣ የፋሲል ከተማ እና የሰበታ ከተማ ዋና አሠልጣኝ የነበሩት ውበቱ አባተ ብሔራዊ ቡድኑን ለሁለት ዓመታት ለማሰልጠን መሾማቸው ተነግሯል። ታዲያ እሳቸው ወደ መንበሩ ከመምጣታቸው በፊት የብሔራዊ ቡድኑን አሠልጣኝ ለመምረጥ በነበረው ሂደት ውስጥ የፌዴሬሽኑ የቴክኒን ኮሚቴ እና ሥራ አስፈፃሚው መካከል የተፈጠረውን ልዩነት አቶ ኢሳይያስ ጂራ አብራርተዋል።

“የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ በሥራ አስፈፃሚው ስር የሚገኝ ንዑስ ኮሚቴ ነው። ኮሚቴውም ሥራ አስፈፃሚውን የሚረዳ ነው። የኢትዮጵያን እግርኳስ በበላይነት የሚመራው ፌዴሬሽኑ ውስጥ የሚገኘው የሥራ አስፈፃሚ ነው። ከዚህ ሥር ያለ ማንኛውም ኮሚቴ እየተነሳ የውሳኔ አካል ልሁን ማለት አይችልም።

“የዛሬ ሁለት ዓመት አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱን ወደ ብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝነት ስናመጣ የቴክኒክ ኮሚቴው እንደ አሁኑ ምክረ ሃሳብ አቅርቦልን ነበር። ግን በጊዜው በቀረበው ነገር ስላላመንን አብርሃምን መርጠን በቦታው ሾመናል። አሁንም የሆነው ይህ ጉዳይ ነው። ኮሜቴው እንደ ድጋፍ ሰጪነቱ ምክረ ሃሳብ እንዲሰጠን ጥያቄ አቀረብን። ኮሚቴውም አማራጮች እና ዝርዝሮች የሌሉት ባለ 9 ነጥብ ሃሳብ አቀረበልን። በነጥቦቹ ውስጥም በኮሮና ምክንያት ውድድሮች በመቋረጣቸው፣ አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ የመጨረሻውን ጨዋታ አሸንፎ በመሸለሙ፣ አሠልጣኙ ከተጫዋቾቹ ጋር ጥሩ ግንኙነት ስላለው፣ ምንም አይነት ማስጠንቀቂያ ከዚህ በፊት ስላልተሰጠው እያሉ የሚቀጥሉ ሃሳቦች በሰነዱ ሰፍረዋል። እኛ ግን ምክረ ሃሳቡ ለአንድ አካል ያጋደለ መሆኑን ነግረን አብርሃምን ጨምራችሁ ሌሎች አማራጮችንም እዩ እና አምጡልን። ለዚህም ሁለት ቀን እንሰጣችኋለን ብለን ትዕዛዝ ስናስተላልፍ አይሆንም የሚል ምላሽ ተሰጠን። እኛ ግን የፌዴሬሽኑ መሪዎች ስለነበርን ውሳኔዎችን ወስነን በቶሎ ወደ ቀጣይ ሥራዎች ተላለፍን።

“የስራ አስፈፃሚው ስብሰባ ሲያደርግ የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሰውነት ቢሻው መሃል ላይ ከቤተሰቦቻቸው በተደወለ ስልክ ምክንያት እኔን አስፈቅደው ወተዋል። እኛ ግን እንደ ስራ አስፈፃሚ ያመንበትን እየወሰንን መቀጠል ስላለብን ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠን ወጥተናል።

“የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ትልቅ ተቋም ነው። የሚከተለው አሰራር እና አደረጃጀትም ተቋማዊ ነው። ፌዴሬሽኑ ውስጥ ያለ ግለሰብ ሁሉ ነገሮችን በግሉ ማድረግ አይችልም። በግልም ‘ውሳኔ ሰጪ እኔ ልሁን’ ማለት የለበትም። በተጨማሪም ሁሉም ለየብቻው መግለጫ አይሰጥም። ስለዚህ ተቋሙ እንደ ተቋም አደረጃጀቱን ወጥ አድርጎ ሥራዎችን ይሰራል።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!