“የተዝረከረከ ፣ ውጤት ያጣ በቀላሉ እጅ የሚሰጥ ፣ የሚሸነፍ ቡድን ከዚህ በኋላ በኢትዮ ኤሌክትሪክ አይገነባም” አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ የሊጉን ዋንጫ ካሳኩ አልፎም ደግሞ ለሀገራችን እግር ኳስ አበርክቷቸው ላቅ ካሉ ክለቦች መካከል ይጠቀሳል ኢትዮ ኤሌክትሪክ። የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለሁለት ጊዜያት ያክል ያሳካው ክለቡ ከሀገሪቱ ትልቁ የሊግ ዕርከን በ2010 ከወረደ ከአራት ዓመታት የከፍተኛ ሊግ ተሳትፎው በኋላ በተጠናቀቀው የ2015 የውድድር ዘመን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደግ ቢችልም በርካታ አሰልጣኞችን በመቀያየር በሊጉ ለመቆየት ከታገለ በኋላ በመጨረሻም ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ከፍተኛ ሊግ ለመውረድ መገደዱ ይታወሳል። ቡድኑ ባለፈው የውድድር ዘመን ከፕሪምየር ሊጉ መውረዱን ካረጋገጠ በኋላ የቀድሞው የሐረር ቢራ ፣ ስሑል ሽረ እና ድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ የነበሩትን አሰልጣኝ ሳምሶን አየለን በሦስት ዓመት ውል በመቅጠር ሰፋ ካሉ ቅድመ ዝግጅቶች በኋላ በዘንድሮው የከፍተኛ ሊግ ምድብ ‘ሀ’ ስር በመደልደል ቡድኑ ሲወዳደር ቆይቶ በድጋሚ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ 2017 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቀሪ አምስት ጨዋታዎች ቡድኑ እየቀረው ማደጉን አረጋግጧል። ተወዳጇ ሶከር ኢትዮጵያም ስለ ውድድር ዘመን ጉዞው እና መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት ከአሰልጣኙ ጋር ቆይታን አድርጋለች።


ስለ ውድድር ዓመቱ ጉዞው…

“በጣም ደስ ብሎኛል ምክንያቱም ትልቁ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ እና ሪከርድ በሚባል ደረጃ በጣም በጥራት ቀደም ብሎ ጨዋታዎች እየቀሩት ወደ ፕሪምየር ሊግ ወደነበረበት ከፍታው መመለሱ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል ፣ ከዚህ ውጪ ግን ይሄኛው ውጤት እንዲመጣ ትልቁን ትልቁን ድርሻ የተወጣው አመራሩ ነው። አመራሩ ይህንን ሚና የተወጣበት ዋናው ምክንያት ምንድነው እንደሚታወቀው በ2015 በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ታችኛው ሊግ መውረዱ ይታወቃል ነገር ግን አመራሩ እዛ ጋር የወሰደው ቁርጠኛ ነገር ምንድነው ወደ ውስጥ የነበሩትን ችግሮች በማየት አሁን ላይ ያለንበት ሁኔታ ምንድነው ወደፊት ቡድኑን ለመመለስ ምን ማድረግ አለብን የሚለውን በጣም በስፋት ካየና ከተወያየበት በኋላ በቀጥታ ወደ ስራ ውድድሩ ሳያልቅ የተገባው ከዛ አንፃር የመጀመሪያ ስራቸው አሰልጣኝ መቅጠር ነበር በዛም እኔ ነኝ ዕድሉን አግኝቼ እንድሰራ የተደረገው ያንን መነሻ በማድረግ ጎን ለጎን ሊጉ ላይ ልምድ ያላቸው አቅም ያላቸው ተጫዋቾችን እንድመለምል በጊዜ ዕድሉን ሰጥተውኛል። 2015 ቡድኑ ሲወርድ የነበሩ እኔ ማስቀጠል የምፈልጋቸውን ይህንን ሁሉ አማራጭ ሰጥተውኝ ነው ወደ ስራ እንድገባ የተደረኩት ከዛ አንፃር የምፈልጋቸውን አንድ ሦስት ተጫዋቾች ይዣለሁ በመቀጠል ከፍተኛ ሊጉ ላይ በአጋጣሚ ውድድሩን የማየትም አጋጣሚ ስለነበረኝ ሊጉም ላይ የመስራት ዕድሉ ነበረኝ ከዚህ በፊት ምንም ቆየት ቢልም ያንን መነሻ አድርጌ በጣም ወጣቶች ኢነርጀቲክ የሆኑ የከፍተኛ ሊጉን የውድድር ባህሪ የሚያውቁ ተጫዋቾች በመመልመል ፣ የምልመላው ጥራት ብቻ አይደለም ስፋት እንዲኖረው በማድረግ በስፋትም በጥልቀትም ተጫዋቾችን ይዘን ጠንካራ አድርገን ፣ ሰፊ የዝግጅት ጊዜ ፣ የሚያስፈልገው ሁሉ ተሟልቶ ጠንካራ ስራ ሰርተን ይህው ዛሬ ላይ በዛ ልክ ወደነበረበት ወደ ከፍታው ፕሪምየር ሊግ ለመመለስ ዕድል አግኘተናል በድጋሚ በጣም ደስ ብሎኛል።”


ይህንን ትልቅ ቡድኑ በፍጥነት ወደ ፕሪምየር ሊጉ የመመለስ ፈተናው እና ስለ ፈጠረባቸው ስሜት …

“ኢትዮ ኤሌክትሪክ የኢትዮጵያ የዘመናዊ እግር ኳስ መሠረት ነው ፣ አንጋፋ ክለብ ነው ስለ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በዚህች አጭር ጊዜ ይሄ ነው ብሎ መጨረስ አይቻልም ነገር ግን በዚህ ውስጥ ይህንን ቡድን በጣም በከፍተኛ ጥራት እና በጥሩ አቅም በዚህ ልክ ወደነበረበት ለመመለስ እንደዚሁ ቀላል አልነበረም ፈታኝ ነበር ውጫዊው ፣ ውስጣዊም ተፅዕኖዎች ነበሩ በቃ እነደዚህ ብለን በዝርዝር የማንገልፃቸው ነገር ግን ከሜዳ የውድድር ባህሪ አንፃር ስንነሳ ግን ከፍተኛ ሊግ በጣም ፈታኝ ውድድር ነው። እንደውም ምንአልባት ከፕሪምየር ሊጉ አንድ ስቴፕ ዝቅ ሲል ብዙ ሰዎች ላይረዱት ይችላሉ እኔ እንደ ባለሙያ የምገልጸው ከፕሪምየር ሊጉ በላይ ፈታኝ ፣ እልህም አስጨራሽ ነው። የትኛውም ተጋጣሚ ቡድን ቀላል ነው ነጥብን እወስድበታለሁ ብለህ የምትመጣበት ሁኔታ የለም ፣ ተጫዋቾቹም የተሰጣቸውን ሀላፊነት ለመወጣት ያደርጉት የነበረው የሰጡትም መስዋዕትነት በጣም ከፍተኛ ነበር ነገር ግን እነዚህ ውስጣዊ የነበሩ ተፅዕኖዎች ፣ ውጫዊ የነበሩ ተፅዕኖዎች ተቋቁመን ለምሳሌ በአንደኛው ዙር አካባቢ ዛሬ ላይ እንዲህ ነው ብዬ በማልገልፀው ሁኔታ ቅጣት ተቀጥቼ ነበር አንዱ ይሄ የትግሉ አንድ አካል አድርጌ ነው የምወስደው ፣ የነበሩ ነገሮችን ሁሉ በመቋቋም ቻሌንጅ በማድረግ በተለይ ተጫዋቾቹ በአካልም በአዕምሮም ጠንክረው የተሰጠንን ኃላፊነት ለመወጣት እንዳልኩህ የሜዳ ላይ ስራ ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጪም የሚኖራቸው ከስነ ልቦና ጋር ተያይዞ ጠንክረው እንዲሰሩ ተሞክሯል። የትኛውም የእኛ ተጋጣሚ ቡድን ወደ እኛ የሚመጣበት መንገድም አንዱ ቻሌንጅ ነበር እጅግ እጅግ ጠንካራም ነበር ነገር ግን እርሱን ውጤታማ አድርጎ ከመሄድም አንፃር ሰፊ ስራ ነው የሰራነው በዚህ አጋጣሚ ተጫዋቾቼ ለከፈሉት መስዋዕትነት ሳላመሰግን አላልፍም። በተለይ እንደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዓይነት አንጋፋ እና ትልቅ ክለብ የበጀት ችግር የሌለበት ነገር ግን በውጤት ውጣ ውረድ ውስጥ በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚያዋዥቅን ክለብ በዚህ ሁኔታ በጣም በአጭር ጊዜ ወደነበረበት እንዲመለስ ለማድረግ ተጫዋቾቹም ፣ የክለብ አመራሩም ፣ ፅህፈት ቤቱም ፣ ኮቺንግ ሰታፉም ለከፈለው መስዋዕትነት እጅጉን በጣም አመሰግናለሁ እንደ አጠቃላይ ግን በጣም ፈታኝ የውድድር ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል።”

አምስት ጨዋታዎች እየቀራችሁ ማደጋችሁን ተንተርሶ ብዙ ማሰቢያ እና ማሰላሰያ ጊዜ አላችሁ ባለፈው ዓመት የገጠመው ችግር እንዳይደገም ምን መሰራት አለበት ….

“በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው ፣ ምንድነው ቀደም ብዬ እንደገለፅኩልህ ክለቡ የመጀመሪያው ስራዬ የ2015 የውድድር ዘመን ከማለቁ በፊት በተለይ ቡድኑ ወደ ታችኛው ሊግ መውረዱ ሲረጋገጥ አመራሩ ከፍተኛ ስራ የሰራው አንዱ ዕቅድ ምንድነው በርካታ አሰልጣኞችን ለውድድር በማቅረብ በዛው ውስጥ ለሚመጣው አሰልጣኝ ሰፊ የስራ ጊዜን መስጠት ነው። ለምሳሌ ለእኔ የሰጡኝ የሦስት ዓመት ኮንትራት ነው ከእነኚህ የሦስት ዓመት ኮንትራቶች ውስጥ የመጀመሪያው ዓመት ላይ ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊግ መመለስ ፣ ሁለተኛው ዓመት ላይ በሊጉ እንዲቆይ ማድረግ ፣ ሦስተኛው ዓመት ላይ በፕሪምየር ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ለሻምፒዮንነት የሚጫወት ቡድን መገንባት የሚል ነው። ከዛ አንፃር ዕቅዱ ሰፊ ነው አሁን በዚህ ሦስት ዓመት ውስጥ ምን መሰራት አለበት የሚለውን በዝርዝር ሲቀመጥ ያለፉትን ዓመታት የቡድኑን የውጤት ቀውስ እና ውጣ ውረድ ያማከለ እና በዛ ላይ ሰፊ ግምገማ እና ስራ ተሰርቶበን ነው ስለዚህ በቀጣይ የባለፉት ዓይነት የተዝረከረከ ፣ ውጤትም ያጣ በቀላሉ እጅ የሚሰጥ ፣ የሚሸነፍ ቡድን ከዚህ በኋላ በኢትዮ ኤሌክትሪክ አይገነባም። በዚህ እኔ መቶ ፐርሰንት ዕርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁ ምክንያቱም ከተጫዋች ጥራት ፣ ከአደረጃጀት ፣ ከዝግጅት ጊዜ እንደ አጠቃላይ ሰፊ ስራ በመስራት ልክ አሁን በመጣንበት ልክ ፕሪምየር ሊጉም ላይ ጠንካራ ቡድን ገንብተን የማስቀጠል ስራዎች ከወዲሁ ተጀምሯል እርሱን አጠናክረን የምንሄድበት ነገር እንፈጥራለን ከዛ ውጪ አመራሩ እንደ አመራር እንደ አንድ ጥሩ ግብዐት የወሰደው ነገር ምንድነው በስትራክቸር ደረጃ ቡድኑ ችግር የለበትም ፣ በመዋቅር ደረጃም አደረጃጀቱ በጣም ዘመናዊ ነው የራሱ የመለማመጃ ሜዳ ያለው ፣ የበጀት ችግር የሌለበት ቡድኖ ሆኖ ነገር ግን አፈፃፀም ላይ ከጥራት አንፃር ባልተሟሉ ነገሮች ላይ የሚደረጉን ወደ ውስጥ ገምግሟል ፣ እነኚህ ከአሁን በኋላ በኢትዮ ኤሌክትሪክ ቡድን ውስጥ አይታዩም። ወደነበረበት ወደ ድሮ ከፍታው በመሄድ እንደ ዛሬ አቻዎቹ እንደነ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ እንደነ መቻል በዛ ልክ እና ከዛም ከፍ ብሎ እንዲሄድ ከወዲሁ ስራዎች እየተሰሩ ነው ያለው እርሱን አጠናክረን እንቀጥላለን በዚሁም መጠን እንዲጠብቁንም ነው ደጋፊውን የማሳስበው።”

በመጨረሻም …

“በመጨረሻም የማስተላልፈው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ትልቅ ክለብ ነው። በውጤት ውጣውረድ ውስጥ አልፎ የነበረው ዘንድሮ በዚህ ባልተለመደ ሁኔታ ከፍ ብሎ አምሰት ጨዋታ እየቀረው ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲገባ ፣ የመግባት ዕድልም እንዲያገኝ ሲደረግ የዛ ታሪክ የመጀመሪያው የትልቁ ክለብ አሰልጣኝ ሆኜ በመገኘቴ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል። በዚህ ውስጥ ይህ ቡድን ውጤታማ እንዲሆን ለረዱኝ ፣ ለተባበሩኝ ቤተሰቦቼ ፣ ጓደኞቼ ፣ የክለብ አመራር ፣ ሰራተኞች ፣ ደጋፊው በተለይ ተጫዋቾቹ እና ኮቺንግ ስታፉ ላደረገልኝ ድጋፍ እና ዕገዛ በእጅጉ እያመሰገንኩ እናንተም ለሰጣችሁኝ ጊዜ በጣም አመሰግናለሁ።”