የኢትዮጵያ ዋንጫ መረጃዎች

ኃይቆቹ እና ቡናማዎቹ ወደ ፍጻሜው ለማለፍ የሚያደርጉትን ተጠባቂ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ወላይታ ድቻን ተከትሎ ወደ ፍጻሜው የሚያልፍ ቡድን የሚለየውን ተጠባቂ ጨዋታ አስመልክተን የሚከተሉትን ነጥቦች አንስተናል።

ወልዲያን አራት ለባዶ በማሸነፍ የኢትዮጵያ ዋንጫ ጉዟቸው አሀዱ ብለው የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ኮልፌ ቀራንዮና ፋሲል ከነማ ላይ ያስመዘገቧቸው ድሎች ወደ ግማሽ ፍፃሜው እንዲገቡ አስችሏቸዋል። ቡናማዎቹ ባከናወኗቸው ሦስት ጨዋታዎች አስር ግቦች ተጋጣሚው ላይ ያዘነበ ጠንካራ የማጥቃት ክፍል አላቸው። የፊት መስመሩ ምንም እንኳ በመጨረሻዎቹ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ላይ ሁለት ግቦች ብቻ በማስቆጠር ውስን መቀዛቀዞች ቢያሳይም በመጨረሻዎቹ አራት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ስምንት ግቦች ላስተናገደው የሀዋሳ ከተማ ተከላካይ ክፍል ፈተና መሆኑ ግን አይቀሬ ነው።

ሆኖም በኢትዮጵያ ዋንጫ ላይ በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ ግብ ያላስተናገደው የቡናማዎቹ የኋላ መስመር ግብ ከማስቆጠር የማይባዝነውን የኃይቆቹ የፊት መስመር የማቆም ትልቅ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኖቹ ከሁለት የጨዋታ ሳምንታት በፊት ባደረጉት ጨዋታ ላይና በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የታዩባቸውን የትኩረት ማጣት ችግሮች መቅረፍ ይኖርባቸዋል።

በሦስቱም ዙሮች ያገኟቸውን ቤንች ማጂ ቡና፣ መቻል እና አርባምንጭ ከተማን አሸንፈው ወደ ግማሽ ፍጻሜ ያሻገራቸውን ውጤት ያስመዘገቡት ሀዋሳ ከተማዎች በፕሪምየር ሊጉ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ድል አድርገው ወደ ነገው ጨዋታ ይገባሉ።

ሀዋሳ ከተማዎች ፍሬያማ የሆነ የፊት መስመር አላቸው ፤ በውድድሩ አንድ ግብ ብቻ በማስተናገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ካበረከተው የተከላካይ ክፍል በጋራ ለቡድኑ እዚህ ደረጃ መድረስ የጎላ ድርሻ የነበረው ጥምረቱ በውድድሩ ሰባት ግቦች ማስቆጠር ችሏል። በተለይም ቡድኑ በውድድሩ ካስቆጠራቸው ሰባት ግቦች ውስጥ ስድስቱን ያስቆጠረው ፈጣኑ አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። ቡድኑ ምንም እንኳ በሊጉ በአራት ጨዋታዎች አስር ግቦች ካስቆጠረበት ድንቅ ጊዜ በኋላ ባደረጋቸው ሁለት የመጨረሻ ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ቢያስቆጥርም ለፊት መስመሩ ጥንካሬ ትልቅ ግምት ከመስጠት አያግድም። ከዚህ በተጨማሪ በውድድሩ በ 270  ደቂቃዎች ከወንድማገኝ ኪራ ውጭ ማንም ያልደፈረው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ሌላው የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል በውድድሩ አራት ግቦች ያስቆጠረው መሐመድኑር ናስር በሀዋሳ ከተማ በኩል ደግሞ ስድስት ግቦች ያስቆጠረው ዓሊ ሱሌይማን በጨዋታው ከሚጠበቁ ተጫዋቾች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።

ሁለቱም ቡድኖች ከቅጣትም ሆነ ከጉዳት ነፃ የሆነውን ስብስባቸው ይዘው ወደ ነገው ጨዋታ ይቀርባሉ።

የሁለቱም ቡድኖች የውድድሩ ጉዞ

ሀዋሳ ከተማ 2 – 1 ቤንች ማጂ ቡና

ዓሊ ሱሌይማን (2) – ወንድማገኝ ኪራ

ሀዋሳ ከተማ 3 – 0 መቻል

ዓሊ ሱሌይማን (3)

አርባምንጭ ከተማ 0 – 2 ሀዋሳ ከተማ

ዓሊ ሱሌይማን
ተባረክ ሄፋሞ

ኢትዮጵያ ቡና 4 – 0 ወልዲያ

ብሩክ በየነ
ብሩክ በየነ
ጫላ ተሺታ
መሐመድኑር ናስር

ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ 0 – 2 ኢትዮጵያ ቡና

መሐመድኑር ናስር(2)

ፋሲል ከነማ 1 – 4  ኢትዮጵያ ቡና

ጌታነህ ከበደ(ፍ)  መሐመድኑር ናስር
አማኑኤል አድማሱ
መስፍን ታፈሰ (2)