“ሁለተኛ ቡድን በማስገባቴ በጣም ደስተኛ ነኝ” ጌቱ ባፋ የኢትዮ ኤሌክትሪክ አምበል

የኢትዮ ኤሌክትሪክን ወደ ፕሪምየር ሊጉ መመለስ ተከትሎ ከክለቡ አምበል እና ተከላካይ ጌቱ ባፋ ጋር አጠር ያለ ቆይታን አድርገናል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በምክትል አምበልነት እየመራ ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ፕሪምየር ሊግ አሳድጎ የነበረው ተጫዋቹ ዘንድሮም በተመሳሳይ ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ተቀላቅሎ ክለቡን በተከላካይነት እና በአምበልነትም ጭምር እየመራ ወደ 2017 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያሳደገ ሲሆን ተጫዋቹም የተሰማውን ስሜት ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል።

ስለ ውድድር ዓመቱ ጉዞ…

“የነበረው ነገር ትንሽ ከበድ ያለ ነው። አንዳንዴ ሰዎች የሚያውቁት ዋንጫውን ስታነሳ ነው በጣም በጣም ችግር አለ ፣ በዛ ላይ ጨዋታም ሰታደርግ ቡድኖች የሚሰጡህ ግምት ይኖራል። እኛ ካለን ነገር አንፃር ትንሽ አስቸጋሪ ነው ግን በተሰጠህ ኃላፊነት ሲያስፈርሙንም ደግሞ በኃላፊነት ነበር አሰልጣኛችም ፣ ስራ አስኪያጁ ሲሳይም ያስገቡህ ቃል አለ እንዴት ነው ንግድ ባንክን አስገብተሃል ይሄንንስ ትደግማለህ እንዴ ሲሉ “አዎ” የሚል ነገር ነበር እና ውድድሩ በጣም ከባድ ነው ትንሽ ትልቅ የምትለው ቡድን የለም ለእኔ ሁለተኛ ቡድን በማስገባቴ ያውም አምስት ጨዋታዎች እየቀሩ ለስኬት ማብቃት በመቻሌ በጣም ደስ ብሎኛል።”

ባለፈው ዓመት ንግድ ባንክን ዘንድሮ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ስለ ማሳደጉ እና ዘንድሮም ይሳካል ስላለው እምነቱ…

“የዓምናው ትንሽ ውጥረት አለው ፣ አንድ ጨዋታ ሲቀረው ነው ያረጋገጥነው ፣ ይሄ ግን በጣም በሰፊ ውጤት ነው ያረጋገጥነው የዓምናው በጣም ውጥረት አለው ይሄኛው የለውም እያልኩህ ሳይሆን በጊዜ የእኛ ጥንካሬ ነውና በተሰጠን ዕድል ተጠቅመን አሰልጣኛችን የሚሰጠን በጣም ጠንካራ ነገር ነው። ከመጀመሪያው ዝግጅት ከመግባታችን ጀምሮ የገባነው ቃል ይመስለኛል ለእዚህ ያበቃን እና ዘንድሮም እንደ ዓምናው ሁለተኛ ዙር ላይ ከእኛ በታች ያሉ ቡድኖች አቻ ሲወጡ እኛ ደግሞ ማሸነፋችን ይመስለኛል ፣ ውጤቱ እንዲሰፋ ያደረገው ያረጋገጥንበትም ምክንያት ያ ይመስለኛል።”

ይህ ውጤት እንዲመጣ በቡድኑ ውስጥ  ስለነበረው አንድነት…

“ዋነኛው ነገር ቲም ስፕሪት ነው። ቡድናችን ቲም ስፕሪቱ በጣም ደስ ነው የሚለው አምበልነትን ሲሰጡህ ደግሞ ብዙ ኃላፊነት አለብህ ዓምና እና ዘንድሮ በጣም ይለያል። ጠንካራ ጎናችን አንድነታችን ነው አንድነታችን በጣም ነው ደስ የሚለው አዲስ አበባ ላይ በጣም ነበር ደስ የምንለው በዛ ላይ ሁለት ጨዋታ ተሸንፈን ነው ከዛ በኋላ ድጋሚ የቀረንን ሁሉ ጨዋታ አሸንፈን አንደኛውን ዙር የጨረስነው እና ጠንካራ ነው በጣም እኔ በጣም ደስተኛ ነኝ ሁለተኛ ቡድን በማስገባቴ።”

ባለፈው ዓመት የገጠመው ችግር በቀጣዩ ዓመት እንዳይከሰት ምን ሊሠራ ይገባል…

“ይሄ የቡድኑ የበላይ ጠባቂዎች ስራ ይመስለኛል ከዚህ በኋላ ያለው ፣ ተጨማሪ ሰው አምጥተው ቡድኑ እንዲቆይ አሁን እንደመጣው ውጤት ሁሉ ፕሪሚየር ሊግም ላይ ከፍ ብሎ ቢታይ ደስ ይለኛል እኔ በመጨረሻም ስለ ሁሉም እግዚአብሔር ይመስገን።”