የኢትዮጵያ ዋንጫ | የፍጻሜ ተፋላሚዎች ተለይተዋል

ቡናማዎቹ ኃይቆቹን 2ለ0 በመርታት ወደ ፍጻሜው ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።

9፡00 ላይ በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ በጥሩ የኳስ ቁጥጥር ፈጣን አጀማመር ማድረግ የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች 9ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን ለመምራት እጅግ ተቃርበው ታፈሰ ሰለሞን ያመቻቸለትን ኳስ የተቆጣጠረው ዓሊ ሱሌይማን ከፍ አድርጎ (ቺፕ) የሞከረውን ኳስ የመሃል ተከላካዩ ራምኬል ጀምስ በድንቅ ቅልጥፍና ኳሱን ከመስመር አግዶታል።

ኃይቆቹ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ 21ኛው ደቂቃ ላይም በአማኑኤል ጎበና አማካኝነት ከሳጥን አጠገብ ጥሩ ሙከራ አድርገው ተከላካዩ ራምኬል ጀምስ በድጋሚ በግንባር በመግጨት አግዶባቸዋል።

ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ግለት የመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች 33ኛው ደቂቃ ላይ ያለቀለት የግብ ዕድል ፈጥረው መስፍን ታፈሰ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ አማኑኤል አድማሱ እና ኪያር መሐመድ ሳያገኙት ቀርተው የተሻለውን የግብ ዕድል አባክነውታል።

ኃይቆቹ በእንየው ካሳሁን እና በዓሊ ሱሌይማን ሙከራ ካደረጉ በኋላ የቡናማዎቹ አማካይ አብዱልከሪም ወርቁ 41ኛው ደቂቃ ላይ በግሩም ክህሎት ተከላካዮችን አታልሎ በማለፍ ያመቻቸለትን ኳስ ያገኘው መስፍን ታፈሰ ኃይል በሌለው ሙከራ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በውዝግብ በተሞሉ የአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ውስጥ የቡናው በፍቃዱ ዓለማየሁ በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት መሬት ለመሬት ያሻገረውን ኳስ ከአንድ ንክኪ በኋላ ያገኘው አማኑኤል ዮሐንስ ኳሱን ሊጠቀምበት ሲል በአማኑኤል ጎበና በተሠራበት ጥፋት ለኢትዮጵያ ቡና የፍጹም ቅጣት ምት ተሰጥቷል። በዚህም ዋሳዋ ጄኦፍሪ ሲመታ ግብ ጠባቂው ጽዮን መርዕድ ቢመልስበትም ኳሱ ከመመታቱ በፊት ከመስመር ወጥቷል በሚል በዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ውሳኔ የፍጹም ቅጣት ምቱ ተደግሟል። ሆኖም ዋሳዋ በሁለተኛው አጋጣሚ ምንም ስህተት ሳይሠራ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል። አጋማሹም በቡና መሪነት ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ሀዋሳዎች እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ሁሉ ጨዋታውን በጥሩ ግለት ቢጀምሩም በ53ኛው ደቂቃ ልፋታቸው ላይ ውሃ የሚቸልስ አጋጣሚ ተፈጥሮባቸዋል። ጸጋአብ ዮሐንስ ለግብ ጠባቂው ጽዮን መርዕድ ለማቀበል ሲሞክር ኳሱ በማጠሩ አቋርጦ ማግኘት የቻለው አንተነህ ተፈራ ግብ ጠባቂውን በቀላሉ በማለፍ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።

በጉሽሚያዎች እየጋለ በኳስ ፉክክሩ እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ 73ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የጨዋታ ቀን ያሳለፈው የኢትዮጵያ ቡናው የመሃል ተከላካይ ራምኬል ጀምስ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋችን በመማታቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወገድ የእርሱን ቦታ ለመሸፈን ወልደአማኑኤል ጌቱ በአማኑኤል አድማሱ ተተክቶ ገብቷል።

ሁለቱም ቡድኖች በርከት ያሉ ቅያሪዎችን በማድረግ ድጋሚ ወደ ተሻለ ፉክክር መመለስ ሲችሉ ቡናማዎቹ 84ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው መስፍን ታፈሰ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) ሊሞክር የፈለገውን ኳስ ግብ ጠባቂው ጽዮን አቋርጦበታል።

በሚያገኙት ኳስ ሁሉ በፈጣን ሽግግር የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲታትሩ የነበሩት ኃይቆቹ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተጭነው መጫወት ሲችሉ የግብ ዕድሎችንም ፈጥረው በተለይም 90+5ኛው ደቂቃ ላይ ተቀየሮ የገባው ያሬድ ብሩክ ያደረገውን ሙከራ በፍቃዱ ዓለማየሁ በግሩም ቅልጥፍና ከመስመር አስወጥቶበታል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ቡና 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በፍጻሜውም ወላይታ ድቻ ከኢትዮጵያ ቡና ይገናኛሉ።