የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ቤንች ማጂ ቡና የዕለቱ ባለድል ሆኗል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 22ኛ ሳምንት በመጨረሻ ቀን ውሎ በምድብ “ሀ” ሁለት ጨዋታዎች ተደርገው ወልዲያ ከሞጆ ከተማ ያለ ግብ ሲለያዩ ቤንች ማጂ ቡና በሰፊ ግብ ልዩነት ተጋጣሚውን አሸንፏል።

ቀዳሚ የነበረው መርሐግብር ወልዲያን ከሞጆ ከተማ አገናኝቶ ያለ ግብ 0-0 ተጠናቋል።

ብዙም ሳቢ ባልነበረው በረፋዱ ጨዋታ ወልዲያ ግብ መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን በመፍጠር የተሻለ ቢሆንም አጥቂያቸው በድሩ ኑሩሁሴን ግብ መሆን ሚችሉ አጋጣሚዎችን በተደጋጋሚ ሲያመክን ተስተውሏል። ሞጆ ከተማም በአንፃሩ ግብ ለማግባት ሙከራ ያደረጉ ሲሆን ልክ እንደ ተጋጣሚው ንፁህ ግብ መሆን ሚችሉ ኳሶችን ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። አደገኛ የሚባለውን ሙከራ ወልዲያ በ39ኛው ደቂቃ አድርገው ሚካኤል ሀሲሳ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አክርሮ የመታው ኳስ ለትንሽ ከፍ ብሎ ወጥቶበታል። ጨዋታው ሌላ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳያስመለክት ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው መነቃቃት የታየበት ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመሪያ አጋማሽ ጥሩ መንቀሳቀስ ችለዋል። ሆኖም ግን ግብ ማስቆጠር ፈፅሞ ተስኗቸዋል። በ52ኛው ደቂቃ ላይ ኃይሌ ያሻገረለትን ኳስ በድሩ ኑሩሁሴን በቀላሉ ማስቆጠር ሚችልበትን አጋጣሚ ሳይጠቀም ቀርቷል። በ85ኛው ደቂቃ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ የሞጆ ከተማው ተቀይሮ የገባው ቴዎድሮስ ንጉሡ ወደግብ መትቶት የግቡ ቋሚ መልሶበታል። በመልሶ ማጥቃት ወልዲያዎች በድሩ ኑሩሁሴን ያደረገውን ሙከራ የሞጆ ከተማው ግብ ጠባቂ መልሶበት ተመላሸ ኳስ ቢንያም ላንቃሞ አግኝቶት ወደ ግብ ሲመታው በድጋሚ ግብ ጠባቂው እንዴትም ብሎ አድኖታል። ግብ ለማስቆጠር ሁለቱም ቡድኖች ቢጥሩም ጨዋታው ያለ ግብ ለመጠናቀቅ ተገዷል።

የሳምንቱ ማሳረጊያ የሆነው መርሐግብር ቤንች ማጂ ቡናን ከኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ አገናኝቶ ቤንች ማጂ ቡና 3-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ገና ጨዋታው እንደተጀመረ በኳስ ቁጥጥር ተጋጣሚዎቻቸውን በልጠው በተደጋጋሚ ወደ ግብ መሄድ የጀመሩት ቤንች ማጂ ቡናዎች ጥሩ የሆኑበትን የመጀመሪያ አጋማሽ በማሳለፍ ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል። ኮልፌ ቀራኒዮ በአንፃሩ በዛሬው አጨዋወታቸው ደካማ ሆነው ተገኝተዋል። በ27ኛው ደቂቃ የጥረታቸው ውጤት የሆነችዋን ግብ ናትናኤል ዳንኤል አክሏል። አብዱልአዚዝ አማን በመስመር በኩል ሆኖ ያሻማትን ኳስ ናትናኤል ዳንኤል በእግሩ አክርሮ ሲመታት የኮልፌው ግብ ጠባቂ ለመመለስ ጥረት ቢያደርግም ኳሷ አልፋ ከመረብ ጋር ተገናኝታ ቤንች ማጅ ቡናን ቀዳሚ አድርጋለች። ኮልፌ ቀራኒዮ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ወደፊት በሚሄዱበት አጋጣሚ የቤንች ማጂ ቡና ተከላካዮች አስጥለው በመልሶ ማጥቃት በአንድ ለአንድ ቅብብል ሙሉቀን ተሾመ እና ሀሰን ሁሴን ተቀባብለው ለጃፈር ሙደሲር አቃብለውት ወደ ግብነት ቀይሮ ቤንች ማጂ ቡና 2-0 እየመራ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገባ ሆኗል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ኮልፌዎች ጠንከር ብለው በመግባት ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም ጥሩ የነበሩት የቤንች ማጂ ቡና ተከላካዮች ኳሶችን ሲያፀዱ ለመመልከት ተችሏል። ጨዋታውን የቀየረችዋን ሦስተኛ ግብ ቤንች ማጂ ቡና ማስቆጠራቸው ለኮልፌዎች ተስፋ ያስቆረጠች ግብ ነበረች። በ60ኛው ደቂቃ ዛሬ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ጃፈር ሙደሲር ሦስት የኮልፌን ተከላካዮች አታልሎ በማለፍ ኳስ ጨርሶ ለሀሰን ሁሴን አቃብሎት ሀሰን ሁሴን ከመረብ ጋር አገናኝቶ 3-0 እንዲመሩ አድርጓል። ጨዋታውም ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክት በቤንች ማጂ ቡና 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።