ከፍተኛ ሊግ ምድብ ‘ለ’ |  አርባምንጭ እና ቢሾፍቱ አሸንፈዋል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ “ለ” 22ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች አርባምንጭ እና ቢሾፍቱ ድል አስመዝግበዋል።

በቀዳሚው መርሐግብር ጨዋታው ጎል ያስመለከተን ገና በ30 ሰከንድ ሲሆን ጨዋታውን ያስጀመሩት አርባምንጮች ለመቀባበል ሲሞክሩ በኦሜድላ ተጫዋቾች ተነጥቀው ከበረከት በቀለ በረጅሙ የተጣለውን ኳስ ቻላቸው ቤዛ በግንባሩ ገጭቶ አመቻችቶለት ሰይፈ ዛኪር በጥሩ አጨራረስ ወደ ግብነት ለውጦታል። ከጎሉ በኋላም ኦሜድላዎች መሪነታቸውን ሊያሰፉበት የሚችሉበት አጋጣሚ አግኝተው የነበረ ሲሆን በሦስተኛው ደቂቃ ሰይፈ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

አርባምንጮች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ለማግኘት ያደረጉት ጥረት በቶሎ ተሳክቷል። 10ኛው ደቂቃ ላይ የአበበ ጥላሁንን ረጅም ኳስ በቀኝ መስመር ሳሙኤል አስፈሪ ተቆጣጥሮ ያቀበለውን ኳስ በፍቅር ግዛቸው ተቀብሎ አሻግሮት አህመድ ሁሴን በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር አርባምንጭን አቻ አድርጓል።

ጨዋታው በተመጣጠነ ሁኔታ ቀጥሎ 34ኛው ደቂቃ ላይ አርባምንጮች መሪ የሆኑበትን ጎል አስቆጥረዋል። አሸናፊ ኤልያስ ከርቀት በግራ እግሩ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂ መልሶበት የተገኘውን የማዕዘን ምት እንዳልካቸው መስፍን አሻምቶት አምበሉ አበበ ጥላሁን በግንባሩ ገጭቶ ማስቆጠር ችሏል።

ከእረፍት መልስ ኦሜድላዎች ተጠናክረው በመግባት ጫና ፈጥረው ለመጫወት ቢሞክሩም የአርባምንጭን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት መስበር ሳይችሉ የጠራ የጎል ዕድልም ሳይፈጥሩ ከእረፍት በፊት በተቆጠሩት ጎሎች ጨዋታው በአርባምንጭ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ድሉን ተከትሎ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ የተቃረበው አርባምንጭ ከተማ ከቀጣይ ጨዋታ አቻ ውጤት ካገኘ ለከርሞ ፕሪምየር ሊግ መግባቱን የሚያረጋግጥ ይሆናል።

በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ቢሾፍቱ ከተማ በተከታታይ ድል ጉዞ ላይ የነበረው ወሎ ኮምቦልቻን 1-0 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል።

በሁለቱም በኩል ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ የተመለከትንበት ቢሆንም ጎል ሊሆኑ የሚችሉ ሙከራዎችን ሳንመለከት የመጀመርያ አጋማሽ ያለ ጎል ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ ብዙ ሳይቆዩ ቢሾፍቱዎች የአሸናፊነት ጎላቸውን አስቆጥረዋል። ወሎ ኮምቦልቻዎች ለማጥቃት ወደ ፊት ባመሩበት ወቅት የነጠቁትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት ወደፊት ይዘው በመሄድ አብዱላዚዝ ኡመር በጥሩ ሁኔታ ከግራ መስመር ያመቻቸለትን ኳስ ከተከላካዮች አምልጦ የተቀበለው ዳዊት ሽፈራው በግሩም አጨራረስ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።

ከጎሉ በኋላ ወሎ ኮምቦልቻዎች ጎል ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን በተለይ 67ኛው ደቂቃ ላይ ሰኢድ ግርማ ያሻገረውን ዮናታን ኃይሉ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣበት የሚጠቀስ ነው። በመልሶ ማጥቃት በተንቀሳቀሱት ቢሾፍቱዎች በኩልም አብዱላዚዝ ኡመር ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ። ሆኖም ተጨማሪ ጎል ሳንመለከት ጨዋታው በቢሾፍቱ 1ለ0 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።