ከፍተኛ ሊግ ምድብ ‘ሀ’ | ነቀምቴ ከተማ የዕለቱ ብቸኛ ባለ ድል ሆኗል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 22ኛ ሳምንት በሁለተኛው ቀን መርሐግብሮች ዛሬ ቀጥሎ ነቀምቴ ከተማ ሲያሸንፍ ፤ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ይርጋጨፌ ቡና ነጥብ ሲጋሩ በሌላኛው መርሐግብር የጅማ አባ ጅፋር እና የስልጤ ወራቤ ጨዋታ በዝናብ ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።

ቀዳሚ በነበረው ጨዋታ ነቀምቴ ከተማን ከአዲስ አበባ ከተማ ያገናኘ ሲሆን ጨዋታውም በነቀምቴ ከተማ የ2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በመጀመሪያ አጋማሽ ፍፁም ጨዋታ በላይነት የወሰዱት ነቀምቴ ከተማዎች በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን በአንፃሩ አዲስ አበባ ከተማዎች ደግሞ ፍፁም ደካማ የጨዋታ እንቅስቃሴ ያስመለከቱበትን የመጀመሪያ አርባ አምስት አሳልፈዋል።

ነቀምቴ ከተማዎች የጥረታቸው ውጤት የሆነችውን ግብ በሰላሳ ሶስተኛው ደቂቃ አስቆጥረዋል ፤ በ33ኛው ደቂቃ ምኞት ማርቆስ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ኢብሳ በፍቃዱ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ነቀምቴ ከተማን መሪ አድርጓል።

እንዲሁም እረፍት ሊወጡ ሽርፍራፊ ሰከንዶች በቀሩበት የአዲስ አበባ ከተማው ተከላካይ ምስጋናው ፈይሳ ኳሱን ለማፅዳት ሲሞክር ኳሷን ያገኘው ምኞት ማርቆስ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ኳሷን በቀላሉ ከመረብ ጋር ማገናኘት ችሏል።

ጨዋታው ከመልበሻ ክፍል ሲመለስ አዲስ አበባ ከተማ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ጠንከር ብለው የተመለሱ ሲሆን በአንፃሩ ነቀምቴ ከተማዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በመልሶ ማጥቃት ጥሩ መንቀሳቀስ ችለዋል።

በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎችን ባስመለከተን በዚሁ አጋማሽ በ85ኛው ደቂቃ የአዲስ አበባ ከተማ ተከላካዮች ኳስ በእጅ በመንካታቸው የፍፁም ቅጣት ምት ያገኙት ነቀምቴ ከተማዎች ሶስተኛ ግብ ማስቆጠር ሚችሉበትን አጋጣሚ ተመስገን ዱባ አምክነቶታል። በዚህም ጨዋታው ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ነቀምት ከተማን አሸናፊ በማድረግ ተቋጭቷል።

ሁለተኛው ጨዋታ አስቀድሞ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን ያረጋገጠውን ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከይርጋጨፌ ቡና አገናኝቶ ያለግብ ተጠናቋል።

የ8:00 ሰዓቱ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር የታየበት ጨዋታ ሲሆን ይርጋጨፌ ቡና ካለበት ከውጤት ቀውስ ለመውጣት ጠንከር ብለው የቀረቡ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በአንፃሩ አሸናፊነታቸውን ለማጠናከር ጥሩ ቢንቀሳቀሱም ጠንካራ ሆኖ የዋለውን የይርጋጨፌ ቡናን ተከላካይ መስመር አልፎ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል።

ሁለቱም ቡድኖች ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም በተለይም ይርጋጨፌ ቡናዎች ግብ መሆን ሚችሉበትን አጋጣሚ ፈጥረው ሳይጠቀሙ ሲቀሩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎችን በአቤል ሀብታሙ አማካኝነት ቢያደርጉም በተመሳሳይ ወደ ግብነት መቀየር ተስኗቸው የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ጨዋታው ከመልበሻ ክፍል ሲመለስ ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ግብ መሆን ሚችሉ አጋጣሚዎችን ሁለቱም ቡድኖች ፈጥረው ከመረብ ጋር ኳስን ማዋሄድ ተስኗቸዋል። ይርጋጨፌ ቡና በኳስ ቁጥጥር ጥሩ ሆኖ ግብ ለማስቆጠር ተጭኖ የተጫወቱበትን ሁለተኛ አጋማሽ ቢያሳልፉም ጨዋታው ግብ ሳያስመለክት ያለ ግብ ተጠናቋል።

ሦስተኛው ጨዋታ ከቀኑ 10:00 በጅማ አባ ቡና እና በስልጤ ወራቤ መካከል ሊደረግ የነበረ ቢሆንም ሀዋሳ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል።