በኢትዮጵያ ምድብ የምትገኘው ኮትዲቯር ከዓለም ቁጥር አንዱ ብሔራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ልታደርግ ነው

ከሳምንታት በፊት ኦስትሪያ ላይ የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድንን በወዳጅነት ጨዋታ ለመግጠም ቀጠሮ ይዘው የነበሩት ዝሆኖቹ መርሐ-ግብሩን ሰርዘው ከወቅቱ የዓለም ቁጥር አንድ ጋር ለመጫወት ቀን ቆርጠዋል።

የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች ወደ 2022 ለተሸጋገረው የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለማለፍ ይረዳቸው ዘንድ የወዳጅነት ጨዋታዎቸን ለማድረግ መርሐ-ግብሮችን እያወጡ ነው። በምድብ 11 ከኢትዮጵያ፣ ኒጀር እና ማዳጋስካር ጋር የተደለደለችው ኮትዲቯርም በመስከረም ወር መጨረሻ ከናይጄሪያ አቻዋ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ ይዛ ነበር። ነገርግን የናይጄሪያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት እንዳስታወቀው ከሆነ ተጋጣሚያቸው ኮትዲቯሮች በውስጥ አሰራር ችግር ምክንያት ጨዋታውን ሰርዘዋል።

ዝሆኖቹ ምንም እንኳን ከጎረቤታቸው ጋር የሚደረገውን የወዳጅነት ጨዋታ ቢሰርዙም ከጥቅምት ወር መጨረሻ ቀናት ጀምሮ እስከ ህዳር 8 ድረስ ለሚደረጉ የአፍሪካ ዋንጫ የምድቡ 3ኛ እና 4ኛ ጨዋታዎች ለመዘጋጀት ይረዳቸው ዘንድ ከቤልጂየም ብሔራዊ ቡድን ጋር ለመጫወት ቀን ቆርጠዋል። ጨዋታውም ከ10 ቀናት በኋላ ብራስልስ ላይ ይደረጋል። በዚህ ጨዋታ ብቻ የዝግጅት ጊዜያቸውን የማይቋጩት ኮትዲቯሮች ከቤልጂየም አቻቸው ጋር ብራስልስ ላይ ከተጫወቱ ከአምስት ቀናት በኋላም ወደ ሆላንድ በማቅናት ከጃፓን ብሔራዊ ቡድን ጋር ሌላ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ ይዘዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!