“ሰሞኑን የተፈጠረውን ነገር ገምግመን የእርምት እርምጃ ወስደናል” ውበቱ አባተ

የዋልያዎቹ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከሰሞኑን በበርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ዘንድ መነጋገሪያ የነበረውን ጉዳይ አስመልክቶ ሀሳብ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከኒጀር ጋር ላለበት የምድቡ 3ኛ እና 4ኛ ጨዋታ ዝግጅቱን በካፍ የልህዕቀት ማኅከል እያደረገ ይገኛል። በነገው ዕለትም ከዛምቢያ አቻው ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል። ታዲያ ታፈሰ ሰለሞንን ጨምሮ በስብስቡ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ተጫዋቾች ከቀናት በፊት በማኅበራዊ ገፅ ላይ በለቀቁት ምስል የስፖርት ቤተሰቡ የተለያዩ ሃሳቦችን ሲሰነዝር ቆይቷል። የጉዳዩ ቀጥተኛ ባለቤት የሆነው ታፈሰ ሰለሞንም በትላንትናው ዕለት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ “በፍፁም ሆን ብዬ ያደረኩት አደለም” ብሎ ጉዳዩን አስረድቶ ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ የብሔራዊ ቡድኑን የዝግጅት ጊዜ እና የወዳጅነት ጨዋታዎቹን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ መነጋገሪያ የነበረውን ነገር አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ሀሳብ ሰጥተዋል።

“ብሔራዊ ቡድኑ የሁላችንም ነው። የሁላችንንም እርዳታ ይፈልጋል። በተለያዩ ነገሮች ሃሳቦችን የምንሰጥ ከሆነ ሀገራዊው ስሜት ይጠፋል። ስለዚህ ሀገራዊው ጉዳይ ላይ እናተኩር።

“በቡድኑ ውስጥ የሚጫወቱት ተጫዋቾች እንደ ቀልድ የሚያደርጉትን ነገር በደንብ ማወቅ አለባቸው። ምን መዘዝ እንደሚያመጣም መረዳት አለባቸው። ሰሞኑን የተፈጠረው ነገር ካለማወቅ የተፈጠረ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። ወጣትነተም ስላለ የተፈጠረ ነገር ነው። እኛም ከተጫዋቾቹ ጋር አውርተን ገስፀናቸዋል። ከዚህ በኋላ ግን እንደዚህ አይነት ነገር አይፈጠርም።

“እንደዚህ አይነት ነገሮች ከዚህ በኋላ እንዳይፈጠሩም ሁሉንም ተጫዋቾች የሚገዛ ነገር እናዘጋጃለን። በዚህ ጉዳይም ከፌዴሬሽኑ ጋር እያወራን ነው። ተጫዋቾቹ ማድረግ የሌለባቸውን ነገር በደንብ አስቀምጠን ካስረዳናቸው እና ካስተማርናቸው በኋላ ነገሮች ይቀላሉ። ከዚህ የሚያልፍ ካለም የሚወሰንበትን ነገር እንዲኖር ሁሉን አቃፊ ነገር እንዲኖር ለፌዴሬሽኑ ያዘጋጀሁትን ወረቀት አስገብቻለሁ። አሁን ላይ ግን እንደዚህ አይነት ትናንሽ ነገሮች ላይ በማውራት ጊዜያችንን አናጠፋም። ትኩረታችንን ሙሉ በሙሉ ብሔራዊ ቡድኑ ላይ አድርገን ዝግጅታችንን እንቀጥላለን። ሰሞኑን የተፈጠረውን ነገር ግን ገምግመን የእርምት እርምጃ ወስደናል።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!