ሶከር ታክቲክ | የአጨዋወት እቅድ ማዘጋጀት (…ካለፈው የቀጠለ)

አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ከተለያዩ ድረ-ገጾች ያገኛቸውን የእግርኳስ ታክቲክ ንድፈ-ሐሳቦችን የተመለከቱ ጥልቅ ትንተናዎች፣ የሥልጠና መመሪያዎች እና መጻህፍትን ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም ሌሎች አሰልጣኞችና አንባቢን ይጠቅም ዘንድ ጥቅም ላይ ለማዋል ይሞክራል፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው ፅሁፍም አንዱ አካል ነው፡፡         

ጸሃፊ – ማክስ ቤርማን
ትርጉም
– ደስታ ታደሰ

                  የጨዋታ ሒደት ሽግግሮች

                  ★ የማጥቃት ሽግግር

– የተጋጣሚ ቡድን የመከላከል አደረጃጀትን መፈተን

በጨዋታ ወቅት በርካታ ግቦች ከሽግግር ቅፅበቶች እንደመቆጠራቸው በማጥቃት ሒደት ተጋጣሚ ቡድን የመከላከል አደረጃጀቱን ለመጠበቅ ስለሚጥር የቡድኑ መነሻ ቅርፅ ምን እንደሚመስል በአግባቡ ማጤን ተገቢ ነው፡፡ለምሳሌ፦ በተጋጣሚ ቡድን የኋላ መስመር ላይ የሚኖርን ክፍተት ለይቶ ማጸቅ ወደ ባላጋራ የግብ ክልል በቀላሉ ለመድረስ ያግዛል፡፡ አስቀድሞ እንደተገለጸው የማጥቃት ሽግግር በጨዋታ ላይ ከሚታይ የቡድኖች የመከላከል ሒደት ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው፡፡ ስለዚህ በጨዋታ ወቅት በመከላከል ሒደት ላይ የሚገኝ ቡድን ሁሉም ተጫዋቾች የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ከተገኘ በአግባቡ መጠቀም እንዲቻል ጥሩ አቋቋም ላይ መገኘታቸውን እርግጠኛ መሆን ይገባል፡፡ ለዚህ እቅድ በጥሩ ምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችለው ወደ ተጋጣሚ ቡድን ተጠግተው የሚያጠቁ የመስመር  ተከላካዮችን ለያዘ ቡድን በ4-5-1 ከመጫወት ይልቅ 5-4-1 ፎርሜሽንን መጠቀም የተሻለ ነው፡፡ ከታች በቀረበው ምስል የዎልቨርሃምፕተን ቡድን በመከላከል ሒደት የ5-4-1 አሰላለፍ ይዞ ማንችስተር ሲቲን በዚሁ ዘዴ ሲከላከል እናያለን፡፡ የቡድኑ የመስመር አማካዮች የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾችን እግር በግር ተከታትሎ መከላከል አያስፈልጋቸውም፡፡ ይህም  ወልቨርሃምፕተን ለመልሶ ማጥቃት የተዘጋጁ ሦስት ተጫዋቾች ከፊት እንዲኖሩት አድርጓል፡፡

ምንም እንኳ 5-4-1 መከላከል ላይ ያተኮረና የማጥቃት ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ደካማ ፎርሜሽን ቢመስልም ለመልሶ-ማጥቃት ግን የተሻለ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያትም ሁለቱ የክንፍ ተጫዋቾች የተጋጣሚ ቡድን የመስመር ተከላካዮችን የማጥቃት እንቅስቃሴ ስለሚገድቡ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የመስመር አጥቂዎቹ ወደፊት ተጠግተው የሚጫወቱበት ክልል ያስገኝላቸዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህ አጥቂዎች ቡድናቸው ከተጋጣሚ ላይ ኳስ እንደነጠቀ ከባላጋራቸው ተከላካዮች ጀርባ ያለውን ክፍት ቦታ በፍጥነት ለማጥቃት ተዘጋጅተው ይጠብቃሉ፡፡

               ★የመከላከል ሽግግር

የተጋጣሚ ቡድን መልሶ-ማጥቃትን መከላከል

የመከላከል ሽግግር ተጋጣሚ ቡድን ጎል እንዳያገባ ለመከላከል በጣም ወሳኝ የጨዋታ ሒደት ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ የተጋጣሚ ቡድን ‹የፕረሲንግ› አጨዋወት እና የመልሶ ማጥቃት አወቃቀርን ማጥናት የራስን ቡድን የተከላካይ ክፍል በአግባቡ ለማዘጋጀት ይረዳል፡፡ የተጋጣሚ ቡድንን የመልሶ-ማጥቃት ስልት ካጠናን በኋላ በሽግግር ጊዜ የሚከሰተውን አደጋ ለማክሰም የሚረዳ አቀራረብን ማሰብ ያስችለናል፡፡ የተጋጣሚ ቡድን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወትን በጥሩ ሁኔታ ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ ታክቲካዊ ሥልቶችን የሚዳስስ ጽሁፍ ባልደረባችን ፖል ስሚዝ በመጽሄታችን የ2019 የመስከረም ዕትም ላይ አውጥቶ ነበር፡፡ ከታች የቀረበው ምስልም በወቅቱ የአርስናል የተከላካይ ክፍል በተጋጣሚ ቡድን አጥቂዎች ላይ የቁጥር ብልጫ የሚያስገኝ የ<<3-2>> ቅርፅ እንደሚጠቀም እናያለን፡፡

ከላይ በቀረበው ምስል የአርሰናል ቡድን ሁለት አጥቂዎችን በማጥቃት ሲሶው ከሚያቆም ቡድን ጋር ሲጫወት በመከላከል ሂደት ላይ <<3-2>> ቅርፅን ይጠቀም ነበር፡፡ ሦስቱ ተከላካዮች ጥንዶቹን የባላጋራ አጥቂዎች በቁጥር በልጠው ይከላከላሉ፡፡ የመሐል ተጫዋቾቹ ደግሞ የተጋጣሚያቸውን አማካዮች ይከላከላሉ፡፡

በአጠቃላይ ከተጋጣሚ ቡድን አጥቂዎች አንጻር በቁጥር የሚበልጡ ተከላካዮችን በመከላካል ወረዳ ላይ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ከኳስ ርቀው ያሉት ተከላካዮች በዚህ ቅጽበት ሃላፊነታቸውን በመረዳት በተጋጣሚ ቡድን የማጥቃት ተጫዋቾች እና በራስ የግብ ክልል መካከል ያለውን ክፍተት ለመዝጋት የሚያስችላቸው ቦታ ላይ መገኘት አለባቸው፡፡


የጽሁፉ ተርጓሚ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል፡፡ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፂዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡