ከፍተኛ ሊግ | ቡታጅራ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ሾመ

የከፍተኛ ሊጉ ክለብ ብታጅራ ከተማ ካሊድ መሐመድን በዋና አሰልጣኝነት ሾሟል፡፡

የተሰረዘውን የውድድር አመት በከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ ተደልድሎ እየተወዳደረ የነበረው እና ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመግባት ሰፊ ዕድል ከነበራቸው ቡድኖች መካከል የነበረው ቡታጅራ ከተማ በኮቪድ 19 እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ በአሰልጣኝ አሥራት አባተ ሲመራ የነበረ ሲሆን አሰልጣኙ ዘንድሮ ከክለቡ ጋር ለመቀጠል ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝነት ጥሪ የቀረበላቸው በመሆኑ ከክለቡ ጋር ተለይተዋል። በምትኩም ክለቡ እንደ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና እና ገብረክርስቶስ ቢራራን አይነት አሰልጣኞችን ለመቅጠር ንግግር ቢያደርግም አሰልጣኝ ተመስገን ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ደርሶት፣ ገብረክርስቶስ ደግሞ በግል ጉዳይ ክለቡን መያዝ ባለመቻላቸው አማራጩን ወደ ሌሎች አሰልጣኞች በማዞር አሰልጣኝ ሰብስቤ ይባስ እና ካሊድ መሐመድን ከተመለከተ በኃላ ካሊድ መሐመድን በዋና አሰልጣኝነት ለአንድ ዓመት መቅጠሩን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ የላከው መረጃ ይጠቁማል፡፡

የቀድሞው ድንቅ ተጫዋች ወደ አሰልጣኝነቱ ከመጣ ወዲህ ኢትዮጵያ ቡናን በረዳት እና በዋና አሰልጣኝነት፣ በዳሽን ቢራ፣ መድን እና ዓምና እስከ ዓመቱ አጋማሽ በሀላባ ከተማ ሠርቷል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!