ክለብ ያላገኙ ተጫዋቾች ጉዳይ በፌዴሬሽኑ ስብሰባ ላይ ሊታይ ነው

በወቅታዊ ችግር ምክንያት ክለብ አልባ ሆነው የተቀመጡ ተጫዋቾች ጉዳይ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ አባላት በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ሊታይ ነው።

መቀመጫቸውን ትግራይ ክልል ያደረጉት መቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ እና ሱሑል ሽረ በወቅታዊ ጉዳይ ምክንያት ዘንድሮ ከቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድር እየተሳተፉ እንዳልሆነ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት የሦስቱ ክለብ ተጫዋቾች የነበሩ እና የዝውውር መስኮቱ ሳይዘጋ ወደ ሌላ ክለብ ሄደው እንዲጫወቱ የተለየ የዝውውር ደንብ ፌዴሬሽኑ በማዘጋጀቱ ይህን ዕድል በመጠቀም ከአስራ አምስት የሚበልጡ ተጫዋቾች ወደ ተለያዩ ክለቦች በማምራት በአሁን ሰዓት እየተጫወቱ ይገኛል።

ሆኖም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የመቐለ፣ ወልዋሎ እና ሽረ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮቱ ከተዘጋ በኃላ ችግሩ ከተፈጠረበት የትግራይ ክልል ዘግይተው ወደ የአካባቢያቸው በመለሳቸው ምክንያት ወደ የትኛውም ክለብ ሄደው መጫወት የማይችሉበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። በግል ጥረታቸው ወደ ተለያዩ ክለቦች ሄደው ለመጫወት ቢያስቡም አብዛኛው ክለቦች “ሞልተናል” በማለት ምላሽ እየሰጧቸው ይገኛል።

ይህ ሁኔታ ያሳሰባቸው ተጫዋቾቹ “የቤተስብ ኃላፊነት አለብን፤ በቀድሞ ክለባችን አስቀድሞ ያልተከፈለን የወራት ደሞዝ አለ። ይህ ችግር ተፈጥሮ በድጋሚ ደግሞ ሥራ ፈትተን መቀመጥ የበለጠ ችግር ውስጥ የሚከተን በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ልዩ ትኩረት ሰጥቶን ክለቦች ከሚይዙት የተጫዋቾች ኮታ በተለየ ሁኔታ አዲስ ደንብ ወጥቶ ከፍ አድርገው እንዲይዙ በማድረግ ወደ ተለያዩ ክለቦች ሄደን የምንጫወትበት ዕድል እንዲመቻች እንጠይቃለን።” ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።

ይህን ተከትሎ ነገ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ አባላት ከረፋዱ 04:00 ጀምሮ በሚያደርገው ስብሰባ ይህን ጉዳይ በማጤን አንድ ውሳኔ ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ