ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ወላይታ ድቻ

የፋሲል እና ድቻን ጨዋታ የመለከቱ ነጥቦችን እነሆ።

የመጀመሪያውን ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ የሚገቡት ፋሲሎች ከሦስተኛ ሳምንት ጨዋታቸው ከውጤት ባሻገር ብዙ መልካም ነገሮችን አግኝተዋል። በተለይም ቡድኑ ላይ የታየው የአሸናፊነት መንፈስ እና ትጋት ለነገው ጨዋታ ግብአት የሚሆን ነው። በተነጣል ካየነውም የሽመክት ጉግሳ ድንቅ አቋም ላይ መገኘት እርሱ ከሚገኝበት መስመር ብቻ ሳይሆን መሀል ለመሀልም ቡድኑ የተዋጣለት ጥቃት እንዲመሰርት በር የከፈተ ነበር። የሳሙኤል ዮሃንስ ብቃትም ቡድኑ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ሊያካትተው የሚችል ብቁ አማራጭ ስለማግኘቱ ምልክት የሰጠ ነበር። እነዚህ እና ሌሎች ጠንክልራ ጎኖቹ በዘላቂው ውጤቱ ላይ ቀጣይነት ያለው በጎ መነሻ መሆናቸውን ለማሳየት ግን እንደነገው ዓይነት ጨዋታዎች ላይ ደግሞ ማሳየት ይጠይቃል። የኳስ ቁጥጥር ፍጥጫ ሊኖር በሚችልበት በዚህ ጨዋታም አፄዎቹ እንደጅማው ጨዋታ መሀል ለመሀል በሚከፍቱት ጥቃት በፍጥነት ቅብብሎችን በመከወን ጎል ላይ የመድረስ አቅማቸውን አውጥተው ከተጠቀሙ ነጥብ የማግኘት ዕድላቸው የሰፋ ነው። ለጨዋታው ከሚጠቀመው ስብስብ አንፃር የአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ቡድን ከሰዒድ ሁሴን እና ሀብታሙ ተከስተ ጉዳት ውጪ የሚያጣው ሌላ ተጫዋች እንደሌለ ሰምተናል።

በርካታ ጠንካራ ጎኖቹን አጥቶ በወልቂጤ ከተማ ሽንፈት ያስተናገደው ወላይታ ድቻ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ከባድ ፍልሚያ ይጠብቀዋል። በመሆኑም በአዳማው ጨዋታ ላይ የነበረውን ጠንካራ ስነ ልቦና እና የግብ ዕድሎችን በቶሎ ተጠቅሞ ጨዋታን የማረጋጋት አካሄዱን መልሶ ማግኘት ይኖርበታል። በተለይም ከኳስ ውጪ ቡድኑ በሜዳው ቁመት ያሚኖረውን ጥቅጥቅነት በሚያጣበት ወቅት ለተጋጣሚ አማካይ ክፍል ቀላል ሆኖ መታየቱ ነገም የነሱራፌል ዳኛቸው ቀጥተኛ ኳሶች ሰለባ ሊያዳርገው ይችላል። ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል መግቢያ ላይ በአማካይ ክፍሉ እና በፊተኛው አጥቂ መሀል የሚከወኑ ቅብብሎች ጥራት መውረድም ቡድኑ አሻሽሎት ሊመጣ እንደሚችል የሚጠበቅ ሌላው ደካማ ጎኑ ነው። ከዚህ ውጪ ከጠንካራው የፋሲል የኋላ ክፍል ጀርባ ለመገኘት ከአዳማ ጋር በነበረው መልኩ የፊት አጥቂው ስል ሆኖ መገኘት እና የግብ አስቆጣሪነት ኃላፊነቱም ለሌሎች ተሰላፊዎች ጭምር መካፈል ይኖርበታል። ወላይታ ድቻ በነገው ጨዋታ ፍኒያንስ ተመስገን ፣ ያሬድ ዳንሳ እና እዮብ ዓለማየሁን ከጉዳት መልስ ሲያገኝ ቅጣቱን የጨረሰው አናጋው ባደግ ግን ልምምድ ላይ በገጠመው መጠነኛ ጉዳት ምክንያት የመሰለፉ ነገር እርግጥ አልሆነም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ6 ጊዜያት ሲገናኙ አቻ በማያውቀው ግንኙነታቸው ተመጣጣኝ ሪከርድ አላቸው። ሁለቱም ክለቦች እኩል 3 ጊዜ ሲሸናነፉ ወላይታ ዲቻዎች 7 ፣ ፋሲል ከነማዎች ደግሞ 6 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ

እንየው ካሳሁን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

በዛብህ መለዮ – ይሁን እንዳሻው – ሱራፌል ዳኛቸው

ሽመክት ጉግሳ – ሙጂብ ቃሲም – ሳሙኤል ዮሀንስ

ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)

ሰዒድ ሀብታሙ

ፀጋዬ አበራ – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ – መሳይ አገኘሁ

በረከት ወልዴ

እዮብ በቀታ – ኤልያስ አህመድ – እንድሪስ ሰዒድ – ቸርነት ጉግሳ

ስንታየሁ መንግሥቱ


© ሶከር ኢትዮጵያ