የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 0-1 ሀዲያ ሆሳዕና

ሀዲያ ሆሳዕና ድሬዳዋን 1-0 ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

ፍሰሀ ጥዑመልሳን – ድሬዳዋ ከተማ

ስለጨዋታው

” በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተመለከትኩት ነገር ቀድመህ ከተጠቀምክ ታሸንፋለህ። መጀመሪያ ላይ የእኛ የፊት አጥቂ ያገኛቸውን አጋጣሚዎች ቢጠቀም ኖሮ አሸንፈን እንወጣ ነበር። ከዛ በኃላ የነበረው ጨዋታ ሰዓት ገደላ እና መውደቅ ነበር። ስለዚህ ምንም ማድረግ አልቻልንም ተሸንፈናል።”

በተከታታይ ሽንፈት ጫና ውስጥ ስለመግባቱ

“ያው እንደምታየው ነው ሁሌም ከሽንፈት ለመውጣት እጅግ ከባድ ነው። ልጆቹ ጫና ውስጥ ስላሉ ነው ዕድሎችን እየሳቱ ያሉት። ቀድመን በገዛ ስህተታችን በሰራነው ስህተት ግብ አስተናገደናል። ከዛ በኃላም ወደ ጎል መድረስ ብንችልም በቀሩት ደቂቃዎች ሰዓት በማባከን ተሸንፈን ልንወጣ ችለናል።”

ስለባከኑ የግብ ዕድሎች

“ሁልጊዜም ቢሆን ያገኘናቸውን ዕድሎች መጠቀም ላይ ክፍተቶች አሉብን። ዕድሎችን ባመከንን ቁጥር እንደ ቡድን የመውረድ ነገር አለ። በቀጣይ ይህን ለመቅረፍ መሥራት ይኖርብናል።”

አሸናፊ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና

ጨዋታውን በጥንቃቄ ስለመቅረባቸው

“ሜዳ ላይ ስንቆም 4-2-3-1 ይምሰል እንጂ ሜዳ ላይ ስንከላከል እና ስናጠቃ የተለያዩ መንገዶችን ነው የምንጠቀመው። ኳስ ስናገኝ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በአራት አጥቂ ነው የምንጫወተው፤ ኳስ ስናጣ ደግሞ በ5-4-1 ቅርፃችን እንለውጣለን። ስለዚህ በታክቲካል ዲሲፕለን የተሞላ በቀላሉ ግብ እንዳይቆጠርብን የተንቀሳቀስንበት ጨዋታ ነበር።”

በ63ኛው ደቂቃ ስለተደረጉ ቅያሬዎችና ያስገኙት ውጤት

“የምፈልገው ደረጃ ባይሆንም ፎፋናን ጨምሮ ሌሎች ተጫዋቾች ባለፈው ጨዋታ ጉዳት ላይ ነበሩ። ታድያ እነዚህን ተጫዋቾን ጠብቀህ የማታጫውታቸው ከሆነ በቀጣይ ጨዋታዎች ከፍተኛ ጉዳት ነው ያለው። ከዚህ አንፃር ከሁለቱም ተጫዋቾች የምፈልገውን አግኝቻለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ