ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አጀማመሩ ያላማረው አርባምንጭ በድል አንደኛውን ዙር አጠናቋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የዘጠነኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን አርባምንጭ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲን ያገናኘው ጨዋታ አርባምንጭን ባለ ድል አድርጓል፡፡

የአርባምንጭ ከተማ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ መሻሻል የታየበት እና የአቃቂ ቃሊቲ መዳከም የተስተዋለበት ይህ ጨዋታ በመጀመሪያው አስራ አምስት ደቂቃዎች አቃቂ ቃሊቲዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥሮ ቢኖራቸውም ደቂቃ እየገፋ ሲሄድ እየወረዱ መሄዳቸው ለአርባምንጮች ፈጣን የሽግግር አጨዋወት መልካም መንገድን የከፈተላቸው ሆኗል፡፡ ትደግ ፍሰሀ ከኪፊያ አብራህማን መሀል ለመሀል የተሰጣትን ኳስ በቀጥታ መምታት እየቻለች በቀላሉ ሳትጠቀምበት በቀረችበት አጋጣሚ አቃቂዎች በሙከራ ቀዳሚ ረገድ ቀዳሚ መሆን ችለው ነበር።

አርባምንጮች በሰናይት ባሩዳ እና ሜሮን አማካኝነት የሚያገኙትን ኳስ ወደ መስመር ቶሎ ቶሎ ሲያሻግሩ የታየ ሲሆን ይህም አጨዋወታቸው ወደ ውጤታማነት አሸጋግሯቸዋል፡፡ ሰርካለም ባሳ በተደጋጋሚ በቀኝ በኩል ሰብራ ለመግባት ጥረት ስታደርግ የነበረች ሲሆን 7ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ በኩል አጠገቧ ለነበረችሁ ሰናይት ባሩዳ ስትሰጣት ተጫዋቿም ነፃ አቋቋም ለነበረችሁ ድርሻዬ መንዛ አሳልፋላት አጥቂዋም ወደ ጎል ቀይራው አርባምንጭን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡ ከጎሉ መቆጠር በኃላ አስናቀች ትቤሶ ካደረገችው የቅጣት ምት ሙከራ ውጪ ተጨማሪ ነገር ሳንመለከት ለእረፍት አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ አቃቂዎች በእንቅስቃሴ የተሻሉ የነበሩ ቢሆኑም ጨራሽ የሚባሉ አጥቂዎችን በስብስቡ ውስጥ ባለማካተቱ ያገኟቸውን ዕድሎች መጠቀም አልቻሉም፡፡ በአንፃሩ አርባምንጮች ወደ መከላከሉ አመዝነው በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ቢጥሩም በዚህኛው አጋማሽ ጎሎችን ሳንመለከት በአቃቂ የጨዋታ ብልጫ በአርባምንጭ ከተማ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡


ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ሰናይት ባሩዳ ከአርባምንጭ ከተማ የልሳን የሴቶች ስፖርት የጨዋታ ምርጥ ተብላ ተሸልማለች፡፡

በኮቪድ 19 ወቅት የምንገኝ እንደመሆኑ ይህን በሽታ ለመከላከል እና በስታዲየሞች አካባቢ እንዳይስፋፋ ለማድረግ የሀዋሳ ከተማው የህክምና ባለሙያ ዘሪሁን ዳዊት በግል ጥረቱ የፀረ ተዋህስያን መድሀኒት ሲረጭ መስተዋሉ ሊበረታታ እና ሊመሰገን የሚገባው መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ