የአሠልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 3-4 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከ9 ሰዓቱ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የቡድኖቹ አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

ማሒር ዴቪድስ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለ ጨዋታው?

ጥሩ የመጀመሪያ አጋማሽ ነበረን። በጨዋታው ቀድመን ግብ አስተናግደን ነበር። ነገርግን በጥሩ ሁኔታ በቶሎ ወደ ጨዋታው ተመልሰናል። ኳሶችን በመያዝ እና ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስም የተሻልን ነበርን። በአጠቃላይ ግን በጨዋታው ጥሩ ነበርን።

ቡድኑ ሦስት ግቦችን ስላስተናገደበት መንገድ?

ከአምሮ ጋር የሚያያዝ ይመስለኛል። አራት ግቦችን ማስቆጠራችን ጉልበታችንን ቆጥበን እንድንጫወት ያደረገን ይመስለኛል። እንደ ተመሪ ቡድን በሙሉ ሀይል እና የማጥቃት ፍላጎት በሁለተኛው አጋማሽ አልተጫወተንም።

ስለ ቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ?

ጥሩ ነው። ጎሎች በተለያዩ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች እየተቆጠሩ ነው። ተቀይረው ወደ ሜዳ የገቡት ተጫዋቾቻችንም እንደነ ጌታነህ እና አማኑኤል ግብ ማስቆጠራቸው አይቀርም።

ስለ ቀጣዩ የፋሲል ጨዋታ?

የሦስት ነጥብ ጨዋታ ነው። አሁን ላይ በቶሎ የማገገሙ ጉዳይ ላይ ነው የምንሰራው። ከእሁዱ ጨዋታ በፊትም በቶሎ ድካማችንን አራግፈን ለጨዋታው እንዘጋጃለን።

ደግአረ ይግዛው – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው?

በመጀመሪያ ይዘነው የገባነውን አጨዋወት ለመተግበር ተጫዋቾቼ የነበራቸው ነገር ደስ የሚል ነበር። ግን ጎል ካገኘን በኋላ ያንኑ ነገር ማስቀጠል ሲገባን አልቀጠልንበትም። በተለይ ግን በአንዳንድ የመከላከል አደረጃጀታችን ስህተቶች እንዲሁም ተጫዋቾቻችን ላይ በነበረ የሰሩትን ነገር ያለማመን ችግር ክፍተት ነበረብን። እነሱ ኳሶችን ወደ መስመር አውጥተው መጫወት እንደሚፈልጉ ከዚህ ቀደም በነበሯቸው ጨዋታዎች አይተናል። በዚህም የእነሱን የመስመር ላይ እንቅስዋሴ ተቆጣጥረን በቶሎ ለማጥቃት የሚያስችሉን ተጫዋቾችን ነበር በቋሚነት የተጠቀምነው። ነገርግን ባሰብነው መንገድ ጨዋታውን መቆጣጠር አልቻልንም። ግቦቹም የተቆጠሩበት መንገድ በጥቃቅን ስህተት ነው። የጎሎቹም መቆጠር ተጫዋቾቻችን ላይ ጫና አሳድሯል። ወደ ጨዋታው ለመመለስ ብንጥርም ጥረታቸን ከረፈደ በመሆኑ ምንም ማድረግ አልቸልንም።

ስለ ቡድኑ የአንደኛ ዙር ድክመት?

እንደምታቁት ውድድሩ በአራት ቀን ልዩነት ጨዋታዎች የሚደረጉበት ነው። ለዚህ ደግሞ በአካልም ሆነ በአምሮ ዝግጁ ሆነን መቅረብ አለብን። በሜዳ ላይ ያለን ነገር ጥሩ ነው። ኳሶችን የምንጀምርበት መንገድም ጥሩ ነው። ነገርግን ከዚህ የበለጠ ኳሶችን የማስቀጠል ነገር ላይ መስራት አለብን። በተጨማሪም ቡድናች በጉዳት እና በቅጣት ተጫዋቾችን እያጣ ነው ያለው። ዛሬ እንኳን ጀማልን ማጣታችን ትልቅ አስተዋዕኦ አድርጓል። በመጫወት ብቻ ሳይሆን ቡድኑን በመምራት ይጠቅመን ነበር። በዚህ አጋጣሚ የአወዳዳሪው አካል የአንደኛውን ዙር በደንብ ገምግሞ ለሁለተኛ ዙር የሚስተካከልበት መንገድ ቢፈጠር ጥሩ ነው። በአጠቃላይ ግን በውድድሩ ያየነውን ድክመት ለማስተካከል ጠንክረን እንሰራለን።

በሁለተኛ ዙር ስላሰቡት ነገር?

በአንደኛ ዙር የተመዘገበውን የነጥብ ልዩነት በሁለተኛ ዙር መቀልበስ የማይቻልበት ዕድል የለም። በውድድሩ ወጥ የሆነ እንቅስቃሴ የማሳየት እና ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ መቅረብ ነው ፍላጎታችን። ስለዚህ በእያንዳንዱ ጨዋታ ውጤት ይዘን ለመውጣት እየሰራን ነው። ከፊታችን ባሉት 12 ጨዋታዎች ብዙ ነገሮች መለወጥ ይችላሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ