ሪፖርት | ፈረሰኞቹ ሠራተኞቹን አሸንፈዋል

ሰባት ግቦች የተቆጠሩበት የወልቂጤ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በጊዮርጊስ 4-3 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በጉዳት እና ተለያዩ ምክንያቶች በርካታ ተጫዋቾችን ያጡት ወልቂጤ ከተማዎች ከቀናት በፊተ በሰበታ ከተማ ከተሸነፉበት ጨዋታ አራት ተጫዋቾችን ለውጠዋል። በዚህም ጅማል ጣሰውን በጆርጅ ደስታ፣ ይበልጣል ሽባባውን በተስፋዬ ነጋሽ ፣ ሀብታሙ ሸዋለምን በዳግም ንጉሴ እንዲሁም ፍሬው ሰለሞንን በያሬድ ታደሰ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በአሠልጣኝ ማሂር ዴቪድስ የሚመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው በአዳማ ላይ ወሳኙን ድል ካገኙበት ቡድን አስቻለው ታመነን በፍሪምፖንግ ሜንሱ ብቻ ተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል።

የሚያገኟቸውን ኳሶች በፍጥነት በመቀባበል የጊዮርጊስ የግብ ክልል በመድረስ ጨዋታውን የጀመሩት ወልቂጤዎች ገና በጊዜ ግብ አስቆጥረው መሪ ሆነዋል። በዚህም በ8ኛው ደቂቃ ራሱን ነፃ አድርጎ ቆሞ የነበረው ተስፋዬ መላኩ ከአቡበከር የተቀበለውን ኳስ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። በተቃራኒው ገና በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ግብ ያስተናገዱት ጊዮርጊሶች የማጥቂያ መስመራቸውን በግራ መስመር በኩል (በአብዱልከሪም እና አማኑኤል) በማድረግ የወልቂጤዎችን የግብ ክልል መጎብኘት ይዘዋል።

በ15ኛው ደቂቃ የአቡበከር ሳኒን ስህተት በጥሩ ቅልጥፍና ተቀብሎ ወደ ግብ የደረሰው የግራ መስመር ተከላካዩ አብዱልከሪም መሐመድ ግብ ጠባቂው ጆርጅ ደስታን አልፎ ወደ ግብ የመታው ኳስ ወደ ግብነት ሊቀየር ተቃርቦ ስህተቱን ቀድሞ የሰራው አቡበከር በፍጥነት ደርሶ ኳሱ ወደ ገብነት እንዳይቀየር አድርጓል። ወደ ጨዋታው ቶሎ ለመመለስ አሁንም ጥረታቸውን የቀጠሉት ጊዮርጊሶች በ28ኛው ደቂቃ የተገኘን የቅጣት ምት በቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ አማካኝነት ወደ ግብነት ቀይረውት አቻ ሆነዋል።

በጨዋታው ጥሩ ተነሳሽነት የነበረው እና በጨዋታው ቡድኑን አቻ ያደረገው ጌታነህ በ36ኛው ደቂቃ አቤል ያለው ያሻገረውን የመዓዘን ምት በግንባሩ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ አድሯል። ከመመራት ተነስተው መሪ የሆኑት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሙሉ ሀይላቸው ማጥቃታቸውን ቀጥለው ሁለተኛ ግባቸውን ካስቆጠሩ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ሌላ ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም አማኑኤል ወደ ግብ የመታውን ኳስ ተከላካዮች በሚገባ ማውጣት ሳይችሉ የተመለሰውን ኳስ በጥሩ ቦታ ላይ የነበረው አቤል እንዳለ አግኝቶ የቡድኑን ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል።

በጨዋታው ጅማሮ ያገኙትን መሪነት ማስጠበቅ ያልቻሉት ወልቂጤዎች የጊዮርጊስን ጥቃት መመከት ሳይችሉ በተቆጠረባቸው ተከታታይ ሦስት ግቦች እየተመሩ አጋማሹ ተገባዷል።

ከደቂቃ ደቂቃ እየተሻሻሉ የመጡት ፈረሰኞቹ የሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በሁለት ደቂቃዎች ውስጥ ግልፅ የግብ ማግባት ዕድል ፈጥረው መክኖባቸዋል። በዚህም ለዓለም ብርሃኑ በረጅሙ የመታውን ኳስ የወልቂጤው የመሐል ተከላካይ ዳግም ንጉሴ ማፅዳት ተስኖት የተገኘውን ኳስ ጌታነህ ከበደ በጥሩ ቅልጥፍና ግብ ጠባቂውን አልፎ የሞከረው ኳስ የግቡ ቋሚ መልሶታል። ባልተለመደ ሁኔታ በሚሰሯቸው የመከላከል ስህተቶቸ በጨዋታው ተጋልጠው የታዩት ወልቂጤዎች በ50፣ 51 እና 57ኛው ደቂቃ በያሬድ ሔኖክ እንዲሁም አብዱልከሪም አማካኝነት በሞከሩት ኳስ ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል።

ጨዋታው በሚፈልጉት መንገድ እየተጓዘላቸው የሚገኘው ጊዮርጊሶች በ55ኛው ደቂቃ ሌላ ግብ አስቆጥረው መሪነታቸውን ወደ አራት አሳድገዋል። በዚህ ደቂቃም በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አብዱልከሪም ከጌታነህ የተቀበለውን ኳስ ከሳጥን ውጪ በመምታት ጎል አስቆጥሯል።

የማጥቃት ሀይላቸውን ለማጠናከር ለውጦችን ማድረግ የጀመሩት ወልቂጤዎች በ61ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል። በዚህም ረመዳን ከግራ መስመር ለሔኖክ ያሻገረውን ኳስ ለመመለስ ሲጥር የነበረው የጊዮርጊሱ የግብ ዘብ ለዓለም ብርሃኑ ኳሷን በሚገባ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ በራሱ ላይ ግብ አስቆጥሯል።

አራት ግቦችን አስቆጥረው ከጨዋታው የሚፈልጉትን ያገኙ የሚመስሉት ጊዮርጊሶች የሁለተኛው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ጫናዎች በስተውባቸው ከኳስ ውጪ በርካታ ደቂቃዎችን አሳልፈዋል። በተለይ ወልቂጤ ከተማዎች የተጫዋች እና የአጨዋወት ለውጥ አድርገው ጥቃቶችን ሰንዝረዋል። በዚህም በ87ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በገባው አህመድ ሁሴን የቅጣት ምት ጥሩ ለግብነት የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመሩት አራት ደቂቃዎች ማብቂያ ላይ የመዓዘን ምት ያገኙት ወልቂጤዎች የተገኘውን የመዓዘን ምት አሻምተውት ሲመለስ በአሜ አማካኝነት ጥሩ ኳስ ወደ ጎል መተው በጨዋታው ጥሩ ጊዜን ያላሳለፈው ለዓለም ኳሱ የግቡን ቋሚ ገጭቶ ሲመለስ ባለመቆጣጠሩ ሁለተኛ የራሱ ላይ ግቡን አስቆጥሮ ወልቂጤዎች የጨዋታውን የመጨረሻ ግባቸውን አግኝተዋል። ጨዋታውም ተጠናቆ ቅዱስ ጊዮርጊሶች 4-3 አሸንፈዋል።

ውጤቱን ተከትሎ በጨዋታው ሦስት ነጥብ ያገኙት ጊዮርጊሶች ያገኙትን ነጥብ ወደ 24 ከፍ አድርገው ያሉበት 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በተቃራኒው አራት ግቦችን በጨዋታው አስተናግደው የተረቱት ወልቂጤዎች በ16 ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ