ወልቂጤዎች አማካይ አስፈርመዋል

በአሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመሩት ወልቂጤ ከተማዎች የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ማስፈረማቸው ታውቋል።

የአንደኛውን ዙር የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ደረጃን በመያዝ ያገባደዱት ወልቂጤ ከተማዎች በሁለተኛው ዙር የሊጉ ውድድር ተጠናክሮ ለመቅረብ ትናንት የተከፈተውን የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት መጠቀም ጀምረዋል። በዚህም የአማካይ መስመር ተጫዋች ጅብሪል ናስርን ማስፈረማቸው ተረጋግጧል።

የቀድሞ የደደቢት፣ ጅማ አባ ቡና፣ ሻሸመኔ ከተማ፣ ጉለሌ ክፍለ ከተማ እና ሰበታ ከተማ ተጫዋች የነበረው ጅብሪል በየጨዋታው ተለዋዋጭ የጨዋታ መንገድ ለመከተል የሚሞክረውን ወልቂጤን ተቀላቅሏል። ማክሰኞ ለቡድኑ መሰለፍ የሚችል ከሆነም በመጀመርያ ጨዋታው ታናሽ ወንድሞቹ ሬድዋን ናስር እና አቡበከር ናስርን በተቃራኒ መለያ የሚገጥም ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ