አዳማ ከተማ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን አስፈረመ

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን የሾመውና ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት አልሞ ዝውውር እያደረገ የሚገኘው አዳማ ከተማ ተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

ኤልያስ አሕመድ ከፈራሚዎቹ መካከል ነው። የቀድሞው የሰበታ ከተማ፣ ባህር ዳር ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር አማካይ በዚህ የውድድር ዓመት ወደ ወላይታ ድቻ በማምራት ግማሽ ዓመት ያሳለፈ ሲሆን ከቀናት በፊት ከክለቡ ጋር ተያይቶ ወደ አዳማ ከተማ አቆንቷል።

ያሬድ ብርሀኑ ሌላው የአዳማ አዲስ ተጫዋች ነው። ከትራንስ ኢትዮጵያ ቢ ቡድን ከተገኘ በኋላ በደደቢት፣ ወልዲያ እንዲሁም በሁለት አጋጣሚ ለመቐለ 70 እንደርታ መጫወት የቻለው ይህ ፈጣን ተጫዋች መቐለን በተሰረዘው የውድድር አጋማሽ ከለቀቀ በኃላ ለወልዋሎ ለመጫወት የተስማማ ቢሆንም ክለቡ በፕሪምየር ሊጉ አለመሳተፉን ተከትሎ ጥቂት ወራት ካለ ክለብ ከቆየ በኃላ አዳማ ከተማን ተቀላቅሏል።

ሁለቱን ጨምሮ ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾችን የቀላቀለው አዳማ ከተማ በቀጣይ ከስምንት ተጫዋቾች ጋር ይለያያል ተብሎ ይጠበቃል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ