ትናንት ምሽት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት ብቸኛ ጨዋታ በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ነጥብ ሲጥል የቆየው ኢትዮጵያ ቡና የሊጉ የመጨረሻ ደረጃ ላይ የተቀመጠውን ሀዲያ ሆሳዕናን በጨዋታው መገባደጃ ላይ በተገኘችው የፓትሪክ ጐል በመታገዝ 2-1 በሆነ ውጤት ለመርታት ችሏል፡፡ የሶከር ኢትዮጵያው ዮናታን ሙሉጌታ በዛሬው የታክቲክ ትዝብቱ በጨዋታውን የታዩ ዋና ዋና ታክቲካዊ ክስተቶችን እንደሚከተለው አቅርቦላችኋል፡፡
የሁለቱ ቡድኖች የጨዋታ አቀራረብ
የ4-1-4-1 አጨዋወትን ወደሜዳ ይዞ የገባው ኢትዮጵያ ቡና እንደተለመደው ሁሉ ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወት ላይ ያመዘነ ቅርፅ ነበረው፡፡ ቡድኑ በአብዛኛው ኳስ ይነኩ በነበሩት ሁለቱ የመሀል አማካዮቹ መስዑድ እና ኤልያስ ላይ ያተኮረ የኳስ ቅብብሎችን በማድረግና የመስመር ተከላካዮቹን ጭምር በማጥቃት ላይ በማሳተፍ በመሀል ሜዳው እንቅስቃሴ የቁጥር ብልጫን ለማግኝት በመሞከር የጐል እድሎችን ለመፍጠር ያለመ አቀራረብ ነበረው፡፡ ከጋቶች ፊት ከነበሩት አራቱ አማካዮች መካከል መስዑድ መሀመድ በጥቂቱ ወደ ጋቶች እየቀረበ ኳስን የማደራጀት ስራን የሰራባቸው አጋጣሚዎች የቡድኑን አጨዋወት 4-2-3-1 ቢያስመስለውም በአብዛኛው ግን አራቱ አማካኞች በሜዳው ስፋት ከብቸኛው አጥቂ ያቤውን ዊልያም ጀርባ ይታዩ ነበር፡፡ ይህም የቡድኑ የተጨዋቾች አደራደር ወደ 4-1-4-1 ይበልጥ የቀረበ እንደሆነ ያመለክታል፡፡
የሀዲያ ሆሳዕና ቡድን በበኩሉ ትላንት ኢትዮጵያ ቡናን የገጠመው በ4-2-3-1 ቅርፅ ነበር ፡፡ የእንግዳው ቡድን የአማካይ መስመሩን በራሱ የሜዳ አጋማሽ ላይ በማድረግና ለተጋጣሚው የመሀል ሜዳ የኳስ ፍሰት የሚያገለግሉ ክፍተቶችን በመዝጋት እንዲሁም ኳሶችን በማጨናገፍ ላይ ያተኮረ አጨዋወትን መርጧል፡፡ ቡድኑ ከተጋጣሚው የሚነጥቃቸውን ኳሶች በፍጥነት ወደ ሁለተኛው የሜዳ አጋማሽ ይዞ በመግባት የጐል እድሎችን ለመፍጠር አቅዶ ወደሜዳ እንደገባ መናገር ይቻላል፡፡
በተጨማሪም የሆሳዕናው ቡድን በአመዛኙ በመከላከሉ ላይ ማተኮሩ ከ አጥቂው ጀርባ የነበሩት ሶስቱ አማካዮች ወደ ኋላ መሳብ የቡድኑን አጨዋወት ወደ 4-5-1 የቀረበ አንዲመስል አድርጎታል፡፡
የመጀመሪያ አጋማሽ የኢትዮጵያ ቡና ያልተሳካ ማጥቃት
ባለፉት ዓመታት በአለም እግር ኳስ ላይ ኳስን ተቆጣጥረው የሚጫወቱ ቡድኖች ውጤታማ ሲሆኑ በተደጋጋሚ ተመልክተናል፡፡ በተጋጣሚ የሜዳ ክልል ውስጥ ኳስን ረዘም ላለ ጊዜ በመያዝ በተደጋጋሚ ቅብብሎሽ እና በተጠና የተጨዋቾች ከኳስ ውጪ በሚደረግ እንቅስቃሴ አማካይነት ተጋጣሚን ክፍተት እንዲፈጥር በማድረግ የጐል እድሎችን መፍጠር የነዚህ ቡድኖች መገለጫ ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይህ አጨዋወት ከሚፈተንባቸው አጋጣሚዎች አንዱ ተጨዋቾቹን ከኳስ ኋላ አድርጐ በጥልቀት ወደራሱ የግብ ክልል በመጠጋት የሚከላከል ቡድን በሚገጥመው ወቅት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ተጋጣሚዎችን አስከፍቶ እድሎችን ለመፍጠር በተጨዋቾች መካከል የሚኖረው ውህደት ኳስ ሳይበላሽባቸው በትእግስት በዙ ቅብብሎችን በማድረግ እንዲሁም ከኳስ ውጪ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በመታገዝ በተከላካዮች መካከል በሜዳው ቁመትም ሆነ ስፋት ክፍተቶችን የማስፋት ብቃት ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡
ትናንት ኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያው አጋማሽ የዚህን ዓይነቱን ጠንከር ያለ የመከላከል አጨዋወት በተመግበር ላይ የነበረውን የሀዲያ ሆሳዕናን የመሀል ክፍል ሰብሮ መግባት ከብዶት ታይቷል፡፡ ከጋቶች ፓኖም ፊት የነበሩት የኢትዮጵያ ቡና አራቱ አማካዮች በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ጊዜያቸውን ቢያሳልፉም ነገር ግን የኳስ ቅብብላቸው የተጋጣሚያቸውን ወደኋላ ያፈገፈገ የመከላከል መረብ አልፎ ለመግባት አቅም አልነበረውም፡፡ ለዚህም ይመስላል ቡድኑ የጐል ሙከራዎችን ያደርግ የነበረው ከተጋጣሚው ሳጥን ውጪ ከርቀት በሚሞከሩ ኳሶች ነበር፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ቡድኑ የጐል አጋጣሚ ሲፈጥር የታየው በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ ነበር፡፡ ለዚህ ያልተሳካ የማጥቃት እንቅስቃሴ እንደምክንያትነት ሊጠቀስ የሚችለው የቡድኑ አብዛኛው የኳስ ፍሰት ትኩረት ያደርግ የነበረው መሀል ለመሀል በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ የነበረ መሆኑ ነው (ምስል 2ን ይመልከቱ)፡፡ የቡድኑ የመስመር አማካዮች ጥላሁን እና እያሱ ሳይቀሩ ወደ ውስጥ በመግባት ይበልጥ ለኤልያስ እና መስዑድ በመቅረብ ሲጫወቱ ተስተውለዋል፡፡
ይህ ሁኔታ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ በጣሙን ወደመሀል የጠበበ እንዲሆን አስገድዶታል፡፡ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያው አጋማሽ የሜዳውን የጐን ስፋት ለመጠቀም ያሰበው ከሁለቱ የመስመር አማካዮች በበለጠ የመስመር ተከላካዮቹን በአብዱልከሪምና በሳላምላክ ተገኝ አማካይነት ይመስል ነበር፡፡ ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች አብዛኛውን የመጀመሪያውን አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተጋጣሚያቸው ግማሽ ሜዳ ላይ ቢያሳልፉም ነገር ግን ቡድኑ በሚፈልገው መጠን ሁለቱን መስመሮች ተከትለው ወደፊት ከተጋጣሚያቸው አቻ የመስመር ተከላካዮች ጀርባ ያለው ቦታ ድረስ ገብተው እድሎችን ለመፍጠር ብሎም የተጋጣሚን ተከላካዮችን በእንቅስቃሴ ወደ ራሳቸው በመሳብ ለአራቱ አማካዮች ወደ መሀል የጠበበ አጨዋወት ክፍተት መፍጠር አልቻሉም ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ የአጥቂው ያቤውን ዊልያም ኳስን ለመቀበል ወደኋለው ያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ ሲጨመርበት የኢትዮጵያ ቡና አማካዮች በሀድያ ተከላካዮች ፊት ለፊት በቁጥር በዝተው በሚገኙባቸው አጋጣሚዎች እንኳን የኳስ መቀባበያ ክፍተት (passing space) ሲያጡና በተደጋጋሚ ኳስ ሲበላሽባቸው ይታዩ ነበር፡፡
የመጀመሪያው አጋማሽ ሀድያ ሆሳዕና
የሀድያ ሆሳዕና የመጀመሪያ አጋማሽ እንቅስቃሴ ስኬታማ ነበር፡፡ ከፊት አጥቂያቸው እንዳለ ደባልቄ በቀር ሦስቱ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው አማካዮች ወደ ሁለቱ የተከላካይ አማካዮች በመጠጋት እና በጥልቀት በመከላከል ለተጋጣሚያቸው በቂ የመጫወቻ ክፍተት ባለመፍጠር ተጫውተዋል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኑ በተከላካዮቹ እና በሁለቱ የተከላካይ አማካዮች እንዲሁም ከእነሱ ፊት በሚገኙት ሦስቱ አማካዮች መካከል በሜዳው ቁመት የነበረውን ክፍተት በጣም አጥብቦ ተጫውቷል፡፡ ይህም በጐላቸው ትይዩ ከሳጥናቸው ግማሽ ክብ እስከ መሀል ሜዳው ክብ ድረስ ባለው ቦታ ላይ ያበዛ የነበረውን የኢትዮጵያ ቡናን አማካዮች የኳስ ቁጥጥር የመጨረሻ የግብ እድል እንዳይፈጥር ለማድረግ ጠቅሟቸዋል፡፡
ሁለቱ የተከላካይ አማካዮች አበው ታምሩና አግላን ቃሲም የኢትዮጵያ ቡናን ዋነኛ አማካዮች የኤልያስንና የመስዑድን እንቅስቃሴ በቅርብ ርቀት በመከተል ከራሳቸው የግብ ክልል ሳይርቁ ለመቆጣጠር ችለዋል፡፡ በተለይም አበው ታምሩ ኤልያስን እየተከተለ ኤልያስ ከኳስ ውጪ በሚሆንበት ጊዜ ነፃ ሆኖ ኳስ ለመቀበል እንዳይችል ለማድረግ ሞክሯል፡፡ ኤልያስ ከዚህ ጫና ለመላቀቅ ከመስዑድ ጋር ቦታ እየተቀያየረ እንዲሁም ወደኋላ እየተሳበ ሲጫወትም ተስተውሏል፡፡ ሀድያዎች ኳስ በሚነጥቁበት ጊዜ ሁለቱ የመስመር አማካዮቻቸው አየለ ተስፋዬና አምራላ ደልታታ በፍጥነት ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመግባት ይሞክራሉ፡፡ በተለይ የሀድያ ተጨዋቾች የነጠቁት ኳስ በቡድኑ የመሀል አማካይ አበባው ዮሐንስ ጋር በሚደርስባቸው አጋጣሚዎች ቡድኑ በፈጣን መልሶ ማጥቃት በተለይም በቀኝ መስመር በአምራላ በኩል በማድረግ ከኢትዮጵያ ቡና መሀል ተከላካዮች ጀርባ ያለውን ቦታ በመጠቀም ተደጋጋሚ ሙከራዎች አድርገዋል፡፡
የሁለቱ ቡድኖች የሽግግር ጨዋታዎች
ሀድያዎች በድንገተኛ የመልሶ ማጥቃት ወደተጋጣሚያቸው ሜዳ ሲገቡና የግብ እድል ለመፍጠር በሚሞክሩባቸው አጋጣሚዎች ኳስ ሲበላሽባቸው ተጋጣሚያቸው ኳስን መስርቶ ወደነሱ የሜዳ ክልል ለመግባት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ወደ ግብ ክልላቸው ከመድረሱ በፊት በፍጥነት ወደኋላ በመመለስ እና የመከላከል ቅርፃቸውን በመያዝ የተሳካ ከማጥቃት ወደመከላከል የሚደረግ ሽግግር አሳይተውናል፡፡
በአንፃሩ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ወደ ማጥቃት በሚያደርጉት ሽግግር ላይ ደክመው ታይተዋል፡፡ ተጋጣሚያቸው ወደፊት ለማጥቃት ሲሄድ መጀመሪያ በራሱ የሜዳ ክፍል ላይ ሆኖ ሲከላከል በተጨዋቾቹ መካከል ከሚኖረው ጠባብ ክፍተት የተሻለ ሰፊ ክፍተት ሲፈጠርበት በፈጣን እና ቀጥተኛ ኳሶች የተፈጠሩትን ክፍተቶች መጠቀም አለመቻላቸው ለሀድያዎች የመከላከል ስርአት ምቹ እንዲሆኑ አድርጓቸው ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ መከላከልም የሚያደርጉት ሽግግርም ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡ ቡድኑ ኳስ ይዞ በሚያጠቃበት ወቅት የሚኖረው ቅርፅ የሁለቱን የመስመር ተከላካዮች የተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ ግማሽ ድረስ መምጣት የሚጠይቅ በመሆኑ ቡድኑ ኳስ ሲነጥቅ በመሀል ሜዳ አካባቢ የሚገኙትን የመሀል ተከላካዮች እና ጋቶች ፓኖምን በከፍተኛ ሁኔታ ለመልሶ ማጥቃት ተጋላጭ ያደርጋቸው ነበር፡፡ በነዚህ አጋጣሚዎች በተለይ ከጋቶች ፓኖም ፊት ያሉት አማካዮች በፍጥነት ወደራሳቸው የጐል ክልል በመግባት ቡድኑን የመከላከል መስመር ጥቃት ለመቀነስ ሳይችሉ ከኳስ ጀርባ ሆነው በሜዳው አጋማሽ ላይ ይታዩ ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱ ደካማ ሽግግር በፈጣን አጥቂዎች የሚመራና ፈጣን በሆነ የማጥቃት ሽግግር በቁጥር በዛ ብሎ በተጋጣሚው ሜዳ ላይ የሚገኝ ተጋጣሚ በቀላሉ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ ሀድያ ሆሳዕናዎችም ይህን ክፍተት በመጠቀም በተለያዩ አጋጣሚዎች ጫና በመፍጠር በተለይም በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች በአምራላ ደልታታ አማካይነት የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡ እንዲሁም በ19ኛው ደቂቃ የአጥቂው እንዳለ ደባልቄ ጎልም ሲቆጠር የኢትዮጵያ ቡናዎች ደካማ የመከላከል ሽግግር አስተዋፅኦ ነበረው፡፡
የሁለተኛው አጋማሽ ለውጦችንና የኢትዮጵያ ቡና ጫና
በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከመጀመሪያው በተሻለ መልኩ ተጋጣሚያቸውን ጫና ውስጥ መክተት ችለዋል፡፡ በዚህም ሁኔታ በሁለተኛው 45 መጀመሪያ ላይ በተወሰነ መልኩ ወደፊት ለመጠጋት ሞክሮ የነበረውን ተጋጣሚያቸውን የተቀረውን ጊዜ በሙሉ በራሱ አጋማሽ ላይ ሆኖ ጨዋታውን እንዲጨርስ አድርገውታል፡፡ የሀድያ ሆሳዕናዎች የመከላከል ጥንካሬና ውህደትም ከመጀመሪያው አጋማሽ ቀንሶ ታይቷል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና የማጥቃት አጨዋወት ጫናው እየበረታ ለመምጣቱ የቀኝ መስመር ተከላካዩ የአብዱልከሪም ሚና የጐላ ነበር፡፡ ቡድኑ በመጀመሪያው ግማሽ አጥቶት የነበረውን በሜዳው የጐን ስፋት ተጋጣሚውን የመለጠጥ አጨዋወት ከእረፍት መልስ አስተካክሎ ገብቷል፡፡ ይህንንም ማሳካት የቻሉት በመስመር ተከላካዮቻቸው አማካይነት ነበር፡፡ በዚህም አቀራረብ የሀድያን ተጨዋቾች የመከላከል እንቅስቃሴ ወደመሀል በመሳብ በመስመር በሚፈጠሩት ክፍተቶች በተለይም በቀኝ በኩል በአብዱልከሪም የተሳካ እንቅስቃሴ አማካይነት ጫና ፈጥረዋል፡፡ የ60ኛው ደቂቃ የአቻነት ጐልም በዚህ እንቅስቃሴ አማካይነት ተገኝታለች፡፡ አብዱልከሪም ጎሏን ባገባበት አጋጣሚ የኢትዮጵያ ቡና አማካዮች የግራ መስመር እንቅስቃሴ የሀድያዎችን ተከላካዮች ትኩረት ወደ ግራ በመሳቡ አብዱልከሪም ኤልያስ የሰጠውን ኳስ ተቀብሎ ወደ ጎልነት ለመቀየር በቂ ጊዜና ክፍተት እንዲኖረው አድርጓል፡፡
ከጐሏ መቆጠር በኋላም የኢትዮጵያ ቡና የተጨዋቾች ቅያሬ በሁለቱ መስመሮች የሚገኙትን ክፍተቶች በመጠቀም ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡ አሰልጣኝ ፓፓዲች ኤልያስ ማሞንና ጥላሁን ወለዴን በማስወጣት ፓትሪክ ቤናውንን (21) እና ንዳዬ ፋይስን (12) አስገብተዋል፡፡ በነዚህም ቅያሬዎች የቀኝ መስመር ተሰላፊውን እያሱን በኤልያስ ቦታ በመቀየር የግራና የቀኝ መስመራቸውን በያቤውን ዊልያም (በግራ) እና ንዳዬ ፋይስን (በቀኝ) አጠናክረዋል (ሁለቱ ተጨዋቾች በጨዋታው ማብቂያ አካባቢ ቦታ ተቀያይረው ነበር) ፡፡ የያቤውን ወደመስመር መሄድ ተከትሎም የአጥቂነት ቦታውን በመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ከቆመ ኳስ የተገኘውን አጋጣሚ ወደጐልነት በቀየረው ፓትሪክ ቤናውን(21) እንዲመራ አድርገዋል (ምስል 2ን ይመልከቱ)፡፡
ይህ የ63ኛ ደቂቃ ቅያሬ ለኢትዮጵያ ቡና የመስመር እንቅስቃሴ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል፡፡ ቡድኑም ወደግራ ባደላ የማጥቃት እንቅስቃሴ በመጀመሪያው አጋማሽ አጥቶት የነበረውን ክፍተቶች ለመፍጠር ችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ሁለት ተቀያሪ የመስመር አማካዮችም የተጋጣሚያቸውን እንቅስቃሴ ወደጐን በመለጠጥ የመከላከል ትኩረቱን እንዲያጣና ሰዓት በገፋ ቁጥር ከመጀመሪያው በተለየ ብዙ ክፍተት እንዲፈጥር ሲያደርጉት ተስተውሏል፡፡ በዚህ ጫና ውስጥ የነበሩት ሀድያዎች የተከላካይ አማካይ ቦታቸውን በአዲስ ሀይል ለማጠናከር ኢማኑኤል ኢኪራሽን በአበው ታምሩ ቀይረው አስገብተዋል፡፡ ነገር ግን ቡድኑ የኢትዮጵያ ቡና የሁለተኛውን ግማሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደኋላ ገፍቶት እንጂ አጋጣሚዎችን ቢያገኝ እድሎችን ለመፍጠር የመሞከር ሀሳብ እንደነበረው የዱላ ሙላቱ አምራላን ቀይሮ መግባቱ ይነግረናል፡፡ የዘንድሮ ውድድር ለቡድኑ አራት ጎሎችን ያስመዘገበው ዱላ ሙላቱ ተቀየሮ ከገባ በኋላ አጥቂውን እንዳለ ደባልቄ በመጨረሻ ደቂቃዎች በተዘራ አባቴ ተቀይሮ እስኪወጣ ድረስ ወደ ቀኝ መስመር መቀየሩም የቡድኑ የመልሶ ማጥቃት ኳሶችን የመፍጠር ፍላጎቱ ሌላው ማሳያ ነው (ምስል 3ን ይመልከቱ)፡፡ ነገር ግን ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከተፈጠረባቸው ጫና ተላቀው ሌላ የግብ ሙከራ እድል ሳይፈጥሩ በፓትሪክ ቤናውን 90ኛ ደቂቃ ጎል ለአሳዛኝ ሽንፈት ተዳርገዋል፡፡
ባጠቃላይ የትላንት ምሽቱ ጨዋታ የሀድያ ሆሳዕናን ድንቅ የመከላከል አደረጃጀትና የኢትዮጵያ ቡናን እስከመጨረሻው ድረስ ክፍተቶችን ለማግኘት ያደረገውን ጥረት ያስተዋልንበት ጥሩ ጨዋታ ሆኖ አልፏል፡፡