ኡመድ ኡኩሪ ተቀይሮ በገባበት ጨዋታ ኢኤንፒፒአይ በአል መስሪ ተሸንፏል

 

ትላንት ማምሻውን በኢስማኤሊ ከተማ በሚገኘው የኢስማኤሊ ስታድየም በተደረገ የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ አል መስሪ ኢኤንፒፒአይን 4-0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል፡፡ ኢትዮጵያዊው አጥቂ ኡመድ ኡኩሪ በጨዋታው ላይ ተቀይሮ በመግባት መጫወት ችሏል፡፡

ፈጣን መልሶ ማጥቃት እና ጥብቅ መከላከልን የመረጡት ባለሜለዳዎቹ አል መስሪ በ23 ደቂቃዎች ውስጥ የምሽቱ ኮከብ በነበረው አህመድ ራውፍ እና አህመድ ካቦሪያ ግብ ታግዘው 2-0 መምራት የቻሉ ሲሆን የኢኤንፒፒአይ አሰልጣኝ ሃምዳ ሰድኪ ቡድናቸው ወደ ጨዋታው እንዲመለስ በማሰብ አጥቂውን ኡመድ በኑር ኤል ሳዒድ በ29ኛው ደቂቃ አስገብተውታል፡፡ አል መስሪዎች በአህመድ ራዉፍ ሁለተኛ ግብ ታግዘው የመጀመሪያውን አጋማሽ 3-0 እየመሩ ሲጨርሱ አህመድ ራዉፍ ሃት-ትሪክ የሰራባትን ግብ በ83ኛው ደቂቃ በግንባር በመግጨት ከመረብ አዋህዶ ጨዋታው በአል መስሪ 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ኡመድ በጨዋታው ላይ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻለም፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ በመሃል ሜዳ የተገደበ እንቅስቃሴ የነበረው ዘጠኝ ቁጥር ለባሹ ኡመድ ለክለቡ እስካሁን ግብ አላስቆጠረም፡፡

ሽንፈቱን ተከትሎ ኢኤንፒፒአይ በደረጃ ሰንጠረዡ በ28 ነጥብ 10ኛ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል፡፡ ሊጉን ዛሬ ከሽመልስ በቀለ ክለብ ከሆነው ፔትሮጀት ጋር የሚፋለመው አል አሃሊ በ41 ነጥብ ይመራል፡፡ ዛማሌክ እና አል መስሪ በ38 እና በ36 ነጥብ ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል፡፡

ታላላቆቹ የካይሮ ክለቦች አሃሊ እና ዛማሌክ አዲስ አሰልጣኞችን በሳለፍነው ሳምንት መሾማቸው ይታወሳል፡፡ ሆላንዳዊው የቀድሞ የቶትንሃም ሆትስፐርስ አሰልጣኝ ቀይ ለባሾቹ አሃሊን ለማሰልጠን ሲስማሙ ስኮትላዳዊው የቀድሞ የበርሚንግሃም ሲቲ፣ አስቶንቪላ እና የስኮንትላንድ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አሌክስ ማክሊሽ ነጭ ለባሾቹን ተረክበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *