‹‹ እቅዳችን አሸንፈን አልያም ለመልሱ ጨዋታ የሚረዳንን ውጤት ይዘን መመለስ ነው›› የሉሲዎቹ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው   

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ ዛሬ ምሽት ወደ አልጄርያ ከማቅናቱ በፊት የመጨረሻ ልምምዱን ዛሬ ጠዋት በአዲስ አበባ ስታድየም አድርጓል፡፡ በሉሲዎቹ የመጨረሻ ልምምድ ላይ የተገኘችው ሶከር ኢትዮጵያ ከዋና አሰልጣኙ ብርሃኑ ግዛው ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡ እኛም ለእናንተ ለአንባቢያን በሚመች መልኩ እንዲህ አሰናድተነዋል፡-

ዝግጅት

‹‹ ያለፉትን 20 ቀናት ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ሁሉም ተጫዋቾች ከክለብ ውድድሮች እንዲሁም ከ17 እና 20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች የመጡ በመሆናቸው የዝግጅት ጊዜው በቂ ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ ፌዴሬሽኑም የምንጠይቀውን በፍጥነት እያሟላልን ዝግጅታችንን በአግባቡ እድንሰራ አድርጎናል፡፡ ››

ስለተቀነሱት ተጫዋቾች

‹‹በመጀመርያ የጠራናቸው ተጫዋቾች 30 የነበሩ ሲሆን ኋላ ላይ ወደ 25 ቀንሰናል፡፡ አሁን ደግሞ ወደ አልጄርያ የሚጓዙትን 20 ተጫዋቾች መርጠናል፡፡ ተከላካይዋ ውባለም በጉዳት ምክንያት አብራን መጓዝ አልቻለችም፡፡ ውባለምን ጨምሮ ከጉዞው የቀሩት 5 ተጫዋቾች ሙሉ ለሙሉ ከብሄራዊ ቡድን ተቀንሰዋል ማለት አይደለም፡፡ በገንዘብ እጥረት ምክንያት እንጂ በመጀመርያ አስበን የነበረው ሁሉንም ተጫዋቾች ይዘን ለመሄድ ነበር፡፡ ከመጀመርያው ጨዋታ ስንመለስ የተቀነሱት ተጫዋቾች በድጋሚ ይቀላቀሉናል፡፡››

በስህተት ወደወጡበት ውድድር መመለስ 

‹‹ በመጀመርያ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጫዋቾች ምን እንደተሰማቸው ጠይቄያቸው ነበር፡፡ ከውድድሩ በስህተት መውጣታችን አሳዝኗቸው ነበር፡፡ ይህንን ስህተት የፈፀሙትን ግለሰቦችም አዝነውባቸው ነበር፡፡፡ ኋላ ላይ ፌዴሬሽኑ ባደረገው ጥረት ወደ ማጣርያው መመለሳችን ስንሰማ ሁላችንም አላመንንም ነበር፡፡ ወደ ውድድር መመለሳችን በጣም አስደስቶናል፡፡

‹‹ አሁን ለሰበብ የሚሆን ቦታ አይኖረንም፡፡ ብሄራዊ ቡድናችን ድል ካስመዘገበ 4 አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህንን ቀልብሰን ማጣርያዎችን በድል በመወጣት ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለመመለስ ጠንክረን እየሰራን እንገኛለን፡፡››

የባንክ እና ደደቢት ተጽእኖ

በቅርቡ የቻን ውድድር አሸናፊ የሆነው የኮንጎ ብሄራዊ ቡድንን የተመለከትን እንደሆነ 9 ተጫዋቾች የተመረጡት ከአንድ ክለብ (ቪታል) ነው፡፡ ከጥቂት ክለቦች ተጫዋቾች ሲመረጡ ለቡድን ውህደት አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ደደቢት የወቅታዊው የሴቶች እግርኳስ ጠንካራዎቹ ቡድኖች እንደመሆናቸው ከሁለቱ ክለቦች በርካታ ተጫዋቾች መመረጣቸው ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ››

IMG_3505

ተጋጣሚያቸው

‹‹ የተጋጣሚችንን ወቅታዊ ሁኔታ ለማወቅ ጥረት አድርገናል፡፡ ረዳት አሰልጣኝ ቢንያም አዲሱ በዚህ ረገድ ያደረገው ጥረት የሚመሰገን ነው፡፡ ቡድኑ በቅርቡ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ያደረገውን ጨዋታ ቪድዮ ከደቡብ አፍሪካ ረዳት አሰልጣኝ ጋር በመነጋገር አግኝቶልናል፡፡ በቪድዮው ላይ አልጄርያ ጠንካራ ቡድን እንደሆነ በሚገባ ተመልክተናል፡፡

‹‹የልሳን የሴቶች ስፖርትም ወቅታዊ የቡድኑን መረጃዎች በየጊዜው በማቅረብ እገዛ አድርጎልናል፡፡ አልጄርያ በዚህ ወር በፊፋ ደረጃ 77ኛ ስትሆን በአፍሪካ 7ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ 4 ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈች ሃገር ስትሆን ባለፈው አመት የአረብ ሊግ ቻምፒዮን ሆናለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በናሚቢያው አፍሪካ ዋንጫ የኛን ብሄራዊ ቡድን ጥሎ ያለፈው ጠንካራው የጋና ብሄራዊ ቡድንን አሸንፈዋል፡፡

‹‹አልጄርያ ከስብስቧ መካከል 11 ተጫዋቾቿ በፈረንሳይ ይጫወታሉ፡፡ ስለዚህም የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምዳቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ይንንም በተመለከትነው ቪድዮ ላይ ተገንዝበናል፡፡ በደካማ ጎኖቻችን ላይ ይበልጥ በመስራት ይህንን ጠንካራ ቡድን ለማሸነፍ ነው የተዘጋጀነው፡፡››

የወዳጅነት ጨዋታ

‹‹ የወዳጅነት ጨዋታ አለመኖሩ እንደሚጎዳን ጥርጥር የለውም፡፡ በዝግጅታችን መሃል የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ የቻልነው ከወንዶች ቡድኖች ጋር ነው፡፡ በተፈጥሮ ደግሞ ወንዶች እና ሴቶች ተመሳሳይ ጉልበት እና አቅም አይኖራቸውም፡፡ የጨዋታው ፍጥነት ከሚገባው በላይ ሲጨምር ያሰብነውን ታክቲክ ያፈራርስብናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ተጋጣሚው ቡድን (ወንዶቹ) ኳስን ለረጅም ጊዜ ሲይዙ የኛ ተጫዋቾች ኳሱን ለመቀማት ከሚገባው በላይ ጉልበት ያወጣሉ፡፡ በአጠቃላይ በወዳጅነት ጨዋታ አለመኖር ተጎድተናል፡፡

‹‹ የወዳጅነት ጨዋታ የማመቻቸት ተግባር የአሰልጣኝ ሳይሆን የአስተዳደር ነው፡፡ ዝግጅት ሲኖር ወዳጅነት ጨዋታም የዝግጅት አካል እንዲሆን ሊታስበት ይገባል፡፡ አንድ አሰልጣኝ የተጫዋቾቹን ስህተት እና የቡድኑን ክፍተት ሊያርም የሚገባው በነጥብ ጨዋታ ሳይሆን በወዳጅነት ጨዋታዎች ነው፡፡ በወዳጅነት ጨዋታ የቡድኑ ክፍተት ካልታየ በነጥብ ጨዋታ በስህተት አንድ ግብ ካስተናገድን ለማገገም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለስነ ልቦና እና ለጨዋታ ዝግጁ ለመሆንም የቀዳጅነት ጨዋታ አስፈላጊ ነው፡፡››

ከአልጀርስ ምን እንጠብቅ?

‹‹ በአልጀርስ በሚገባ እየተከላከልን በሚገኙ ክፍተቶች ግብ ለማስቆጠር የሚረዳንን አጨዋወት እንተገብራለን፡፡ እቅዳችን ጨዋታውን አሸንፈን አልያም ለመልሱ ጨዋታ የሚረዳንን ውጤት ይዘን መመለስ ነው፡፡››

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *