ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ድሬዳዋ ከተማ

የነገውን የመጀመሪያ ጨዋታ በዳሰሳችን እንዲህ ተመልክተነዋል።

በመካከላቸው የሦስት ነጥቦች ልዩነት ብቻ ኖሮ የሚገናኙት ጅማ አባ ጅፋር እና ድሬዳዋ ከተማ በታችኛው የሰንጠረዡ ክፍል ላይ ልዩነት የሚፈጥር ወሳኝ ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ።

በባህር ዳር ቆይታው የመጀመሪያዎቹ የሆኑ ሁለት ድሎችን ማስመዝገብ የቻለው አባ ጅፋር በሌሎቹ ምንም ነጥብ ባለማሳካቱ ከአዳማ ከተማ ውጪ ሌላ ክለብ መብለጥ አልቻለም። ከለበት ደረጃ ቀና ለማለት በማሰብም በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በማዘዋወር ነው ወደ ድሬዳዋ ያቀናው። ከነዚህም ውስጥ ቀደም በለው ጨዋታዎችን ካከናወኑት ሥዩም ተስፋዬ እና አማኑኤል ተሾመ በተጨማሪ በረከት አማረ ፣ አሌክስ አሙዙ ፣ ዋለልኝ ገብሬ እና ራሒም ኦስማኖ የክለቡን ያለመውረድ ትግል መቀላቀል ችለዋል።

ከአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም መምጣት በኋላ የመከላከል አቅሙን ማሻሻል የቻለው ጅማ ወደ ፊት ሄዶ ጥቃቶችን የመሰንዘር ድፍረቱም ጨምሮ ታይቷል። ነገር ግን መከላከል ሂደቱን ከስህተት የፀዳ ማድረግ እና በጨዋታዎች ላይ ብልጫ ውስዶ ከአንድ በላይ ጎል ለማስቆጠር የሚያችሉ ዕድሎችን መፍጠሩ ላይ አሁንም ገና የሚቀረው በመሆኑ ትኩረቱን እዚህ ላይ አድርጎ ሲዘጋጅ እንደከረመ መረዳት ይቻላል። መሀል ተከላካዩ መላከ ወልዴን ብቻ በጉዳት እንዳጣ የተሰማው ቡድኑ ሲራባቸው የከረሙ መሻሻሎችን በውጤት ለማጀብ በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ከሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ጋር መገናኘቱም መልካም አጋጣሚ የሚሆንለት ይመስላል።

ከዘጠነኛው ሳምንት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በደረጃ የሚበልጠውን ተፎካካሪ በማግኘቱ እንደጅማ ሁሉ ጨዋታው ከተጋጣሚ ደካማ መሆን አንፃር ለድሬዳዋም ለማንሰራራት መነሻ ሊሆንለት ይችላል። ውድድሩ ወደ መቀመጫ ከተማቸው በመጣመት ቀዳሚው ሳምንት ጅማን ያገኙት ድሬዎች ምንም እንኳን ከጅማ በሦስት ነጥብ ርቀት ላይ ብቻ ቢገኙም የቡድናቸው ጠጣርነት ላይ መሻሻሎች መታየት ጀምረው ነበር። ክለቡ አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስን ከሾመ በኋላ ወደ ድል አይመለስ እንጂ በንፅፅር የተሻሉ ከነበሩት ተጋጣሚዎቹ ጋር በተከታታይ ነጥብ ከመጋራት ባለፈ ኋላ ክፍሉ ላይ በስፋት ይታዩ በነበሩት ግልፅ ድክመቶች ላይ መጠነኛ መሻሻል ማሳየት ችሏል።

በወራጅ ቀጠና አፋፍ ላይ የሚገኘው ክለቡ ባህር ዳር ላይ ከተጠቀመባቸው ዐወት ገብረሚካኤል እና ሄኖክ ገምቴሳ በተጨማሪ ዳንኤል ኃይሉ ፣ ያሲን ጀማል ፣ ሄኖክ ገምቴሳ እና ፕሪንስ ሰቨሪንሆን በእጁ በማስገባትም ደካማ ጎኖቹን ለማጠናከር ሞክሯል። የመጨረሻውን የቡናን ጨዋት ሳይጨምር እንደቡድን የመከላከል ብቃቱ ላይ ያስተካከላቸውን ነገሮች ከማስቀጠል በተጨማሪ የቅርፅ እና የተጫዋቾች ኃላፊነት ለውጥ የተደረገበት የማጥቃት ሂደቱ ላይም የተሻለ የውህደት ደረጃ ላይ ደርሶ ወደ ውድድሩ መመለስ ለቡድኑ ዋነኛ ግብ ይመስላል። ነገ ለአዲስ ፈራሙዎቹም የመሰለፍ ዕድል እንደሚሰጥ የሚጠበቀው ቡድን ውስጥ ያሉትን የጉዳት እና ቅጣት ዜናዎችን ለማካተት ያደረግነው ጥረት ግን ሳይሳካ ቀርቷል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ድሬ እና ጅማ ከአምስት ግንኙነታቸው በአንዱ ብቻ አቻ በተለያዩበት ታሪካቸው ድሬዳዋ ሦስት ጊዜ ጅማ ደግሞ አንድ ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል።

– በጨዋታዎቹድሬዎች ስምንትግቦችን ሲያስቆጥሩ ጅማዎች ደግሞ አራት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)

አቡበከር ኑሪ

ሥዩም ተስፋዬ – አሌክስ አሙዙ – ውብሸት ዓለማየሁ – ኤልያስ አታሮ                   

ንጋቱ ገብረሥላሴ – አማኑኤል ተሾመ –  ዋለልጅ ገብሬ

ተመስገን ደረሰ – ራሒም ኦስማኖ –  ሱራፌል ዐወል 

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ፍሬው ጌታሁን

ዐወት ገብረሚካኤል – ያሬድ ዘውድነህ – ፍሬዘር ካሳ – ሄኖክ ኢሳይያስ

ዳንኤል ደምሴ – ዳንኤል ኃይሉ

አስቻለው ግርማ – ሙኸዲን ሙሳ – ኢታሙና ኬይሙኒ

ጁኒያስ ናንጄቦ


© ሶከር ኢትዮጵያ