የአሠልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 2-3 ሀዋሳ ከተማ

አምስት ግቦች ከተቆጠሩበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከአሠልጣኞች አስተያየት ተቀብሏል።

ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ስለነበረው ውጥረት?

ቅያሪ ተጫዋች ከሌለህ ጉልበት ቆጥበህ መጫወት ነው ያለብህ። ይህ ደግሞ እንደ አሠልጣኝ ያስጨንቃል። በተለይ ከበድ ያለ ተጋጣሚ ስትገጥም ያስጨንቃል። ግን ሜዳ ላይ ያየነው በተቃራኒ ነው። እንደ አጠቃላይ የኮቪዱ ጉዳይ በዓለም የመጣ ነው። ምንም ማድረግ አይቻልም።

ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ ስለመሻሻሉ?

በእርግጥ እንደዚህ አይነት ጨዋታዎች ከባዶች ናቸው። ምክንያቱም ተጋጣሚን ያነሰ ትኩረት ሰጥተን መጫወት ትንሽ ይከብዳል። በእረፍት ሰዓትም ነቃ እንዲሉ እና ራሳቸውን እየጠበቁ 90 ደቂቃውን እንዲጫወቱ ነበር የነገርኳቸው። በአጠቃላይ ኮስተር ብለው ትክክለኛ ጨዋታ እንዲጫወቱ እና ክለቡን የሚገልፅ አጨዋወት እንዲጫወቱ ነበር የነገርኳቸው። ከሞላ ጎደል የነበረው ነገር የተሻለ ነው። ከተጋጣሚያችን አንፃር ትንሽ መጨመር ነበረብን። ግን ይሁን ይሄም ቆንጆ ነወ።

ዘላለም ሽፈራው – ወላይታ ድቻ

የትኛው ጎል አበሳጨህ?

የመጀመሪያው እና ሦስተኛው ጎል አበሳጭቶኛል። በተለይ ደግሞ ሦስተኛው ጎል። ምክንያቱም ሰዓቱ አልቆ ነበር። በተጨማሪም ከፍተኛ የትኩረት ችግር ነበር ግቡ እንዲቆጠርብን ያደረገው። በቀላሉ መቆጣጠር የምትችለው ኳስ ሲቆጠርብህ ትንሽ ያበሳጫል።

በአጥቂነት የተጠቀምካቸው ሁለቱ የግብ ዘቦች ብቃት?

የሚችሉትን አድርገዋል። ግብ ጠባቂዎቹን ገልብጠን በአጥቂነት እንዲጫወቱ አድርገናል። እንደውም በረኝነቱ ትዝ ብሏቸው ተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጃቸው እንዳይዙ እየሰጋን ነበር (እየሳቀ)። በአጠቃላይ ግን የሚችሉትን አድርገዋል። እነሱ ብቻ ሳይሆን ቡድኑም እንደ ቡድን የሚችለውን አድርጓል። በጣምም ታግለዋል። ሁለት ጎልም ማስቆጠር ትልቅ ነገር ነው። ደግሞም የተቆጠሩብን ጎሎች ያን ያክል ተለፍቶባቸው የመጡ ሳይሆኑ በእኛ የትኩረት ማነስ የመጡ ስለሆኑ ብዙም ቅር አላለኝም። ተጫዋቾቹ በጣም ታግለዋለወ።

ከጨዋታው በፊት አስቦት ስለነበረው ነገር?

አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ አይነት ነገሮች ሲያጋጥሙ ልበ ሙሉ መሆን ያስፈልጋል። ምንም አይነት ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ግን እነዛን ችግሮች ተቃቁሞ ማለፍ ያስፈልጋል። ትልቁ አቅም የሚባለውም ይሄ ነው። ትልቁ ብቃት የሚባለው በተሳኩ ሁኔታዎች ማለፍ ሳይሆን በፈተናዎች ተረማምዶ ማሸነፍ ነው። ከተጫዋቾቼም ጋር ስናወራ የነበረው ይሄንን ነወ። ከዚህ መነሻነት ተጨዋቾቼ በደንብ ተጋድለው እንደሚጫወቱ ግምት ነበረኝ። እንደውም እንቅስቃሴው ከገመትኩት በላይ ነው። ሁለት ጎል እናገባለን ብዬ ባላስብም ከጨዋታው ቢያንስ ነጥን ይዘን እንወጣለን የሚል እምነት ነበረኝ።


© ሶከር ኢትዮጵያ