በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ዛሬ 2 ጨዋታዎች ተካሂደው ንግድ ባንክ ከሜዳው ውጪ አዳማን በማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ይዞ ተመልሷል፡፡ ኤሌክትሪክ በተጨማሪ ደቂቃ ባገኘው ግብ ታግዞ ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡
በ09፡00 አዳማ አበበ ቢቂላ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ያስተናገደው አዳማ ከተማ የ3-2 ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ በአዳማ ከተማ የረጅም አመት ደጋፊ ህልፈት ምክንያት በ1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት የተጀመረው ጨዋታ የመጀመርያ አጋማሽ ሳቢ ያልነበረ እና ብዙ የግብ ሙከራዎች ያልተስተናገዱበት ነበር፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ የተጠናቀቀውም ጋብሬል አህመድ በ36ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ እንግዶቹ ንግድ ባንኮች እየመሩ ነበር፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ጋናዊው በ67ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት የባንክን መሪነት ወደ ሁለት ሲያሰፋ ከ1 ደቂቃ በኋላ የተጋለጠው የአዳማ የተከላካይ መስመርን ጥሶ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን 3ኛውን አክሏል፡፡ አዳማ ከተማ በ78ኛው ደቂቃ በታፈሰ ተስፋዬ በ90+1ኛው ደቂቃ በአቢኮዬ ሻኪሩ አማካኝነት ሁለት ግብ ቢያስቆጥርም ከውድድር ዘመኑ የመጀመርያ የሜዳው ሽንፈት ለመዳን በቂ ሊሆን አልቻለም፡፡
የንግድ ባንክን የድል ግቦች ከመረብ ያሳረፉት ጋብሬል አህመድ እና ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን በንግድ ባንክ ማልያ የመጀመርያ ግቦቻቸውን ከመረብ አሳርፈዋል፡፡
ውጤቱ አዳማ ከተማን ሁለት ጨዋታ ከሚቀረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በግብ ልዩነት አንሶ 2ኛ ደረጃ ላይ እንዲረጋ ሲያደርገው ንግድ ባንክ ከፍተኛ የደረጃ መሻሻል አሳይቶ ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ከፍ ብሏል፡፡
11፡30 አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ወላይታ ድቻን ያስተናገደው ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡ ድቻ እንደተለመደው በበርካታ ደጋፊዎቹ ታጅቦ እስከ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች መምራት ቢችልም ኤሌክትሪክ የማታ የማታ ነጥብ ተጋርቷል፡፡
የመጀመርያው አጋማሽ ካለግብ እና ካለማራኪ እንቅስቃሴ በተጠናቀቀበት ጨዋታ ወላይታ ድቻ በበድሉ መርዕድ የ58ኛ ደቂቃ የቅጣት ምት ግብ መሪ መሆን ችሏል፡፡ ለግቧ መቆጠር የኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ አሰግድ አክሊሉ ስህተት ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ኤሌክትሪኮች በፒተር ኑዋድኬ የግል ጥረት በተገኘች የ90+2ኛ ደቂቃ ግሩም ግብ ታግዘው ጨዋታው በአቻ ውጤት አጠናቀዋል፡፡
ውጤቱ ወላይታ ድቻ ባለበት እንዲረጋ ሲያደርገው ኤሌክትሪክን አንድ ደረጃ ወደ ታች አውርዶታል፡፡
የደረጃ ሰንጠረዡ የሚከተለውን ይመስላል፡-
የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ደረጃ
የ13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ የሚቀጥሉ ሲሆን ፕሮግራሙ ይህንን ይመስላል፡-
አርብ የካቲት 25 ቀን 2008
09፡00 ሀዋሳ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ (ሀዋሳ)
09፡00 ሲዳማ ቡና ከ ዳሽን ቢራ (ይርጋለም)
እሁድ የካቲት 27 ቀን 2008
09፡00 ድሬዳዋ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ (ድሬዳዋ)
09፡00 ሀድያ ሆሳዕና ከ ደደቢት (ሆሳዕና)
ማክሰኞ የካቲት 29 ቀን 2008
09፡00 ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮጵያ ቡና (ቦዲቲ)
09፡00 መከላከያ ከ አዳማ ከተማ (አአ ስታድየም)
11፡30 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ኤሌክትሪክ (አአ ስታድየም)