የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከአልጄርያ ጋር ለሚያደርገው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ ትላንት ምሽት ወደ አልጀርስ አቅንቷል፡፡ ሉሲዎቹ ትላንት ጠዋት በአዲስ አበባ ስታድየም የመጨረሻ ልምምዳቸውን በሰሩበት ወቅት በስፍራው የተገኘችው ሶከር ኢትዮጵያ ከቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች መካከል ዋንኛ ከሆኑት ብርቱካን ገብረክርስቶስ እና ሽታዬ ሲሳይ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡
በብሄራዊ ቡድኑ ከፍተኛ ልምድ ያካበተችው ብርቱካን ገብረክርስቶስ በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የቡድኑ አምበል ተደርጋ ተመርጣለች፡፡ የደደቢቷ አማካይ በ2014 የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ የሉሲዎቹ አምበል የነበረች ሲሆን አሁንም የአምበልነት ሃላፊነቱን ለመወጣት እንደማትቸገር ትገልፃለች፡፡ ‹‹ አምበልነት ትልቅ ሃላፊነት ነው፡፡ ነገር ግን ቡድኑን የመምራት ሃላፊነት የእኔ ብቻ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ሁሉም የቡድናችን አባል ራሳቸውን አምበል አድርገው የሾሙ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ አምበል በመሆኔ የሚከብድ ነገር የለም፡፡ ›› ትላለች፡፡ አክላም ከ17 አመት በታች እና 20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ሉሲዎቹን የተቀላቀሉት ተጫዋቾችም ከቡድኑ ጋር ለመላመድ እንዳልተቸገሩ ትገልፃለች፡፡
‹‹ቡድናችንን አዳዲስ ተጫዋቾች ቢቀላቀሉንም ከኛ ጋር ለመዋሃድ የከበዳቸው ነገር የለም፡፡ ሁሉንም ነገር ለመቀበል ያላቸው ዝግጁነት እና ፍላጎት የሚያስደስት ነው፡፡ ››
ከወራት በፊት ከማጣርያ ድልድሉ ውጪ በመሆኗ ምክንያት መነጋገርያ የነበረችው ሃገራችን እሁድ አመሻሽ ላይ ከአልጄርያ ጋር የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታዋን ታደርጋለች፡፡ ብርቱካንም በድጋሚ ያገኙትን እድል በአግባቡ መጠቀም እንደተዘጋጁ ተናግራለች፡፡
‹‹ ከአልጀርስ መልካም ውጤት ይዘን መመለስና ህዝባችንን ማስደሰት እኛንም ከፍ ያለ ደረጃ ማድረስ እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም ይህ እድል የተገኘው በከፍተኛ መስዋዕትነት ነው፡፡ ይህን እድል ደግሞ አሳልፈን መስጠት አንፈልግም፡፡ ሜዳ ላይ የምንችለውን አድርገን ለመምጣት ተዘጋጅተናል፡፡ ›› ስትል ሃሳቧን አጠቃላለች፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ግብ አዳኝ ሽታዬ ሲሳይም እንደ ብርቱካን ሁሉ በድጋሚ የተገኘውን እድል በዋዛ አሳልፈው መስጠት እንደማይገባ ትናገራለች፡፡
‹‹ በመጀመርያ ከድልድሉ መውጣታችን ሲነገር መደረግ የሌለበት ተግባር በመሆኑ በጣም አዝነን ነበር፡፡ ኋላ ላይ መመለሳችን ስንሰማ እጅግ ተደስተናል፡፡ በህዝቡ እና መገናኛ ብዙሃኑ ጥረት ፍሬ አፍርቶ ተመልሰናል፡፡ አሁን ይህንን እድል እንዲሁ ማሳለፍ የለብንም፡፡ ወደ ውድድሩ ገባን ለማለት ብቻ ሳይሆን ብዙ ርቀት ተጉዘን ስማችንን መመለስ ይገባናል፡፡
ለአልጄርያው ጨዋታ ያደረግነው ዝግጅት መልካም ነበር፡፡ በየእለቱ የተለያዩ ልምምዶችን ስንሰራ ነበር፡፡ የአልጄርያ አጨዋወት ላይ የተመረኮዘ አጨዋወት ለመተግበርም ልምምድ አድርገናል፡፡ጥሩ በመዘጋጀታችን ጥሩ ውጤት ይዘን እንመጣለን ብዬ አስባለሁ፡፡››
ባለፉት የውድድር ዘመናት ከ30 በላይ ግቦች በማስቆጠር ግብ አዳኝነቷን ያስመሰከረችው ሽታዬ ዘንድሮ የግብ መጠኗ እንደቀደመው መሆን አልቻለም፡፡ ነገር ግን ወቅታዊ የግብ ማስቆጠር ብቃቷ በብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ላይ ተፅእኖ እንደማይፈጥርባት ተማምናለች፡፡
‹‹ በርካታ ግቦች አለማስቆጠሬ በብሄራዊ ቡድኑ ላይ ተጽእኖ ይፈጥርብኛል ብዬ አላስብም፡፡ አቅሜን አውቀዋለሁ፡፡ አጥቂ እንደመሆኔ ጎል ፊት ምን ማድረግ እንዳለብኝም አውቃለሁ፡፡›› ብላለች፡፡