የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ለአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ትላንት አልጄርያ ገብቷል፡፡ ቡድኑ አልጄርያ ሲደርስ በአልጄርያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አቀባበል የተደረገለት ሲሆን በዛሬው እለት በሚጫወቱበት ሜዳ ልምምዳቸውን አከናውነዋል፡፡
ቡድኑ ዴር ዲአፍ በተባለ ሆቴል ያረፈ ሲሆን በሆቴሉ ደረጃ እና በሚደረግላቸው መስተንግዶ ደስተኛ መሆናቸውን አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ አሰልጣኝ ብርሃኑ አክለውም ሁሉም ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ የሚገኙ ሲሆን የነገውን ጨዋታ ለማድረግ በጉጉት እየጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአልጀርስ ወቅታዊ የአየር ሁኔታም ንፋስ የበዛበት እንደሆነ ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
ሉሲዎቹ ከ2014 የናሚቢያ አፍሪካ ዋንጫ በጋና በድምር ውጤት 5-0 ተሸንፈው የቀሩ ሲሆን በነገ 12፡00 ጨዋታ ከ2 አመት በኋላ ድል ማስመዝገብን አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ፡፡
ዲሞክራቲክ ኮንጎ ከውድድሩ ራሷን በማግለሏ ምክንያት ተጋጣሚዋ ኬንያ በቀጥታ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈች በመሆኑ የኢትዮጵያ እና የአልጄርያ አሸናፊ ኬንያን የሚገጥም ይሆናል፡፡
ሌሎች የማጣርያ ጨዋታዎች
ረቡዕ የካቲት 26 ቀን 2008
ታንዛንያ 1-2 ዚምባብዌ
ቅዳሜ የካቲት 27 ቀን 2008
ቦትስዋና 7-0 ሞሪሸስ
ቡርኪናፋሶ 0-0 ቱኒዚያ
ሴኔጋል 1-0 ጊኒ
ማሊ 0-0 ሞሮኮ
እሁድ የካቲት 28 ቀን 2008
ሊቢያ ከ ግብፅ
ዛምቢያ ከ ናሚቢያ