ኢትዮጵያዊው አጥቂ ጌታነህ ከበደ ቋሚ ሆኖ በተሰለፈበት ጨዋታ የፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ በኔድባንክ ካፕ ፖሎክዋኔ ሲቲ ሮቨርስን 5-0 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ወደ ተከታዩ ዙር አልፏል፡፡
የፕሮቶሪያው ክለብ የደቡብ አፍሪካ ሶስተኛ ዲቨዚዮን ክለብ በሆነው ፖሎክዋኔ ሲቲ ሮቨርስ ላይ የግብ ናዳ ባወረደበት ጨዋታ ጌታነህ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ጨዋታው በተጀመረ በ11ኛው ደቂቃ ጌታነህ ዋሽንግተን አሩቢ እና አቱሳዬ ናዮንዶ ያመቻቹለን ኳስ ተጠቅሞ የአማተክስን የመጀመሪያ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ቀሪዎቹን ግቦች የማላዊ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች የሆነው ናዮንዶ፣ ሲቡሲሶ ማትትዋ፣ ቩዪሲሌ አቶምባዪቴቲ እና አዲስ ፈራሚው ታቦ ኔሙኮንዴኒ ከመረብ አዋህደዋል፡፡
ጌታነህ በሁለተኛው አጋማሽ 71ኛው ደቂቃ በናኮና ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል፡፡ የዋሊያዎቹ የፊት መስመር ተሰላፊ ከሳምንት በፊት በአብሳ ፕሪምየርሺፕ አማተከስ ቺፓ ዩናይትድን 3-0 ሲያሸንፍ በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ግቡን ያስቆጠረ ሲሆን ትላንት ደግሞ ሁለተኛውን ግብ አክሏል፡፡