የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በሴካፋ ለሚሳተፉ ሀገራት የአቀባበል እና የራት ግብዣ ሥነ-ስርዓት አከናውኗል

41ኛው የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር መጀመሪያ ዋዜማ ቀን ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለተሳታፊ ሀገራት የአቀባበል እና የእራት ግብዣ መርሐ-ግብር አከናውኗል።

ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከሠላሳ ጀምሮ በተከናወነው የእንኳን ደህና መጣችሁ የእራት ግብዣ ፕሮግራም ላይ የተሳታፊ ሀገር ተወካዮች፣ አሠልጣኞች እና አመራሮች ተገኝተዋል። ከእግርኳስ ግለሰቦች በተጨማሪ የኢፌዴሪ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ድኤታ ክቡር አቶ ዲና ሙፍቲ፣ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ (የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ) እና የሴካፋ ጄኔራል ሴክሬተሪ አውካ ጌቼዮ በስፍራው ታድመዋል።

በባህር ዳረር ኩሪፍቱ ሪዞርት በተከናወነው መርሐ-ግብር ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል። ፕሬዝዳንቱም በንግግራቸው ተሳታፊ ሀገራት በባህር ዳር በሚኖራቸው ቆይታ ምንም ችግር እንደማይገጥማቸው እና እንደ ቤታቸው እንደሚስተናገዱ ገልፀዋል። በዋናነት ደግሞ ኢትዮጵያ በስፖርቱም ሆነ ከስፖርት ውጪ ባሉ ዘርፎች በአፍሪካ መድረክ ያላትን የጎላ ታሪክ አውስተዋል። ቀጥለውም ኢትዮጵያ ከሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት ልዩ የሚያደርጋትን ባህል፣ ወግ፣ ትውፊት እና ልማድ አስተዋውቀው ውድድሩ ያማረ እንዲሆን ያላቸውን ምኞት ገልፀዋል።

ከፕሬዝዳንቱ ንግግር በኋላ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በውድድሩ ለሚሳተፉ አባል ሀገራት ያዘጋጀውን የማስታወሻ ስጦታ መሰጠት ተጀምሯል። ለዘጠኙም ሀገራት የተዘጋጀውን ስጦታም አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና አቶ አበበ ገላጋይ (የሴካፋ ውድድር ብሔራዊ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ) ሰጥተዋል። ባህር ዳር ካልገቡት የታንዛኒያ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሔራዊ ቡድኖች ውጪም ሁሉም ሀገራት ከክብር እንግዶቹ የማስታወሻ ስጦታቸውን ተረክበዋል።

ስጦታ የመስጠት መርሐ-ግብሩ ከተከናወነ በኋላ እንግዶች እራት እንዲመገቡ ተደርጓል። ከእራቱ በኋላ ደግሞ ሌላ የስጦታ አሠጣት መርሐ-ግብር ተከናውኗል። በዚህም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ በንግግራቸው እንደገለፁት ኢትዮጵያ በቡና እንደመታወቋ ለእንግዶች የኢትዮጵያ ቡና ምርት ያለበት ስጦታ ተሰጥቷል። ስጦታውንም ዶ/ር ድረስ፣ አቶ ኢሳይያስ እና አቶ አበበ ሰጥተዋል።

የዕለቱ ዋና መርሐ-ግብሮች ከተጠናቀቁ በኋላ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ በስፍራው የተገኙ እንግዶችን ባህላዊ ጭፈራ በስፍራው ከነበረው ባህላዊ ባንድ ጋር በመሆን ሲያስጨፍሩ ነበር። በአሁኑ ሰዓትም የሙዚቃ እና የጭፈራ ዝግጅቱ እየቀጠለ ይገኛል።