የሴካፋ ከ23 ዓመት በታች ውድድር የዛሬ ውሎ

በአራተኛ ቀን የሴካፋ ውድድር ኬንያ እና ታንዛኒያ ደቡብ ሱዳን እና ዲሞክራቲክ ኮንጎን ረተዋል።

👉 ደቡብ ሱዳን 0-2 ኬንያ

እምብዛም ሳቢ እና ተመጣጣኝ ፉክክር ባልተደረገበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ላይ ሙከራ መስተናገድ የጀመረው በ4ኛው ደቂቃ ነበር። በዚህ ደቂቃም ኦጊንጋ ቤናርድ ኦቺንግ ከመዓዘን የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ መክኖበታል። ከኳስ ጋር ዘለግ ያለውን ጊዜ ባማሳለፍ የሚጫወቱት ደቡብ ሱዳኖች በበኩላቸው በ20ኛው ደቂቃ የራሳቸውን የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ በስቴፈን ፓዋር ሎኒ አማካኝነት ቢያደርጉም ኳሱን የግብ ዘቡ ብሪያን ቢዊሪ አድኖባቸዋል።

የሚያገኙዋቸውን ኳሶች በፍጥነት የሚቀባበሉት ኬንያዎች በአንፃራዊነት ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ወደ ግብ መድረስ ይዘዋል። በ25ኛው ደቂቃም አቶላ ሄነሪ ከመሐል የደረሰውን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ በመጠቀም ጥሩ ጥቃት ፈፅሞ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ጥሮ ነበር። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ስድስት ደቂቃዎች ሲቀሩትም ይሄንን ሙከራ ያደረገው ሄነሪ ሌላ ጥሩ ኳስ ደቡብ ሱዳኖች የግብ ክልል በመድረስ ቢያደርግም ሀሳቡ ሳይሰምር ቀርቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም ያለ ጎል 0-0 ተጠናቋል።

የሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ኬንያዎች በ51ኛው ደቂቃ በኦቲኖ ሬጋን አማካኝነት መሪ የሆኑበትን ጎል አስቆጥረዋል። በተቃራኒው በተጋጣሚ ሜዳ ሲደርሱ ረጃጅም ኳሶችን ማዘውተር የያዙት ደቡብ ሱዳኖች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ለማግኘት መታተር ጀምረዋል። በተለይ ስቴፈን ፓዋር ሎኒ ከምቹ ቦታ ላይ ያገኘውን የቅጣት ምት አክርሮ መትቶት ለጥቂት የወጣበት አጋጣሚ ለቡድኑ አስቆጪ ዕድል ነበረች።

ጨዋታው ቀጥሎም በ79ኛው ደቂቃ ኬንያ መሪነቷን ወደ ሁለት ያሳደገችበትን ጎል አግኝታለች። በዚህ ደቂቃም በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ቤንሰን ኦቼንግ ከወደ ቀኝ ባዘነበለ ቦታ መነሻን ያደረገ ኳስ በጥሩ አጨራረስ ከመረብ ጋር አዋህዶታል። ሁለተኛውን ጎል ከተቆጠረ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደቡብ ሱዳኖች በማኩቴ አኪን አማካኝነት እጅግ የሰላ ኳስ ሞክረው የነበረ ቢሆንም ኳስ እና መረብ ሳይገናኝ ቀርቷል። ጨዋታውም በኬንያ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም የኬንያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያው የምድብ አላፊ ቡድን መሆኑ ተረጋግጧል።

👉ታንዛኒያ 1-0 ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ

ፈጣን እንቅስቃሴ የተስተዋለበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሽግግሮች፣ ፍልሚያዎች፣ ጉሽሚያዎች እና መመላለሶች የበዙበት ነበር። በአንፃራዊነት ኳሱን በተሻለ ተቆጣጥረው ለመጫወት የሞከቱት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎዎች በ13ኛው ደቂቃ በንሱንዲ ንላንዱ ክርስቲያን አማካኝነት ጥሩ ጥቃት ፈፅመው ነበር። በድጋሜ ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ባሌኬ ኦቶስ ያን ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ በመዝለል በግንባሩ ወደ ግብ ቢልከውም ግብ ጠባቂው ቦኒፌስ ምናታ መልሶበታል።

ወደ ኮንጎ የግብ ክልል በቀላሉ ለመድረስ ያልቻሉት ታንዛኒያዎች ከኳስ ጀርባ በመሆን መንቀሳቀስን መርጠዋል። እስከ መጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ድረስም አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። ኮንጎዎች ግን ተከላካዮቻቸውን ወደ መሐል ሜዳው በማስጠጋት ሲጫወቱ እንዲሁም አጥቂዎቻቸው የተጋጣሚን ተከላካዮች እንዲያስጨንቁ የሚያደርግ እንቅስቃሴ ሲከተሉ ታይቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የሚያገኙዋቸውን የቆሙ እና ተሻጋሪ ኳሶችንም ሲጠቀሙ ነበር። በዚህ አጨዋወትም በ32ኛው ደቂቃ ማንጊንዱላ ሄኖክ ያሻገረውን የቅጣት ምት ባሌኬ ኦቶስ ያን ለመጠቀም ጥሮ መክኖበታል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ይህንኑ ሙከራ ያደረገው ባሌኬ ያን ሳጥን ውስጥ እጅግ ጥሩ ኳስ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ወደ ጎል የመታውን ኳስ በጨዋታው አልቀመስ ያለው ግብ ጠባቂ አውጥቶበታል። ታንዛኒያዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ላይ የራሳቸውን የመጀመሪያ ሙከራ አድርገው ነበር። በዚህም ምዋንዛ ላውረንት ከርቀት የመታው ኳስ ለጥቂት ግብ ጠባቂው ጨርፏት ወጥታለች።

ሁለተኛውንም አጋማሽ በጥሩ መነሳሳት የጀመሩት ኮንጎዎች መሪ ለመሆን የሚያስችላቸውን ዕድል መፈለግ ቀጥለዋል። በዚህም በ58ኛው ደቂቃ ኪንሳንጋላ ክሪስት በሩቁ ቋሚ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ቢልከውም ለጥቂት ወጥቶበታል። በቀጣዩ ደቂቃ ግብ የሚያስቆጥሩ የሚመስሉት ኮንጎዎች በ66ኛው ደቂቃ ሳይታሰብ ግብ አስተናግደው መመራት ጀምረዋል። በዚህም ሪልየንት ምዋካሳጉሌ ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በጥሩ ቦታ አያያዝ በመጠበቅ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።

ወደ መሪነት የተቀየሩት ታንዛኒያዎች በ79ኛው ደቂቃ በጥሩ የማጥቃት ሽግግር ተጨማሪ ጎል ተቀይሮ በገባው አንድሪው ሲንቺምባ አማካኝነት ለማግኘት ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋን እያደረገች የምትገኘው ኮንጎ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በውድድሩ ያላትን ተስፋ ለማለምለም ጥራለች። በተለይ በ80ኛው ደቂቃ ኪምቩይዲ ካሪም ከርቀት በመታው ኳስ ቡድኑ አቻ ሊሆን ነበር። ቡድኑም በቀሪዎቹ ደቂቃዎ ግብ ለማግኘት ቢጥርም የታንዛኒያን የኋላ መስመር ማለፍ ሳይችል ጨዋታው ተገባዷል።