በዝናብ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ጨዋታ በቡሩንዲ አሸናፊነት ተጠናቋል

የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በትናንትናው ዕለት የተከናወነው እና በዝናብ ምክንያት ወደ ዛሬ የተዘዋወረው ጨዋታ ቡሩንዲን አሸናፊ አድርጎ ተገባዷል።

በምድብ ሁለት የሚገኙት ቡሩንዲ እና ኤርትራ በትናንትናው ዕለት እያደረጉ የነበረው ጨዋታ በስታዲየም በጣለው ከባድ ዝናብ 46ኛው ደቂቃ ላይ መቋረጡ ይታወሳል። የምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታዋን እያደረገች የነበረችው ቡሩንዲም በንሽሚሪማና እስማኤል የ16ኛ ደቂቃ ጎል አንድ ለምንም እየመራች ነበር። ዛሬ ከ5 ሰዓት ጀምሮ በተከናወነው ቀሪ የጨዋታው ደቂቃም ቡሩንዲ ሁለት ተጨማሪ ጎሎችን አስቆጥራ በአጠቃላይ ሦስት ለምንም አሸንፋለች።

ጨዋታውን በጥሩ መነሳሳት የጀመሩት ቡሩንዲዎች ገና የተቋረጠው ጨዋታ በተጀመረ በ7ኛው ደቂቃ ትላንት የጀመሩትን መሪነት አስፍተዋል። በዚህም ሩኩንዶ አብዱራማኒ ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በጥሩ የአንድ ንክኪ ወደ ጎልነት ቀይሮታል። ገና ከጅምሩ ፈተናው የጠናባቸው ኤርትራዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ወዲያው መታተር ይዘዋል። በ67ኛው ደቂቃም ከቅጣት ምት የተገኘን ኳስ ሮቤል ተክለሚካኤል በግንባሩ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ቡድኑን ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሞክሯል። ነገርግን ኳሱ ግብ ሳይሆን ቀርቷል።

በዝናባማው አየር የቀጠለው ጨዋታ 73ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ አስተናግዷል። በዚህም የኤርትራው አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ጎል የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ መልሶበታል። ሁለቱ ጎሎች ያልበቃቸው ቡሩንዲዎች በ83ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ወደ ሦስት አሳድገዋል። በዚህም ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ሀኪዚማና ኢሳ በግንባሩ ክብሮም ሠለሞን መረብ ላይ አሳርፎታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል።

ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ ሁለት ቡሩንዲ በ3 ነጥብ ስትመራ ኢትዮጵያ በአንድ ነጥብ ሁለተኛ ሆናለች። የምድብ ጨዋታዋን የጨረሰችው ኤርትራ ደግሞ በ1 ነጥብ እና 3 የግብ እዳ የምድቡ ግርጌ ላይ ተቀምጣለች። በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንም ከምድቡ አንደኛ ሆኖ ለማለፍ የመጨረሻ ጨዋታውን ማሸነፍ ይጠበቅበታል።