ወላይታ ድቻ የአማካዩን ውል አራዝሟል

የጦና ንቦቹ የአማካዩ እድሪስ ሰዒድን ውል አራዝመዋል፡፡

በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም መሪነት አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን እያስፈረሙ የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች በዛሬው ዕለት የአማካዩ እድሪስ ሰዒድ ውል ለሁለት ተጨማሪ አመት አራዝመዋል፡፡ የቀድሞው የወልድያ ከተማ እና ወሎ ኮምቦልቻ የአጥቂ አማካይ ስፍራ ተጫዋች በ2011 ክረምት ወሎ ኮምቦልቻ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ የወቅቱ የድቻ አሰልጣኝ የነበሩት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ባሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ መነሻነት አስፈርመውት ያለፉት ሁለት ዓመታትም በክለቡ ቆይታን አድርጓል፡፡ ውሉ ከክለቡ ጋር መጠናቀቁን ተከትሎ ከድሬዳዋ ከተማ እና ከሀዋሳ ከተማ ጋር ስሙ ቢነሳም በድንጉዛ ለባሾቹ ቤት ተጨማሪ ዓመታት መቆየቱ ተረጋግጧል፡፡

ወላይታ ድቻ በድምሩ የአምስት ነባር ተጫዋቾች ውል ጨምሮ የሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ፈፅሟል፡፡