ኢትዮጵያ ቡና በአህጉራዊ ውድድር ተጋጣሚውን አውቋል

በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ሀገራችንን የሚወክለው ኢትዮጵያ ቡና የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታው ከማን ጋር እንደሆነ ታውቋል።

በአሠልጣኝ ካሣዬ አራጌ የሚመራው ኢትዮጵያ ቡና በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 41 ነጥቦችን በመያዝ ሁለተኛ ሆኖ እንዳጠናቀቀ ይታወቃል። ይህንን ተከትሎም ቡድኑ ከ10 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ የክለቦች የውድድር መድረክ ተመልሷል።

ለውድድሩ ዝግጅት ማድረግ ከጀመረ ቀናት ያስቆጠረው ክለቡም ከደቂቃዎች በፊት በመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ከማን ጋር እንደሚፋለም ታውቋል። በዚህም ኢትዮጵያ ቡና ከዩጋንዳው ክለብ ዩጋንዳ አር ኤ ጋር የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል። ቡናማዎቹም በቅድሚያ ወደ ዩጋንዳ አምርተው የሚጫወቱ ሲሆን የመልሱን ጨዋታ ደግሞ ከሳምንት በኋላ ባህር ዳር ላይ የሚከውኑ ይሆናል። የቡና እና ዩ አር ኤ አሸናፊ ደግሞ በሁለተኛ ዙር ማጣሪያ ከግብፁ አል መስሪ ጋር የሚጫወት ይሆናል።