የሴቶች ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በአራዳ ክፍለከተማ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

በሁለት ምድብ ተከፍሎ በአስር ክለቦች መካከል ሲደረግ የቆየው የኢትዮጵያ ሴቶች ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በአራዳ ክፍለ ከተማ አሸናፊነት በዛሬው ዕለት ተጠናቋል፡፡

(በብሩክ ሀንቻቻ)

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ለመጀመሪያ ከሐምሌ 19 ጀምሮ በሁለት ምድብ ተከፍሎ በአስር ክለቦች መካከል ሲደረግ የቆየው የ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በዛሬው ዕለት በተደረጉ ሁለት መርሀግብሮች ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ በማስቀደም 3፡00 ሲል የደረጃ ጨዋታ ተከናውኖ የከምባታ ዞን እና የሀላባ ዞን ተገናኝተው ከምባታ ዞን 2-1 በሆነ ዉጤት በማሸነፍ ዉድድሩን በሦስተኝነት በማጠናቀቅ የነሀስ ሜዳልያ ተሸላሚ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በማስከተል 5:00 ጀምሮ የፍፃሜዉ የዋንጫ ጨዋታ በአራዳ ክፍለ ከተማ እና በሱሉልታ ከተማ መካከል የተደረገ ሲሆን አራዳ ክፍለ ከተማ 1-0 በሆነ ዉጤት አሸንፎ የ2013 የኢትዮጵያ የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ሆኗል። ጨዋታው እስከ ዘጠና ደቂቃ ድረስ ያለግብ ሲጓዝ የነበረ ቢሆንም በጭማሪ ደቂቃ ሣራ ድንቁ ለአራዳ ክፍለ ከተማ ብቸኛዋን ግብ ከመረብ በማሳረፍ ጨዋታው በአራዳ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቆ ክለቡም ሻምፒዮን መሆን ችሏል፡፡ ወደ መጫወቻ ሜዳ ሲመጡ አስቀድመዉም “ሻምፒዮን” የሚል ቲሸርት ለብሰዉ የተገኙት አራዳዎች በመጨረሻም ባለድል መሆን ችለዋል።

አቶ ሰለሞን ገብረሥላሴ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ምክትል ፀሐፊ፣ አቶ ጌታቸው የማነ ብርሀን የፌዴሬሽኑ የሴቶች ልማት ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ፣ የፌዴሬሽኑ የውድድር ዳይሬክተር አቶ ከበደ ወርቁ፣ የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽነር ፍሬው አሬራ እና የክልሉ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት በክብር እንግነት በመገኘት ለተለያዩ አካላት የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል። የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ፣ ሚቲማ የፀጥታ ሥራ ተቋም እንዲሁም ሲዳማ ክልል እና ሀዋሳ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ለውድድሩ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ተበርክቶላቸዋል።

በመቀጠል በዉድድሩ ላይ ኮከብ ተጫዋች ሀና በኃይሉ ከአራዳ ክፍለ ከተማ ስትመረጥ ኮከብ ጎል አግቢ ደግሞ የሱሉልታ ከተማዋ ማርታ ወልዴ በ8 ጎል ሽልማቷን ወስዳለች፡፡ በውድድሩ ላይ 3 ጎል ብቻ ያስተናገደችዉ የአራዳ ክፍለ ከተማዋ ግብ ጠባቂ ሀዳሰ ዝናቡ በኮከብ ግብ ጠባቂነት ተሸላሚ ሆናለች። ኮከብ አሰልጣኝ በመባል የአራዳ ክፍለ ከተማው አሰልጣኝ ዘሪሁን ታዬ ሲመረጥ የውድድሩ ምስጉን ዋና ዳኛ በመባል ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ አስናቀች ገብሬ እንዲሁም በረዳት ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይልፋሸዋ አየለ ተመርጣለች፡፡ ውድድሩን ለመሩ ዳኞች እና ኮሚሽነሮች የሜዳሊያ ስጦታ የተበረከተ ሲሆን የከምባታ ዞን የነሀስ፣ የሱሉልታ ከተማ የብር እና የአራዳ ክፍለ ከተማ የወርቅ እና የዋንጫ አሸናፊ ሆነዋል፡፡

የዉድድሩ አዘጋጅ የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን የዋንጫ ተሸላሚ የሆነ ሲሆን የክልሉ እግርኳስ ፌዴሬሽን ም/ፕሬዚዳንት አቶ አንበሴ አበበ የተዘጋጀውን ዋንጫ ተቀብሏል። በመጨረሻም የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ ተሸላሚ በመሆን አራዳ ክፍለ ከተማ ተሸልሟል።

ወደ ሁለተኛ ዲቪዝዮን ያደጉ ክለቦች

አራዳ ክፍለከተማ፣ ሀላባ ዞን፣ ወላይታ ዞን እና ሰበታ ከተማ፤ ከምድብ ለ ሱሉልታ ከተማ፣ ከንባታ ዞን፣ አሰላ ከተማ እና ፔንዳ ክለብ