የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት እና ዋና ፀሐፊ አዲስ አበባ አይገኙም

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና ዋና ፀሐፊው ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር አቅንተዋል።

በካሜሩን አስተናጋጅነት በቀጣይ ዓመት በሚዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የሆነችው ኢትዮጵያ በየትኛው ምድብ ትደለደላለች የሚለውን ነገ አመሻሻሽ ላይ በካሜሩን ያውንዴ ከተማ የሚታወቅ ይሆናል። በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመታደምም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ እና ዋና ፀሐፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን ወደ ሥፍራ አቅንተዋል።

ደማቅ ምሽት ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው በዚህ ፕሮግራም ላይ ናይጄሪያዊቷ እውቅ አስተዋዋቂ እና ፕሮዲውሰር ሚሚ ፋዋዝ እና ካሜሩናዊው የቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ፕሮግራሞች አቅራቢ ሊዮናርድ ቻተሌን መድረኩን የሚመሩት ሲሆን የአህጉሪቱ ታላላቅ የእግርኳስ ሰዎች በመርሐግብሩ ላይ እንደሚታደሙ ይጠበቃል።

ሶከር ኢትዮጵያ በዕጣ ማውጣቱ ዙርያ ዐበይት ጉዳዮችን እየተከታተለች ወደ እናንተ የምታደርስ መሆኑን ከወዲሁ እንጠቁማለን።