ፈረሰኞቹ አዲሱ አሠልጣኛቸውን አስተዋውቀዋል

የቅዱስ ጊዮርጊስ አዲሱ አሠልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲች ዛሬ ከሰዓት በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ በይፋ ከጋዜጠኞች ጋር ተዋውቀዋል።

የ27 ጊዜ የኢትዮጵያ ሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሳምንታት በፊት የ64 ዓመቱ ስርቢያዊ ዝላትኮ ክራምፖቲችን ዋና አሠልጣኝ አድርጎ መሾሙን መግለፁ ይታወቃል። ቅዳሜ አዲስ አበባ የደረሱት አሠልጣኙም ትናንት ወደ ቢሾፍቱ አቅንተው ከቡድኑ ተጫዋቾች ጋር ተዋውቀው የክለቡን አካዳሚ (ይድነቃቸው አካዳሚ) ጎብኝተው ነበር። ዛሬ ከሰዓት ደግሞ በቅሎ ቤት አካባቢ በሚገኘው እና በአዲስ መልክ በታደሰው የስፖርት ማኅበሩ የመዝናኛ ማዕከል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ አሠልጣኙ በይፋ ከጋዜጠኞች ጋር እንዲተዋወቁ እና መግለጫ እንዲሰጡ ተደርጓል። ዋና አሠልጣኙ ዝላትኮ ክራምፖቲችን ጨምሮ የስፖርት ማኅበሩ የቦርድ ሊቀ-መንበር አቶ አብነት ገብረመስቀል፣ የቦርድ አባሎቹ አቶ ንዋይ በየነ እና ዳዊት ውብሸት እንዲሁም አቶ ታፈሠ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይም ተገኝተዋል።

ይጀመራል ተብሎ ከተነገረው ሰዓት 30 ደቂቃዎችን አርፍዶ የተጀመረው ጋዜጣዊ መግለጫ ጅማሮ ላይ የስፖርት ማኅበሩ የቦርድ ሊቀ-መንበር አቶ አብነት ገብረመስቀል ገለፃ ሲያደርጉ ተደምጧል። ሊቀ-መንበሩም ያለፉት ስምንት ወራት ክለቡን የሚመጥን አሠልጣኝ ለማምጣት ሲጣር እንደነበር አውስተው ዝላትኮ ክራምፖቲች በተጫዋችነትም ሆነ በአሠልጣኝነት ዘመናቸው ትልቅ ልምድ አላቸው በመሆኑ እና በዋናነት በአፍሪካ እግርኳስ የሰሩ በመሆናቸው ወደ ክለቡ እንዲመጡ እንደተደረገ አስረድተዋል። አቶ አብነት ይህንን ንግግር ከተናገሩ በኋላም የፈረሰኞቹ አሠልጣኝ ሆነው የተሾሙት ዝላትኮ ክራምፖቲች መድረኩን ተረክበው ለጋዜጠኞች ራሳቸውን አስተዋውቀዋል።

“ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ክለብ ነው። ትልቅ ታሪክ ያለው ክለብም ነው። ይህንን አንጋፋ ክለብ ለማሰልጠን ዕድሉን በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ። ስለራሴ ብዙ ነገር ማውራት አልወድም። ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚመጥነውን ሥራ ለመስራት ተዘጋጅቻለሁ።” በማለት በተጫዋችነት እና በአሠልጣኝነት ዘመናቸው ያገለገሉባቸውን ክለቦች ከጠቀሱ በኋላ ሀሳብ ሰጥተዋል። አጭር ደቂቃ ከፈጀው የሁለቱ ግለሰቦች ገለፃ በኋላ በስፍራው የተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ጥያቄዎችን እንዲጠይቁ ተደርጎ ምላሽ መሰጠት ተጀምሯል።

አሠልጣኙ እንዴት ተመረጡ? መስፈርቶቹስ ምን ነበሩ? ክለቡንስ ይመጥናሉ ወይ?

“መመዘኛዎቹ የተለያዩ ናቸው። መነሻው የዕውቀት ደረጃቸው ነው። ይህ በምንም ሊሻር የማይችል መስፈር ነበር። የዩፋ ፕሮ ወይም ተመጣጣኝ የአሠልጣኝነት ላይሰንስ ያለው አሠልጣኝ ነው ወደ ክለባችን እንዲመጣ የምንፈልገው። የካፍ ኤ ላይሰንስ ራሱ ክለባችንን አይመጥንም። እርግጥ ከፍ ያለ ላይሰንስ ወደ ዋንጫ እንድንሄድ ያደርገናል ብለን ሙሉ ለሙሉ አምነን አይደለም ይህንን መስፈር በዋናነት ያስቀመጥነው። ግን ዕውቀት ያለው አሠልጣኝ ተጫዋቾቹ ጋር ተገቢውን እና ሳይንሳዊውን ትምህር እንዲያስተላልፍ ስለምንፈልግ ነው። ምክንያቱም የረጅም ጊዜ እቅዳችን በራሳችን ተጫዋቾች ክለባችንን መምራት ስለሆነ።

“በሁለተኝነት ልምድ እናያለን። በተለይ በአፍሪካ የሰሩ አሠልጣኞችን እንመለከታለን። በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ውድድሮች ያላቸውን እና የደረሱበትን ቦታ እናጠናለን። ከዚህ ጋር ተያይዞ የአፍሪካ ተጫዋቾችን የማወቃቸው ደረጃ እንዲሁም የሊጋችንን ነባራዊ ሁኔታ ተገንዝበን እንመርጣቸዋለን። እውነት ለመናገር ከኢትዮጵያ ከፍ ያሉ ሊጎችን ያሰለጠኑ አሠልጣኞችን ለማምጣት ገንዘብ ያስፈልጋል። ስለዚህ በአቅማችን ልክ ሦስተኛ መመዘኛ አድርገን ገንዘብን እናስቀምጣለን።” አቶ ንዋይየአሠልጣኙን የቀደመ ታሪክ አጥንታችኋል?

“የአሠልጣኙ የክለብ ቆይታ በአማካኝ ትንሽ ነው። ይህንን እኛም አይተነዋል። ምክንያቶቹንም ጠይቀን ተረድተናል። በአብዛኛው ከደሞዝ ክፍያ፣ ከአስተዳደር ችግሮች፣ በስራ ጣልቃ ከመገባት ጋር ተያይዞ የሚመጡ እንደሆኑም አውቀናል። እነዚህ ችግሮች ጊዮርጊስ ቤት የሉም። ጊዮርጊስ ለእሳቸው አመቺ ቤት እንደሆነ ተረድተን ነው ያመጣናቸው። ግን የአሠልጣኝ ህይወት የታወቀ ነው። ውጤት ከመጣ ይቆያል ካልመጣ ሊሰናበት ይችላል።” አቶ ንዋይ

የሀገር ውስጥ አሠልጣኝ ለምን አልተመለከታችሁም?

“የጊዮርጊስ የሁል ጊዜ እቅድ ምን እንደሆነ ይታወቃል። በአፍሪካ ውድድሮች ጥሩ ደረጃ መድረስ ነው። አሁን ግን እዚህ ያለውን ሊግ ማለፍ አለብን። ለዚህ ደግሞ መጎበዝ እና አንደኛ መውጣት ይጠበቅብናል። በአህጉራዊ ውድድር ያስቀመጥነውን ዋነኛ ግባችንን እንድንሳካ ደግሞ እኚህን አሠልጣኙ አምጥተናል። ጊዮርጊስ በሙከራ የሚሰራበት ክለብ አይደለም። ሁሌ ሀሳባችን አሸናፊ መሆን ነው። የሀገር ውስጥ አሠልጣኝ ችሎታ እና እውቀቱ ካለው ወደምናስበው ቦታ ሊወስደን ይችላል። የሀገር ውስጥ አሠልጣኝ አይወስደንም የሚል አመለካከት የለንም። እኛ እንደውም የሀገር ውስጥ እና አቅም ያለው አሠልጣኝ መጥቶ ወዳሰብነው መንገድ ቢወስደን ደስ ይለናል።” አቶ አብነት


የአሠልጣኙ ልምድ እና የጨዋታ መንገድ ምን ይመስላል?

“በአፍሪካ የተለያዩ ክለቦች በመስራት ልምድ አካብቻለሁ። ጥሩ ውጤትም አምጥቼ አውቃለሁ። ግን አፍሪካ ውስጥ የተለያዩ ችግሮች አሉ። ችግሮቹን አሁን መዘርዘሩ ብዙም አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም። ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ግን በፊት ያጋጠሙኝ አይነት ችግሮች ይፈጠራሉ ብዬ አላስብም።

“እኔ የጨዋታ ፍልስፍና ማጥቃት ነው። ግን ለዚህ አጨዋወት የሚሆኑ ተጫዋቾች ከሌሉህ ወደ ሌላ አማራጭ ለመሄድ ትገደዳለህ።” ዝላትኮ ክራምፖቲች

አሠልጣኝ ከመምጣቱ በፊት ለምን አዳዲስ ተጫዋቾችን ማዘዋወር አስፈለገ?

“ውጪ ሀገር ከአሠልጣኞች በላይ መልማዮች ናቸው ተጫዋቾችን የሚያመጡት። እንደ ስካውት በመሆን። እኛ ደግሞ ያዋቀርነው ኮሜቴ አለ። የአሠልጣኝ ቡድን አባላትን ጨምሮ ከቦርድ የተለያዩ ሰዎችን በማካተት። እንደምታውቁት እኛ ሀገር ደግሞ ተጫዋቾች ትንሽ ናቸው። ያሉትን ተጫዋቾች ደግሞ ልክ ዓመቱ እንዳለቀ ክለቦቹ እንደ ቅርጫ ይቀራመቷቸዋል። አዲሱ አሠልጣኝ መጥቶ ተጫዋቾን የሚያይበት ጨዋታዎች ስለሌሉ በዋናነት ከምክትል አሠልጣኖቹ ጋር ተነጋግረን ለጊዮርጊስ የሚመጥን ተጫዋች በቶሎ እናመጣለን። ይህ ነው ሂደቱ።

“እኛ ቡድን ውስጥ በፊት የተጫወቱ እና አንጋፋ ተጫዋቾች አሉ። በተለይ ለክለቡ ፍቅር ያላቸው የቀድሞ ተጫዋች አሉ። እነሱን ወደራሳችን በማስጠጋት ተጫዋች እንዲመለምሉልን አድርገናል። በየክልሉ እየሄዱ እንዲመርጡ የምናደርግበት አቅም የለንም። ሲጀምር በሊጉ ላይ ሲዘዋወሩ የምናያቸው ተጫዋቾች ውስን ናቸው። ስለዚህ በሊጉ ላይ ያሉትን ጥሩ ተጫዋቾች በቀላሉ ስለምንለይ ቀድመን እናስፈርማቸዋለን። የውጪ ተጫዋቾች ላይ ግን ትንሽ ወደ ኋላ እንቀራለን። ዋና አሠልጣኙ መጥቶ ያለውን ነገር እንዲያይም እናደርጋለን። ምክንያቱም አሠልጣኙም ሆነ እኛ የውጪ ተጫዋቾቹን የምናየው በቪዲዮ ብቻ ስለሆነ። በአጠቃላይ የተጫዋች ዝውውራችን ሙሉ ለሙሉ ትክክል ነው ብዬ አላምንም። ግን ከዚህ በላይ ለመጓዝ የሚይዙን ነገሮች አሉ። ስለዚህ ያለውን መሳሪያ ለመጠቀም ነው ይሄንን መንገድ የመረጥነው።” አቶ አብነት

አሠልጣኙ በቆይታቸው የተሰጣቸው ሀላፊነት ምንድን ነው?

“ከኢንሴንቲቭ ጋርም የተቀናጀ ነገር በውሉ ዝርዝር ላይ አለ። ቅዱስ ጊዮርጊስን ወደ ቻምፒየንስ ሊግ ወይም ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ መመለስ ቀዳሚ ሀላፊነት ተሰጥቷቸዋል። ስለዚህ አንደኛ አልያም ሁለተኛ መውጣት አለባቸው ማለት ነው። ይህንን ካላሳኩ ይባረራሉ ማለትም አይደለም። ግን እነዚሁ ነገሮች ካልተሳኩ አሠልጣኙ የሚያጡት ሽልማት እንዳለ በውሉ ተቀምጧል። በሁለተኛው ዓመት ደግሞ በሴካፋ ውድድር መግባት እንፈልጋለን። ከዚህ ውጪ በቻምፒየንስ ሊግም ሆነ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ከዚህ በፊት ደርሰንባቸው የምናቃቸው ደረጃዎች (ምድብ) ላይ መድረስ ይጠበቅብናል።” አቶ ንዋይ

በትናንትናው ዕለት ተጫዋቾቹን ሲያዩ ምን ታዘቡ?

” እኔ ለቅድመ ውድድር ዝግጅት 42 ቀን ይበቃኛል። በስብስቡ ውስጥ አንድ ተጫዋች ከውጪ የመጣ አለን። ሁለት ተጫዋቾችን ደግሞ በቅርቡ እናመጣለን። ግን አሁን ኢትዮጵያዊ ተጫዋቾች ላይ እናተኩራለን። ትናንት ወጣት ተጫዋቾችን አይቻለሁ። እኔ ደግሞ ከወጣቶች ጋር መስራት ደስ ይለኛል።

“እኔ በራሴ ቡድን ላይ ነው ማተኮር የምፈልገው። ስለ ተጋጣሚ ቡድን ማሰብ አልወድም። እርግጥ አንዳንድ ነገሮችን ማየት አለብኝ። ይህንን አደርጋለው ግን በዋናነት በራሴ ቡድን ላይ ነው የማተኩረው። እንዳልኩት ጊዮርጊስ ትክቅ ክለብ ነው። በአፍሪካ ውድድር ላይም መሳተፍ አለበት። እኛም እቅዳችን ቡድኑን ቢያንስ በምድብ ጨዋታዎች ማብቃት ነው።” ዝላትኮ ክራምፖቲች

በቅዱስ ጊዮርጊስ የአመራሩ ጣልቃ ገብነት አለ ስለሚባለው ጉዳይ?

“እኛ ጋር መጥቶ ያሰለጠነ የትኛውም አሠልጣኝ ምንም አይነት ጣልቃ ገብነት ኖሮበት አያውቅም። አሁን የመጣው አሠልጣኝም 100% ነፃነት ተሰጥቶት ነው የሚሰራው። በፈለገው ነገር ላይ ነፃነት ይሰጠዋል። በተለይ ግን ዲስፕሊን ላይ ትኩረት እንዲያደርግ እናደርጋለን። የራስ ምታት የሆነብን እና ውጤት ያላመጣነውም አንድ በዚህ ችግር ነበር። እንደሚባለው እጃችን ረጅም ቢሆን ዘንድሮ ገና ከጅማሮ ብዙ ውሳኔዎችን እንወስን ነበር። ግን አሠልጣኙ ድምፅ እንዲኖረው አድርገን ታግሰናል። ከዛ ግን ወደ ባህር ዳር ካመራን በኋላ ነገሮች ሲባባሱ ወደ ውሳኔ ያመራነው።” አቶ አብነት

የቀድሞ ተጫዋቾች እና ምክትሎች ጉዳይ?

“የቀድሞ ተጫዋቾቻችን በሚፈለገው መንገድ ላይ እንዲገቡልን እንሻለን። ግን እውነት ለመናገር የቋንቋም ችግር አለ። ምክንያቱም ከፍተኛዎቹ የአሠልጣኝ ትምህርቶች በአማርኛ ስለማይሰጡ። ከዚህም የተነሳ አንዳንዶቹ ተጫዋቾቻችን ትምህርት ቤት እንዲገቡ አድርገናል። ስለዚህ ምክትል አሠልጣኞቻችን እንዲያድጉ እናደርጋለን። እነሱ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ይጠቅማሉ። በቅርቡም የአሠልጣኝነት ኮርስ ለማሰጠት ንግግር እያደረግን ነው። በክለባችን የተጫወቱ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ማደግ የሚፈልጉ የቀድሞ ተጫዋቾችንም አካተን ስልጠናውን ለማሰጠት እንቅስቃሴ እያደረግን ነው።” አቶ አብነት