የአሰልጣኝ ካሣዬ እና የክለቡ ተወካዮች ስብሰባ …

ከምክትል አሰልጣኙ ወል አለመታደስ ጋር በተያያዘ አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ እና የክለቡ ሦስት ተወካዮች ምክክር አድርገዋል።

ረፋድ ላይ በነበረው ዘገባችን አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ ቡድናቸውን ከሚያዘጋጁበት ቢሸፍቱ ከተማ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከኢትዮጵያ ቡና አመራሮች ጋር ሊነጋገሩ እንደሆነ መዘገባችን ይታወሳል።

የክለቡ ሦስት ተወካዮች እና አሰልጣኝ ካሣዬ ያደረጉት ውይይት አጭር እንደነበረ እና የምክትል አሰልጣኙን ውል ክለቡ ላለማራዘም ከውሳኔ የደረሰበትን ምክንያት በሰነድ ከተደገፈ ዝርዝር ጋር ስለማቅረቡ ታውቋል። አሰልጣኝ ካሣዬም ከከተወካዮቹ ጋር ያደረገውን ቆይታ ካጠናቀቀ በኃላ ከክለቡ ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ጋር በተናጥል ቆይታ ማድረጉን ሰምተናል።

ጉዳዩን ለመጨረሻ ጊዜ ለመቋጨት ከውሳኔ የተደረሰ ነገር ባይኖርም ክለቡ የምክትል አሰልጣኙን ውል ላለማራዘም ጠንከር ባለ አቋሙ የፀና መሆኑ አረጋግጠናል።

አዳራቸውን አዲስ አበባ አድርገው ነገ ወደ ቢሸፍቱ የሚያቀኑት አሰልጣኝ ካሣዬ በጉዳዩ ዙርያ ያላቸውን አቋም ለጊዜው ማወቅ አልቻልንም። እየወጡ እንዳሉት መረጃዎች ከሆነ ምክትል አሰልጣኙ ዘላለም ፀጋዬ ከቡድኑ ያለመቀጠላቸው ነገርም እየሰፋ መጥቷል።